አጀማመር

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 16፡18-19 ላይ ለጴጥሮስ፡-

‹‹…አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሰራለሁ፣ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም፣ የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፣ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፣ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል››

ብሎት ለእርሱም በተሰጠው በዚያች የክርስቶስ ማንነት ምስጢር መገለጥ ላይ ቤተ ክርስቲያኑን ራሱ እንደሚመሰርትና የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እንደሚሰጠው ተናገረ፡፡ በዚህም መሰረት በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ በዝርዝር እንደቀረበው፣ ጴጥሮስ ተነስቶ በተለይም በቁጥር 38 እና 41 ላይ፡-

‹‹ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፣ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ … ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፣ በዚያም ቀን ሦሰት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ››

በማለት የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎችን ምስጢር በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሰበከ፡፡ እነዚህም መክፈቻዎች ‹‹ንስሐ መግባት››፣ ‹‹ለኃጢአት ስርየት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቅ›› እና ‹‹የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ መቀበል›› ናቸው፡፡ ጌታ ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስን በማደል አብሮ መሰከረለት፤ ብቸኛዋ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም በምድር ላይ ተመሰረተች፡፡

የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ጌታ ኢየሱስ በበዓለ ሐምሳ ቀን የመሰረታት የዚያች የእርሱ ቤተክርስቲያን ክፍል ስትሆን በአሁኑም ዘመን ከኢትዮጵያ ጀምሮ በምድር ሁሉ ላይ እየተስፋፋች ትገኛለች፡፡ እምነቷና አስተምህሮዋም ለኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የመጣ አዲስ አይደለም፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምእራፍ 8 ላይ እንደተጻፈው ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ ሰው በወንጌላዊ ፊልጶስ እጅ ከላይ በተጠቀሰው የጥምቀት ስርዓት ተጠምቆ ነበረና፡፡ ለብዙ ዘመናት ተዳፍኖ የኖረው ይህ በአስራ ሁለቱ ሐዋርያት የተሰበከው የመዳን ወንጌል በኢትዮጵያ እንደገና ያቆጠቆጠው በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ጀምሮ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በሕጋዊ ተቋምነት በመንግሥት ተመዝግባ ከ 1961 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠች ትገኛለች፡፡ ዋና ጽ/ቤቷም በአዲስ አበባ ሲሆን በሺሆች የሚቆጠሩ አጥቢያ አብያተክርስቲያናት እና አገልጋዮች አሏት፡፡ አገልግሎቷም በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ በከፈተላት በር ሁሉ ተጠቅማ በመላው ዓለም ላይ የወንጌል ስርጭትና ቅዱሳንን የማነጽ ተግባር እያከናወነች ትገኛለች፡፡

ብዛት

ብዛትን በሚመለከት ቤተክርስቲያኒቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምእመናን ያሏት ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ አሃዝ በየዓመቱ ከ 40 – 50 ሺህ በሚያህል ብዛት እያደገ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የሚገኙት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን በአፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በእስያና በሌሎችም ክፍለ ዓለማት እየጨመሩ በመሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ዓለም አቀፍ አገልግሎቷም በአፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በመካከለኛው ምስራቅና አውስትራሊያን ጨምሮ በመላው ዓለም ላይ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን መሰረታዊ አስተምህሮ በበዓለ ሐምሳ ቀን ከተወለደችው ከአዲስ ኪዳኗ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በበዓለ ሐምሳ ቀን የተሰበከው፡- ‹‹ንስሐ ግቡ፣ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፣ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ›› የሚለውን ያንኑ የመጀመሪያውን የመዳን ወንጌል እየሰበከች ተግባራዊ ታደርጋለች (ሐዋ. 2፡37-38)

Scroll to Top