የወንጌል ስርጭት እንቅስቃሴ በኮንጎ

ከሐምሌ 20-25 /2013 ዓ.ም የአገልጋዮች ስልጠናና ኮንፍረንስ በኮንጎ ኪንሻሳ ተካሄደ፡፡ የአገልጋዮቹ ስልጠና ከሐምሌ 20-23/2013 ለአራት ቀናት የነበረ ሲሆን በስልጠናው ላይ ከ400 በላይ ኮንጎአውያን አገልጋዮች ተሳትፈዋል፡፡ በስልጠና ፕሮግራሙ ላይ የአንድ አምላክ በስጋ መገለጥ እና ቤተክርስቲያን አንዲት የክርስቶስ አካል የመሆኗ ምስጢራት አስመልክቶ ሰፊና ጥልቅ ትምህርት በእግዚአብሔር ጸጋ የተላለፈ ሲሆን የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በሙሉ ታንጸዋል፡፡

ለአራት ቀናት በተካሄደው የስልጠና ፕሮግራም ላይ የእግዚአብሔርን ቃል ያስተማሩት የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ቢሾፕ ደጉ ከበደ እና የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባልና የምስራቅና ደቡብ ሐረርጌ ቅ/ሰበካ ኃላፊ የሆኑት ቢሾፕ አለማሁ ገ/ሚካኤል ናቸው፡፡

በስልጠናው ላይ ከተሳተፉት አገልጋዮች እንደተሰማው ጌታ ኢየሱስ ልባቸውን በቃሉ ነክቶ ከአሁን በኋላ የወንጌል አገልግሎትን እንደ አዲስ እንደሚጀምሩ እስኪሰማቸው ድረስ ታላቅ የእግዚአብሔር ጉብኝት የፈሰሰበት ፕሮግራም ነበር፡፡ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተካሄደው ብዙ ምዕመናን የተሳተፉበት ኮንፍረንስ ከሐምሌ 23-25/2013 ዓ.ም የተደረገ ሲሆን ሐዋርያት የሰበኩት ወንጌል በታላቅ ኃይል ተሰብኮ ልባቸው የተነካ 117 አዳዲስ ነፍሳት ለኃጢአታቸው ስርየት በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠምቀዋል፡፡ በጉባኤው ላይ ከፍተኛ የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ የነበረ ሲሆን ከ200 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ወርዶ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በልሳን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በምስራቅ አፍሪካ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ አንጎላ፣ ደቡብ ሱዳንና ሌሎችም አካባቢዎች የሐዋርያዊት ወንጌል እየተቀጣጠለ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ለዚህም ጌታ ኢየሱስ የሚጠቀምባቸውን አገልጋዮቹንና ሕዝቡን ሁሉ ይባርክ!

Scroll to Top