አደረጃጀት

ሐዋርያው ጳውሎስ በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጁ ለሆነው ለቲቶ፡-

‹‹…የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፣ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ›› (ቲቶ 1፡5)

እንዳለው በእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ውስጥ መደራጀት የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በምድር ላይ የሚታወቁ ልዩ ልዩ አይነት ተቋማት የሚደራጁበት የየራሳቸው አይነት የሚታወቁ አደረጃጀቶች እንዳሏቸው ሁሉ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያንም የራሱ ስለሆነች አደረጃጀቷ እርሱ እንደወሰነላት ነው፡፡ የቤተክርስቲያን አደረጃጀት በዓለም ላይ ካሉ አደረጃጀቶች ሊኮረጅ አይቻልም፤ ዓለምም የቤተክርስቲያንን አደረጃጀት ልትኮርጅ አትችልም፡፡ ይህም የቤተክርስቲያን ማንነት ከምንም አይነት ተቋም የተለየ ስለሆነ ነው፡፡

በኤፌሶን 1፡22-23 ላይ፡-

‹‹ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት፣ ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተክርስቲያን ሰጠው፡፡ እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት›› ይላል፡፡

በ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡12-13 ላይ፡-

‹‹አካልም አንድ እንደሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን፣ የግሪክ ሰዎችም ብንሆን፣ ባሪያዎችም ብንሆን፣ ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና፡፡ ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል›› ይላል፡፡

በገላትያ 3፡27-28 ላይ፡-

‹‹ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና›› ይላል፡፡

እነዚህንና የመሳሰሉ ሌሎች ድንቅ የእግዚአብሔር ቃሎችን መሰረት በማድረግ እንደ ‹‹አንድ ሰው›› የተመሰለችውን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን የሚመስል ተቋም በዚህ ምድር ላይ የለም፣ ሊኖርም አይችልም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ በአጭር አገላለጽ በሚሊዮንም ሆነ በቢሊዮን የሚቆጠሩ አባላት ቢኖሯትም እግዚአብሔር ግን ‹‹አንድ ሰው›› አድርጎ ነው የመሰረታት፡፡ እያንዳንዱ አማኝ በሰውነት አካል ውስጥ ባለ አንድ የሰውነት ብልት ይመሰላል (1ኛ ቆሮንቶስ 12፡14-31)፡፡ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ተቋም ግን ድርጅታዊ መዋቅሩና ተያያዥ ሕግጋት ናቸው ተቋም አድርገው የሚያቆሙት፡፡ ቤተክርስቲያን የአደረጃጀት መዋቅር ቢኖራትም ማንነቷ ግን በዚያ ሊገለጽ የሚችል አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያን ሕይወቷ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሕያው ሆና እየተንቀሳቀሰች ያለችው ‹‹ሁሉን በሁሉ የሚሞላው የእርሱ ሙላት›› ሆና ስላለችና እስካለችም ድረስ ብቻ ነው፡፡

የቤተክርስቲያን አደረጃጀት የሚወሰነውም በዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረዳት ላይ መሰረት ተደርጎ ነው፡፡ አንድ ሰው አንድ ራስ ብቻ እንዳለው ቤተክርስቲያንም አንድ ራስ ብቻ አላት፤ ያም ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱም ለቤተክርስቲያኑ አገልጋዮችን ሰጥቶአል፣ ይሰጣልም፡፡

በኤፌሶን 4፡11 ላይ፡-

‹‹እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ›› ይላል፡፡

በሐዋርያት ሥራ 15፡2፣ 6-7 ላይ፡-

‹‹በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ጊዜ ስለዚህ ክርክር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቆረጠ … ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ፡፡ ከብሩ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፡- ወንድሞች ሆይ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደመረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ›› ይላል፡፡

እነዚህን ቃላት ስንመለከት በቤተክርስቲያን አገልግሎትና እንቅስቃሴ ውስጥ ብዙ የሚያከራክሩ ጉዳዮች ሊኖሩ ቢችሉም ነገርን እንዲቆርጡ እግዚአብሔር ያስቀመጣቸው አገልጋዮችና ሽማግሌዎች ደግሞ እንዳሉ እናያለን፡፡ ከሽማግሌዎችም መካከል ደግሞ ለየት ተደርጎ የተመረጠ ጴጥሮስም እንዳለ እንረዳለን፡፡

በአራቱ ወንጌላት ተጽፎ እንደምናነበው ደግሞ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረባቸው ጥቂት ዓመታት ‹‹አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ›› ብሎ የመረጠው ስምዖን ጴጥሮስ በአጠገቡ ነበረ፡፡ ቀጥሎም ከሌሎቹ ሐዋርያት ለየት አድርጎ ወደራሱ ያቀረባቸውና ቦአኔርጌስ (የነጎድጓድ ልጆች) ብሎ የሰየማቸው ያዕቆብና ዮሐንስን ጨምሮ ከጴጥሮስ ጋር ሦስቱን እናያለን፡፡ ከዚያም ሰፋ ሲል ደግሞ አስራ ሁለቱን ሐዋርያት እንመለከታለን፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ‹‹ሌሎችን ሰብዓ ሾመ›› ተብሎ እንደተጻፈው ሰባ ምርጦች ነበሩ፡፡ ከዚህ በበለጠ ሲሰፋ ደግሞ ቁጥራቸው በዛ ያሉ የክርስቶስ ተከታዮችን እናያለን፡፡

ይህ የሚያሳየን ቁም ነገር ቢኖር በእግዚአብሔር መንግሥት (በቤተክርስቲያን) ውስጥ የእግዚአብሔርን ሥራ በአግባቡ ለመስራት ከአንዱ ጴጥሮስ ጀምሮ በተዋረድ እስከተከታዮቹ ሕዝብ ድረስ የሚዘረጋ የአሰራር ስርዓት መኖሩን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያንም በዚሁ መሰረት ከክርስቶስ በታች ትዕዛዝን እየተቀበለ አካሉን የሚመራ አንድ ዋና ጠቅላይ እረኛ መኖር እንዳለበት ታምናለች፡፡ ስለዚህም ስያሜው ‹‹ዋና አስተዳዳሪ›› ቢባልም እንደመጽሐፍ ቅዱሱ አሰራር ሁል ጊዜም ከክርስቶስ በታች ሆኖ በኢየሱስ መንፈስና ፈቃድ መንጋውን የሚመራ አንድ መሪ አላት፡፡ በብሉይ ኪዳን የእስራዔል ልጆች በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲወጡና እንዲገቡ እግዚአብሔር ሙሴን መርጦ እንደሰጣቸው በአዲስ ኪዳንም ይህ አሰራሩ አልቀረም፡፡ ሙሴ ሸክም ሲከብድበት (ለብቻው የሕዝቡን የጉዞ ጥያቄ ሸክም መሸከም ሲያቅተው) ሰባ (70) ሽማግሌዎችን መርጦ በሙሴ ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በእነርሱም ላይ አድርጎ እጅ ለእጅ ተያይዘው የእግዚአብሔርን መንጋ ሲመሩ እንደነበረ ተጽፎልናል (ዘኁልቁ 11፡16-30)፡፡

በዚሁ አይነትና መንፈስ በኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን አደረጃጀት ውስጥ ታች በሕዝቡ መካከል ከሕዝቡ ጋር ሆኖ መንጋውን የሚያሰማራ መጋቢ አለ፡፡ መጋቢ የሌለው አንድም በግ የለም፡፡ ካለም የባዘነ በግ ነው፡፡ ይህ የአጥቢያ አደረጃጀት ሲሆን የተወሰነ ቁጥር ያላቸው አጥቢያዎች ደግሞ በንዑስ ሰበካ ተደራጅተዋል፡፡ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ንዑስ ሰበካዎች ደግሞ በቅርንጫፍ ሰበካ፣ ቅርንጫፍ ሰበካዎችም በሰበካ፣ ሰበካና ቅ/ሰበካዎች ደግሞ በሃገረ ስብከት ደረጃ ተዋቅሮና ተደራጅቶ ሁሉም አይነት የእግዚአብሔር መንግሥት አገልግሎት በአንድ መንፈስና በአንድ ራዕይ ይከናወናል፡፡ የዳነ ሰው ሁሉ በዚህ በአንድ አካል እንደ ብልት ተሰክቶ ሕያው ሆኖ ይኖራል፤ ከአንድ ምንጭ ይጠጣል፣ አንዱን ማዕድ ይካፈላል፡፡

ጠቅላይ እረኛ (ወይም ዋና አስተዳዳሪ) ከላይ እንደ ሙሴ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን በአጠገቡ ሸክሙን አብረው የሚካፈሉ 12 አባላት ያሉት ስራ አስፈጻሚዎች እና 50 ያህል የሚሆኑ የጠቅላይ ቦርድ አባላት የአካሉን ስራ በአንድ መንፈስ ያከናውናሉ፡፡ ሁሉም የተሰጠው ሰፋፊ የስራ ድርሻ ያለው ሲሆን በአንድ መንፈስና በአንድ ልብ ተሳስረውና ተያይዘው ስራቸውን ይፈጽማሉ፡፡ ይህ የተደራጀ አካል እንደ አንድ ሰው የሚንቀሳቀሰው በዋናነት ሕግና ደንብን በመፍራት ሳይሆን ከላይ እንደተገለጸው የቤተክርስቲያን ራስ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚተላለፈው ሕይወት ሕይወታቸው ስለሆነና ከዚያ ሕይወት ተለይተው መኖር ስለማይፈልጉ ነው፡፡ ይህ ማለት አካሉ የሚንቀሳቀስበት ሕግና ስርዓት የለውም ማለት ግን አይደለም፡፡ በአንጻሩ ጠንካራ ሕግና ስርዓት ያለው አካል ነው፡፡

Scroll to Top