አንድ አምላክ በብሉይና በአዲስ ኪዳን

እግዚአብሔር አምላክ በብሉይ ኪዳን ራሱን ለሰው ልጆች በተለይም ሕዝቤ ብሎ ሲጠራቸው ለኖረው የእስራኤል ልጆች ያስተዋወቀው ባልተወሳሰበና ግልጽ በሆነ መንገድ አንድ ብቻዬን ነኝ ብሎ ነው። ከአሥርቱ ትዕዛዛትም የመጀመሪያ ሆኖ የተሰጠው “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው÷በታችም በምድር ካለው፡-ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ÷ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ።  አትስገድላቸው÷ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወድዱኝ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና” የሚለው ነው (ዘጸ. 20÷4-6)

ዘዳ. 6÷4-5 “እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ።” ይህ የመጀመሪያ ትእዛዝ በአዲስ ኪዳንም የመጀመሪያ ትእዛዝ ሆኖ እንደሚቀጥል፤ እዚያ ላይ ምንም ለውጥ እንደሌለ ጌታ ኢየሱስ ደግሞ ተናግሮታል (ማር. 12÷29) ።

ዘዳ. 32÷39 “አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደሆንሁ÷ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤እኔ እገድላለሁ÷አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ÷እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም።“

በብሉይ ኪዳን ዘመን እስራኤልና አሕዛብ በሚል ለሁለት የተከፈለ ሕዝብ የምናይበት ዋናው ምክንያት እስራኤላውያን የአንድ አምላክ አማኞች በመሆናቸውና አሕዛብ ደግሞ (ከእስራኤል ውጪ ያለው ዓለም በሙሉ) እግዚአብሔርን የማያውቁ ወይም በብዙ አማልክት እምነት መያዛቸው ነው። ብዙ ጊዜ እስራኤላውያን አንዱን አምላካቸውን ትተው እንደ አሕዛብ ወደ ብዙ አማልክት አምልኮ በገቡ ጊዜ ሁሉ በእግዚአብሔር ሲቀጡ፣ በጠላቶቻቸው ሲሸነፉ፣ ባሪያ ሆነው ሲማረኩ እንመለከታለን (ዘዳ. 32÷16-25፣ 2ዜና. 7÷22፣ ኤር. 10÷1-3፣11፣ 16÷11)

በብሉይ ኪዳን ውስጥ በታቀፉ የሕግ፣ የመዝሙራትና የነቢያት መጻሕፍት ውስጥ እየተደጋገመ ሲታወጅ የኖረው፤ የእግዚአብሔር አንድ ብቻውን መሆን እንጂ ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ጥምር አማልክት እንዳሉ ቅንጣት ያህል እንኳን የሚያጠራጥር ቃል አይገኝም።

በፈጣሪነት ሁሉን ለብቻው መፍጠሩንና በአጠገቡ ሌላ ማንም አለመኖሩን ተናግሮአል።

ኢሳ. 44÷24-25 “ከማኅፀን የሠራህ÷የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡-ሁሉን የፈጠርሁ÷ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?” (ኢሳ. 40÷12-14፣ ኢሳ. 45÷6-7፣ ኤር. 10÷12፣ ዮናስ 1÷9፣ ሚል. 2÷10)

ከእርሱ ጋር፣ ከእርሱ በፊትም ሆነ በኋላ ሌላ አምላክ እንደሌለ፣ እንደማይሆንም አሳውቆአል።

ኢሳ. 41÷4-5 “እኔ እግዚአብሔር ፊተኛው÷በኋለኞችም ዘንድ የምኖር÷እኔ ነኝ።” 

ኢሳ. 43÷10-12 “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ÷እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም። እኔ÷እኔ እግዚአብሔር ነኝ÷ከእኔ ሌላ የሚያድን የለም።” (መዝ. 81÷8-9፣ ኢሳ. 44÷6-8)

በመዳንም በኩል ከእርሱ ሌላ ለአዳኝነት የተሰየመ፣ የሚጠበቅ አምላክ እንደሌለ ተናግሮአል።

ኢሳ. 64÷4 “ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም ዓይንም አላየችም።” (መዝ. 3÷8፣ ኢሳ. 45÷21-23፣ ኢሳ. 63÷1፣ ሆሴ. 13÷4)

በሕፃን (በልጅ) መልክ የሚገለጠውም ራሱ መሆኑን ተናግሮአል።

ኢሳ. 9÷6 “ሕፃን ተወልዶልናልና÷ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር÷ ኃያል አምላክ÷የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።”

በብሉይ ኪዳን ይኽ አንድ አምላክ በመንፈስነትና በቃል እንጂ በሚታይ አካል አይታወቅም። ስለዚህም እግዚአብሔር ይህንን ይመስላል ብሎ ሥዕልና ቅርጽ መሥራት ፈጽሞ ክልክል ነው፤ ጣዖት እንደማምለክም ይቆጠራል። በየዕለቱ ወደ ኤደን ገነት እየመጣ ሲያነጋግረው ለነበረው አዳም እንኳን ሲገለጥለት የነበረው በአካል ሳይሆን በቃል (በድምጹ) ብቻ ነበር (ዘፍ. 3÷8)። ሙሴንም “ሰው አይቶኝ አይድንም ፊቴን ማየት አይቻልህም” ብሎታል (ዘጸ. 33÷20-21)“እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን።” (1ኛ ጢሞ. 6÷16)

ዘዳ. 4÷12-13፣ 15-19 “እግዚአብሔርም በእሳት ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ የቃልን ድምፅ ሰማችሁ መልክ ግን አላያችሁም፤ ድምፅን ብቻ ሰማችሁ።… እግዚአብሔር በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ መልክ ከቶ አላያችሁምና እጅግ ተጠንቀቁ፤ እንዳትረክሱ÷የተቀረጸውን ምሰል የማናቸውንም ነገር ምሳሌ÷በሰማይም በታች የሚበርረውን የወፍን ሁሉ ምሳሌ… እንዳታደርጉ።”

ታዲያ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በመልኩ ፈጠረው (ዘፍ. 1÷27) የሚለው ቃል ምንን ያመለክታል? ብለን ብንጠይቅ፡- እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከምድር አፈር ሲያበጀው በአዲስ ኪዳን ሊገለጥበት ያሰበውን የራሱን ሰውነት (የክርስቶስን መልክ) አምሳልና የአካል ቅርጽ በመስጠቱ አዳም በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ ይባላል። በወቅቱ ግን እግዚአብሔር አዳም የተፈጠረበት መልክ ገና አልነበረውም (ሮሜ. 5÷14፣ ኤፌ. 1÷4-11፣ ዮሐ. 1÷3)

ይህንን የማይነቃነቅ የአምላክ ማንነት ይዘን ነው ወደ አዲስ ኪዳን የምንሸጋገረው። አዲስ ኪዳን ያንኑ የብሉይ ኪዳኑን አንድ አምላክ እንጂ ሌላ አምላክ አያስተዋውቀንም።

የምስራቹም አዋጅ (ወንጌሉ) እግዚአብሔር አማኑኤል ሆነ፤ (እግዚአብሔር ከእኛ ጋር) የሚል ነው (ማቴ. 1÷23)፣ መላእክት መድኃኒት (አዳኝ) ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል ነው ያሉት (ሉቃ. 2÷10-11)፣ ዮሐንስም “በዓለም ነበረ÷ ዓለሙም በእርሱ ሆነ÷ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ÷ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም” ብሎ ነው የጻፈው፣ (ዮሐ. 1÷10-12) ራሱ ጌታ ኢየሱስም “እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና” ብሎ ፍርጥ አድርጎ ተናግሮአል (ዮሐ. 8÷24-25)

ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ” ብሎ ነው የጻፈው። (1ኛጢሞ. 3÷16) ብሉይ ኪዳን ላይ አንድ አምላክን እያየን መጥተን አዲስ ኪዳን ላይ ስንደርስ ማንነው የተገለጠው? በማለት ተደነጋግረን አዲስ አምላክ ወይም ሁለተኛ አምላክ ለመፍጠር መሞከር የለብንም። አንዱ አምላክ በሥጋ ተገልጦ ሰውን ለማዳን ከሄደባቸው አሠራሮች ጋር ተያይዘው የተጠቀሱት አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ የተባሉ የራሱ የእግዚአብሔር የመገለጫ ማዕረጎቹ የማይነቃነቀውን የእግዚአብሔር አንድ መሆን የሚያጸኑ እንጂ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ አይደሉም። ብዙዎች ትክክለኛውን የእምነት አቅጣጫ የለቀቁት እዚህ ጋ ነው።

ዮሐንስ 1÷10-12 እንደተጻፈው ዓለሙ (ከእምነት ውጪ የሆነው) ባለማወቅ፣ ወገኖቹ የተባሉ (በእምነት ውስጥ ያሉት) ባለመቀበል ወይም እርሱ አይደለም በማለት ብዙ መሰነካከል ተፈጠረ። ለማዳን የመጣ አንድ አምላክ የማሰናከያ ዓለት ሆነ። በኢሳይያስ 8÷13-15 “ነገር ግን የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት፤ የሚያስፈራችሁና የሚያስደነግጣችሁም እርሱ ይሁን። እርሱም ለመቅደስ ይሆናል፤ ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች ለዕንቅፋት ድንጋይና ለማሰናከያ ዓለት÷በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሸክላ ይሆናል። ብዙዎችም በእርሱ ይሰናከላሉ÷ ይወድቁማል÷ ይሰበሩማል÷ይጠመዱማል÷ይያዙማል” ተብሎ የተጻፈው ትንቢት ተፈጸመ (1ኛ ጴጥ. 2÷6-8)።

“እግዚአብሔር አምላክ በሥጋ ተገለጠ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይመልስልን፡-

ቀደም ሲል ለመግለጥ እንደተሞከረው በፍጥረት ሁሉ አባትነት የሚታወቀው አንድ አምላክ (ሚል. 2÷10) መንፈስ ስለሆነና ስለማይሞትም ለሰው ልጆች ቤዛ (ምትክ) መሆን እንዲችል የሚገለጥበትንና የማዳን ሥራውን የሚሠራበትን ከራሱ ቃል የተገኘ የሥጋ ሰውነት አዘጋጀ። ይህም በዕብራውያን 10÷4-7 “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና። ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ፡- መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ።” ተብሎ የተጻፈው ዳዊት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው።

ከእኔ በቀር የሚያድን የለም ሲል የኖረው እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ከራሱ በቀር ሌላ የሚላክ አምላክ አላስፈለገውም።

እግዚአብሔር የፈለገው፡-

ዮሐንስ 2÷19-21፣ በቈላስይስ 2÷9-10 እንደተጻፈው የመለኮት ሙላት ሊገለጥበት የሚችል የእግዚአብሔር የራሱ ዘላለማዊ መቅደስ ነው።

ዕብራውያን 7÷26-28 እንደተጻፈው ከኃጢአተኞች የተለየ ቅዱስና ያለነውር የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ነው።

1ኛ ቆሮንቶስ 15÷45-48 እንደተጻፈው ከወደቀው አዳም ጋር ምንም የሥጋና የደም ንክኪ የሌለው ሰማያዊ ሰው ነው።

የዓለምን ኃጢአትና ደዌ ሁሉ መሸከም የሚችል በእግዚአብሔር የተዘጋጀ የእግዚአብሔር በግ ተብሎ የሚጠራ መስዋዕት ነው (ኢሳ. 53÷4-9፣ ዮሐ. 1÷29)።

እግዚአብሔር አጣሁ ያለውን (ኢሳ. 59÷16-17) በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሰው(የሥጋ ሰውነት) በማርያም ማኅፀን በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ከራሱ ቃል አዘጋጅቶ በዚህ የሥጋ ሰውነት የመለኮት ሙላት ተገለጠ። (ቈላ. 2÷9) በሥጋው በኩል የእግዚአብሔር ልጅ (ወልድ) ፣ክርስቶስ፣ ኋለኛው አዳም፣ የእግዚአብሔር በግ እየተባለ ተጠራ። እግዚአብሔር አንድ መሆኑ ሳይቀየር ወይም ሳይባዛ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሰው የሆነ ክርስቶስ ገባ (1ኛጢሞ. 2÷5-6፣ 1ኛ ቆሮ. 8÷5-6)። ይህም ክርስቶስ ማለት አንዱ አምላክ የተገለጠበት የሥጋ ሰውነት ሲሆን መካከለኛ የተባለበትም ምክንያት በሚታየው ክርስቶስ በኩል በውስጡ የሚኖረውን የማይታየውን መለኮት (አብ) ማየትና መቅረብ ስለተቻለ ነው (ዮሐ. 14÷6-10)።

ስለዚህ በ2ኛ ቆሮንቶስ 5÷19 እንደተጻፈው እግዚአብሔር በክርስቶስ ውስጥ ሆኖ (God was in Christ) ዓለሙን ከራሱ ጋር አስታረቀ። ቈላስይስ 1÷22 “በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጣላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ” ይላል። ሮሜ. 5÷10 ላይ “ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ታረቅን” ይላል። በክርስቶስ፣ በልጁ፣ በሥጋው ሰውነት ማለት አንድ ነው። ልጁ የአብ የገዛ ሰውነቱ ወይም መልኩ ስለሆነ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” አለ (ዮሐ. 12÷44-46፣ 14÷6-10)። በመስቀል ላይ የፈሰሰው ደም ከአብ ከራሱ የሥጋ ሰውነት የፈሰሰ ደም ስለሆነ የእግዚአብሔር ደም ተባለ (ሐ.ሥራ. 20÷28)።

በብሉይ ኪዳን ብቻዬን ነኝ እያለ ራሱን ያስተዋወቀው አንድ አምላክ “እኔ እግዚአብሔር÷ፊተኛው በኋለኞችም ዘንድ የምኖር እኔ ነኝ” (ኢሳ. 41÷4-5) ባለው መሠረት በአዲስ ኪዳን በሥጋ ተገልጦ ኢየሱስ በሚለው ከስሞች ሁሉ በላይ በሆነ የማዳን ስም እየተጠራ አሁንም እስከዘላለም ብቻዬን ነኝ እያለ ያውጃል፣ ይታወጅለትማል (ሐ፡ሥራ. 4÷12፣ ፊል. 2÷9-11)።

“ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ ስለዚህ ግን÷የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ዕግሥቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ÷ምሕረትን አገኘሁ። ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን አሜን።” (1ኛጢሞ. 1÷15-17፣ ይሁዳ 2-4)።

በመጨረሻም በምድር ላይ ሊነግሥ ሲመጣ እግሮቹም በደብረዘይት ተራራ ላይ ሲቆሙ፤ እግዚአብሔር አንድ ስሙም አንድ መሆኑ ለማንም ግልጽ ይሆናል (ዘካ. 14÷9-10)።

“አትፍራ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፡- ሞቼም ነበርሁ እነሆም÷ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ÷የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።” (ራዕይ 1÷17-18) ።

Scroll to Top