ቄስ ኤልያስ ሽባባው | የአዲስ አበባ አስኮ ጽዮን አጥቢያ መጋቢ

ስለመጨረሻው ዘመን ወይንም ስለ ጌታ ዳግም መመለስ ለክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ የተላለፉ መልእክቶች ምንድን ናቸው? ክርስቲያኖች ስለመጨረሻው ዘመን ሲነሳ በእምነት እንደሌሉት አህዛብ ለምን ይናወጣሉ፣ ይጨነቃሉ፣ ይረበሻሉ? በሃገራችን ለረጅም ዘመን ሲወራረስ የመጣ የስምንተኛው ሺ ትርክት እና ፍካሬ ተጽዕኖ በሚመስል መልኩ ከጌታችን ኢየሱስ መገለጥ ጋር አብሮ ታላቅ ሽብር ይነዛል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ፍጹም ዓለማዊ እና ፍጥረታዊ በሆኑ ሚዲያዎች እና የልብወለድ ስራዎችን በመከታተል ቅዱሳን አብረው ከዓለም ጋር ሲናወጡ ማየት የተለመደ ሆኗል። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በብዙ ቅዱሳን ወገኖች የተነበበ ባለሁለት መደብል ልቦለድ መጽሐፍ ሃብት ማካበቻ መሆኑን ምስጢሩን ከሚያውቁ ቅርብ ሰዎች ጭምር ማረጋገጫ በመጠየቅ ለማጣራት ጥሯል። በ Y2K እና በ2012 በሚል በተደረጉ ታላቅ ሽብር ብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ ፍርሃት እና አለመረጋጋት ተፈጥሮ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

የእነዚህ እንቅስቃሴዎች እና በተለያየ ዘመን የተነሱ የምጽአት ቀን ናፋቂዎች ባስነሱት ነውጥ ብዙ ትርምስ የንብረት ኪሳራ እና አለመረጋጋት እንዲሁም ትልልቅ ወንጀል ሲፈጸም የታየ ሲሆን ለአዳዲስ የእምነት እንቅስቃሴ እና ኑፋቄ ሁሉ መነሻ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ “ጌታ መምጣት” በተሳሳተ መላምት ለተናወጡት የተሰሎንቄ ሰዎች “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን።” 2ኛ ተሰሎንቄ 2፥1-2 በማለት አጓጉል ውሳኔ ከሚከተላቸው መላምቶች እንዲርቁ አስገንዝቧል።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን በ1914 ዓ.ም የአንዳንድ የእምነት ተቋማት የፈጸሙት ነገር ብዙዎችን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጠሉ እምነትን እንዲቃወሙ እና ሃይማኖት የለሽ እንዲሆኑ እና አዳዲስ ኑፋቄ እንዲፈጥሩ ምክንያት ነበር። በተለይ ቃሉን እና ኃይሉን በካዱ በመናገራቸው ምንም ጸጋን በማያካፍሉ ሰዎች አቅም እና ብርታትን የማያካፍሉ የሽብር ሰብከቶች ምክንያት ዘባችነት (በመዘበት የሚመጡ) የተስፋውን ቃል የሚያቃልሉ የመዝናኛ እና የቢዝነስ ማድመቂያ የመሰሉ ትምህርቶች እየተሰጡ ይገኛሉ:: ቅዱሳን እነዚህን በማንበብ እና በመስማት ምንም አያተርፉም።

“ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ፦ እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ። እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል። እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤ እነርሱ፦ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና። እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው።” ይሁዳ ቁጥር 14-19 እንደሚል ከጥንት ጀምሮ የጌታ መምጣት ከፍርድ ጋር ተያይዞ የሚነገር ድንቅ ትምህርት እንጂ የዘባቾች የፕሮግራም ማጣፈጫ አይደለም። ስለዚህ ስለመጨረሻው ዘመን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት (በቤተክርስቲያን) የተነገረን ነገር በቂ ነው።

በተመሳሳይ የዓመጽ ምሰጢር አሁን እንደሚሰራ ይታወቃል። ይህም ሊመጣ ላለው ክህደት ብዙ ዝግጅት እና መንገድ ጥርጊያ ሊኖር እንደሚችል በቅዱሳኑ ዘንድ የሚታወቅ ሆኖ እያለ አስቀድሞ ሊሆን የሚገባው ነገር ባልተነሳበት በአእምሮ መናወጥ ውስጥ የሚገቡ ክርስቲያኖች በብዙ ሲታወኩ ይታያሉ። ከላይ እንደተመለከትነው ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰሎንቄን ቅዱሳን የጌታን መገለጥ እና ወደ እርሱ ስለመሰብሰባችን በቃል በመንፈስ እና በመልዕክት በማስተማሩ ብዙዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማድረግ አስኪቸገሩ ስራ ለመስራት እስኪያቅታቸው ተሸበሩ። ይህን ለማስተካከል  በሁለተኛው መልዕከቱ እንዲረጋጉ እና እንዳይናወጡ መከራቸው። ዛሬም በግልጽ የሚታይ የአውሬው እና የመንግስቱ እንቅስቃሴዎች በአለማችን በልዩ ልዩ ሁኔታ ይ ስተዋላሉ በዚህ ዘመን እነዚህን ነገሮች ስንመለከት የቅዱሳን ምላሽ ምን መምሰል እንደሚገባው በቅዱስ ቃሉ ላይ በስፋት ተጽፎ ይገኛል።

ለእኛ የጌታ መገለጥ የመምጣቱ የተስፋ ቃል (ቃልኪዳን) የተባረከ ተስፋ ነው። ከሰማይ የሚገለጥ መድኃኒት የምንጠብቅበት ቀን ነው። “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው።” ራዕይ 22፥12-14 እንደሚል ሽልማት፣ ስልጣን እና ዝግጅት፣ ቅዱስ ኑሮ፣ እግዚአብሔርን በመምሰል መመላለስ (ቅድስና) ዋናው ትኩረታችን ነው። ይህ ሁሉ ሲሆን “ቅድስት ቤተክርስቲያን ተለዪ አትደባለቂ!” የሚል መልዕክት እና ጨለማን መቃወም ዋነኛው ትኩረታችን ነው።

በእርሱ ፊት ለመቆም መጽናትን ማሰብ፣ የሰውነታችንን ቤዛነት ልጅነትን መናፈቅ፣ ቤዛን መጠባበቅ፣ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት መጠባበቅ እና ማስቸኮል፣ ዘመኑ አጭር መሆኑን በመረዳት ሁሉ የሚቀልጥ መሆኑን በማሰብ በመጠን መኖር ያስፈልገናል። በመጽሐፍ እንደተጻፈ እምነት እና የፍቅር ጥሩር ለብሰን የመዳን ራስ ቁር አድርገን የምንነቃ እንጂ የምናቀላፋ ሳንሆን በተቀደሰ ሃይማኖታችን ራሳችንን መጠበቅ ያስፈልገናል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን (ቅዱሳንን) ስለመጨረሻው ዘመን የመስበክ፣ የማስተማር እንዲሁም የማንቃት አስፈላጊነት ሲጽፍ “ለእርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቈጠሩ ዘንድ፥ ነው” [2ኛ ተሰ. 1፥5] በሚል ትልቅ ምክንያት በዚህ ርዕስ ይሰብክ እና ያስተምረው እንደነበር ከመልዕክቱ እንረዳለን። በዚህም ምክንያት ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ እንደ እግዚአብሔር ልጆች ስናስብ በእኛ እና በዓለም መካከል የሚኖረው ዕይታ ፍጹም የተለየ ሊሆን ይገባዋል። “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና።” [2ኛ ተሰ. 1፥6-7] እንደሚል ቃሉ ከክርስቲያኖች ማለትም ከዳኑት ቅዱሳን መካከል ማናችንም ቢሆን የጌታ መገለጥ መከራን ይዞብን እንደሚመጣ ማሰብ አይገባንም። ለእኛ ለቅዱሳን የጌታ ቀን ድቅድቅ ጨለማ ቀን ሳይሆን እረፍትን በብድራት (ካሳ) የምንቀበልበት የሚናፈቅ ቀን መሆኑ መታወቅ አለበት።

ዳግም የመምጣቱን ቀን ለጌታ ለራሱ በቅዱሳኑ የሚከብርበት እና የሚገረምበት ቀን ነው። በአንጻሩ ይህ የጌታ መገለጥ የበቀል ወይም የቅጣት የሚሆንባቸው እግዚአብሔርን በማያውቁ እና ለወንጌል በማይታዘዙ ላይ ነው። በዚያ ቀን ከጌታ ፊት ከኃይሉ ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉና። ስለዚህ እኛ በእርሱ ዘንድ ልንከብር እርሱ በእኛ ዘንድ ሊከብር የምንጠባበቀው ቀን ስለሆነ ማራናታ (ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!) ሊያስብለን እንጂ ሊያስፈራራን አይገባም። ዛሬ (ዘወትር) የሚያስፈራ ኑሮ እየኖርን ወደፊት እንዳንፈራ ተመክረናል ወደፊት እንዳንገደል ዛሬ (ዘወትር) ስለ አንተ እንገደላለን እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ዛሬ የምንሞት መስለናል ነገር ግን ሕያዋን ነን።

ከላይ እንደተመለከትነው ከጌታ መምጣት ጋር ተያይዞ እንደ ዕውር እስኪሄዱ ድረስ የሚጨናነቁበት፣ “ጨለማ እና ጭጋግ፣ መፈታት እና መሸበር ፣ መዓት እና የመፍረስ ቀን፣ የምጥ ጣር እና ታላቅ ሽብር፣ ፈጥኖ የሚጨርስ እና የሚበላ እሳት፣ መራራ ለቅሶ እና የእግዚአብሔር ቁጣ፣ በቀል፣ ቅጣት እና የዘላለም ፍርድ ቀን ይሆናል።” የተባለው ለማን መሆኑን አለማወቅ ስለጌታ መምጣት የሚኖረንን ዕይታ ያዛባዋል። በእውነት ይህ ሁሉ አስፈሪ ነገር ውስጥ ማራናታ ወይም ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና ማለት እንዴት ይቻለናል። ማራናታ ለማለት የተባረከውን ተስፋ የምንጠባበቅ ኢየሱስ ሲገለጥ ምንቀበለውን ጸጋ የምንናፍቅ በምድር ስንኖር በስደት እንደምንኖር ታምነን ከሰማይ የሚሆን መኖሪያን የምንናፍቅ ልጆች ልንሆን የምንችለው እርሱ ከሰማይ ሲገለጥ የሚጠብቀንን ክብር በማወቃችን ነው።

ለእኛ ለቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢገለጥ የምናገኘው (የምንቀበለው) ክብር ይናፍቀናል። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን። እንደሚል ቃሉ የጌታ ቀን ደርሶአል ብሎ መናወጥ ትክክል አይደለም። ዛሬ ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች በተበተኑበት ስፍራ ከሚሆኑ የመምጫው ምልክቶች አንጻር ይናወጣሉ ብዙ ሰባኪዎች በጌታ መምጣት ህዝቡን ማናወጥ ማስፈራራትን ይወዳሉ። በእርግጥ ቅዱሳንን የሚያስፈራ እና የሚያስደነግጥ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ሊሆን ይገባዋል። ነገር ግን በአውሬው እና በስሙ ቁጥር በመጨረሻ ዘመን ክስተቶች እና ምልክቶች መገለጥ (መታየትን) የሚያስደነግጠው ኃጢአተኞችን እና ኃጢአትን እተለማመዱ ያሉትን ሊሆን ይገባል። የዚህ ዓለም ስርአት መቀየር እና ራሱን ለአውሬው (ለሃሳዊ መሲህ) ለማዘጋጀት በሚደረገው እንቅስቃሴ ምክንያት ትጋት ጸሎት ጥንቃቄ መንገድን ማጥበቅ የሚሉ ትምህርቶች ከመስጠት ጋር በደስታ ወደ ሽልማቱ የሚቸኩል አሸናፊ ትውልድን ማየት ያስፈልጋል። ስብከታችን ከማሸበር ይልቅ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማንቃት እና በጽድቅ እንዲበረታ ለማሳሳብ ቢሆን ይመረጣል።

Scroll to Top