መዳን

መዳን የሚለው ቃል ሰፊ ትርጉም ያለው ሲሆን በዚህ ክፍል የተገለጸው የሰው ነፍስ ከኃጢአትና ከደመወዙ ስለምትድንበት ሁኔታ ነው፡፡

 መጽሐፍ ቅዱስ:-

ሕዝ.18÷4 ላይ ፡- “… ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች፡፡” ይላል፡፡

ሮሜ 6÷23 ላይ ደግሞ፡- “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና…” ይላል፡፡

ሮሜ 3÷12 ላይ፡- “ሁሉ ተሳስተዋል÷ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል…” ይላል፡፡

ሮሜ 3÷22-23 ላይም፡- “… ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤” ይላል፡፡

ሮሜ5÷12 ላይ እንዲሁ፡- “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት÷ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤” ይላል፡፡ስለዚህ መዳን የሚያስፈልገው ለሰዎች ሁሉ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ማቴ.16÷26 ላይ የተጻፈው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል፡- “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” ይላል፡፡ ከዚህ ቃል የምንገነዘበው ለሰው ከትርፍ ሁሉ የሚበልጠውና ቀዳሚው ትርፍ የነፍሱ መዳን መሆኑን ነው፡፡

የሰው ነፍስ የሚድነው አዳኙን አንድ አምላክ በማወቅና በማመን ፣ ከኃጢአት ሁሉ ንስሐ በመግባት፣ ለኃጢአት ስርየት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመጠመቅና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ እንደሆነ እናምናለን፡፡

ለመዳን አዳኙን አንድ አምላክ ማወቅና ማመን እንደሚያስፈልግ እናምናለን

አዳኙ አምላክ አንዱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ይህን ከቃሉ አረጋግጠን እናምናለን፡-

 ዘዳ.6÷4፡- “እስራኤል ሆይ÷ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡” ይላል፡፡

ኢሳ.43÷10-11፡- “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ÷ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም፡፡ እኔ÷ እኔ እግዚአብሔር ነኝ÷ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም፡፡” ይላል፡፡

ኢሳ.45÷21-22፡- “…ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ ጻድቅ አምላክና መድኃኒት ነኝ÷ ከእኔም በቀር ማንም የለም፡፡ እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ÷ እኔ አምላክ ነኝና÷ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ፡፡” ይላል፡፡

ሆሴዕ 13÷4  “እኔ ግን ከግብጽ ምድር ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም÷ ከእኔም በቀር ሌላ መድኃኒት የለም፡፡” ይላል፡፡

ይህ አንዱ አምላክ እኛን ከኃጢአታችን ለማዳን በሥጋ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ከቃሉ አረጋግጠን እናምናለን፡፡

1ኛጢሞ.3÷16 “እግዚአብሔርን የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ÷ በመንፈስ የጸደቀ÷ ለመላዕክት የታየ÷ በአሕዛብ የተሰበከ÷ በአለም የታመነ÷ በክብር ያረገ፡፡” ይላል፡፡

ማቴ.1÷18-23 “የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበር፡፡ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ጸንሳ ተገኘች፡፡ …ከእርስዋ የተጸነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና… ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ፡፡ በነቢይ ከጌታ ዘንድ፡- እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል÷ ትርጓሜውም፡- እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው፡፡” ይላል፡፡

1ኛጢሞ.1÷15-17 “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ …ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን፡፡” ይላል፡፡

ኃጢአተኞችን ሊያድን ወደ ዓለም የመጣው ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ኃጢአተኞች ሞተ ተቀበረ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተነሳ ብለን እናምናለን (1ኛቆሮ.15÷3-4)፡፡ ሰዎችም ሁሉ መዳንን የሚያገኙት በጌታ ኢየሱስ የመስቀል ሥራ በማመን ብቻ እንደሆነ እናምናለን (1ኛቆሮ.1÷18-24)፡፡

ስለዚህ ለመዳን ይህን አንዱን አዳኝ አምላክ ማወቅና ማመን ያስፈልጋል፡፡ (የበለጠ ለማወቅ “በሥጋ የተገለጠ አንድ አምላክ” በሚል ርዕስ በቢሾፕ ደጉ ከበደ የተጻፈውን መጽሐፍ ያንብቡ)

ለመዳን ከኃጢአት ሁሉ ንስሐ መግባት እንደሚያስፈልግ እናምናለን

ለመዳን ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ንስሐ መግባት እንደሆነ ከእግዚአብሔር ቃል አረጋግጠን እናምናለን፡፡ በሉቃስ 13÷1-5 በተጻፈው ውስጥ፡- “…እላችኋለሁ፤ ነገር ግን ንስሃ ባትገቡ እንዲሁ ትጠፋላችሁ፡፡” ይላል፡፡

ሕዝ.18÷30-32 የተጻፈው ደግሞ፡- “…ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ፡፡ የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም  ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ ÷ ስለ ምን ትሞታላችሁ? የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና÷ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ፡፡” ይላል፡፡

ንስሐ መግባት የኃጢአትን ስርየት ለማግኘትና ለመዳን ከሚያስፈልጉ ነገሮች  አንዱ በመሆኑ በሉቃስ 24÷ 47 ላይ፡- “በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል፡፡” ይላል፡፡

 

“ንስሐ” ማለትም አንድ ኃጢአተኛ ቀድሞ ይኖርበት ከነበረው የኃጢአት ሕይወት በፍጹም ልቡ ተጸጽቶ ለመመለስ ራሱን ለጌታ ሰጥቶ ወደፊት በጽድቅ ሕይወት ለመኖር መወሰን ማለት ነው፡፡

ወንጌልን ሰምተው በመልዕክቱ ልባቸው የሚነካ ወይም የሚያምኑ ማድረግ ስለሚገባቸው ቀጣይ ነገር በሐዋ:ሥራ 2÷38 ላይ፡- “…ንስሐ ግቡ….” ይላል፡፡

ስለዚህ ለመዳን ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ንስሐ መግባት እንደሆነ እንምናለን፡፡

ለመዳን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ እንደሚያስፈልግ እናምናለን

ጌታ ኢየሱስ ሐዋርያቱን የመዳን ወንጌልን እንዲሰብኩ ሲልካቸው የተናገራቸው ቃል በትኩረት መታየት ያለበት ነው፡፡ ቃሉ በማር.16÷15-16 ላይ፡- “እንዲህም አላቸው፡- ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፡፡ ያመነ የተጠመቀም ይድናል÷ ያላመነ ግን ይፈረድበታል፡፡” ይላል፡፡ ከዚህ ቃል የምንረዳው፡-

አንድ የመዳን ወንጌል ወደ ዓለም ሁሉ የተላከ መሆኑን፣

ይህ አንድ የመዳን ወንጌል ለፍጥረት (ለሰዎች) ሁሉ የሚሰበክ መሆኑን፣

ያንን ወንጌል የሚያምንና የሚጠመቅ እንደሚድን፣

 ያንን ወንጌል የማያምን እንደሚፈረድበት ነው፡፡

ቀደም ሲል ለመዳን አዳኙን አንድ አምላክ ማወቅና ማመን እና ንስሐ መግባት እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ስለሆነ ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸው ለመዳን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡

በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ ለመዳን ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ እንደሆነ የምናምነው በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ላይ ተመሥርተን ነው፡፡

ማር.16÷16 ላይ፡- “…ያመነ የተጠመቀም ይድናል” ስለሚል እኛ “ እምነት ከጥምቀት ጋር፣ ጥምቀት በእምነት ሲሆን ያድናል” ብለን እናምናለን፡፡

ወደ ጥምቀት የማያደርስ እምነትና በእምነት ያልሆነ ጥምቀት ሁለቱ ተለያይተው አይሠሩም፡፡

በሐዋ:ሥራ. 4÷12  ላይ፡- “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና፡፡” ስለሚል እኛ ጥምቀት የሚያድነው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሲከናወን ነው ብለን እናምናለን፡፡ በሐዋ:ሥራ. 2÷38 ላይ፡- “…ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ  በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ” የተባለውም ስለዚህ ነው ብለን እናምናለን፡፡

1ጴጥ.3÷20-21 ላይ  “ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግስት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል” ስለሚል በዚህም ቃል መሰረት እኛ “ ጥምቀት ያድናል” ብለን እናምናለን፡፤

ዮሐ.3÷3-6  መሠረት ጥምቀት ሰው ከውኃ ዳግመኛ የሚወለድበት፣ በቆላ.2÷11-12  መሠረት ሰው በእግዚአብሔር አሠራር በክርስቶስ መገረዝ÷ በእኛ ባልተደረገ መገረዝ የሚገረዝበት፣ በገላ.3÷27 መሠረት ሰው ከክርስቶስ ጋር አንድ ይሆን ዘንድ ተጠምቆ ክርስቶስን የሚለብስበት ነው ብለን እናምናለን፡፡

ሐዋ:ሥራ. 19÷1-5 መሠረት ቀደም ሲል በሌላ ጥምቀት ተጠምቀው የነበሩትም ሰዎች ለኃጢአት ስርየት በጌታ በኢየሱስ ስም መጠመቅ ለመዳን ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ በመሆኑ እንደገና መጠመቅ ያስፈልጋቸዋል ብለን እናምናለን፡፡

ሉቃስ 24÷47 ፣ ሐዋ:ሥራ. 2÷38፣ ሐዋ:ሥራ. 8 ÷4-16፣ ሐዋ:ሥራ. 10÷1-2፣ ቁ.43-48፣ ሐዋ;ሥራ. 19÷1-5፣ ሐዋ:ሥራ. 22÷16 መሠረት ያለ ልዩነት ለሰዎች ሁሉ (ለአይሁድም ለአሕዛብም) በጌታ በኢየሱስ ስም መጠመቅ ለመዳን ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ለመዳን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መቀበል እንደሚያስፈልግ እናምናለን

ጌታ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ የተናገረው ቃል በዮሐ.3÷3-6 ላይ፡- “ኢየሱስም መልሶ፡- እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው፡፡ …እውነት እውነት እልሃለሁ÷ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው÷ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡” ይላል፡፡

ይህ ቃል ሰው ለመዳን ከውኃና ከመንፈስ ዳግመኛ መወለድ እንደሚያስፈልገው ይገልጻል፡፡ ለመዳን ከውኃ የመወለድ ወይም ለኃጢአት ስርየት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የመጠመቅ አስፈላጊነት ቀደም ሲል ስለተገለጸ ከዚህ ቀጥሎ ከመንፈስ ስለመወለድ አስፈላጊነት ተገልïአል፡፡

ዮሐ.3÷6 እንደተጻፈው ከሥጋ (ከአዳም ዘር) የተወለደው ሁሉም ሥጋ (አዳማዊ) ነው፡፡ ሥጋውም፣ ነፍሱም፣ መንፈሱም በኃጢአት ምክንያት የረከሰና የሞተ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው በዳግም ልደት መዳን የሚችለው ከውኃ በመወለድ ብቻ ሳይሆን ከመንፈስም በመወለድ ነው፡፡

ቲቶ 3÷4-5 የተጻፈው ቃል፡- “ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ ÷ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ÷ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ስራ አይደለም፤” ይላል፡፡ በዚህ ቃል መሠረት እኛ ሰው የሚድነው ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብ (በጌታ በኢየሱስ ስም ጥምቀት) እና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ሐዋ:ሥራ. 2÷38 ላይ፡- “ንስሐ ግቡ÷ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ፡፡” የተባለውም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መቀበል ለመዳን ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ ስለሆነ ነው ብለን እናምናለን፡፡

Scroll to Top