የሐዋርያት ሃይማኖት

የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን የምታምነውና በድፍረት የምትሰብከው 12ቱ የክርስቶስ ሐዋርያት ያመኑትና የሰበኩትን ሲሆን የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ያተኩራል፤

  • ቃል ስጋ ሆኖ በስጋ የተገለጠው ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የመሆኑ እውነት (1ኛ ጢሞ. 3፡16፤ ዮሐ. 1፡14፤ 1ኛ ዮሐ. 5፡20)
  • በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በደሙ ውስጥ ያለውን የማዳን ኃይል (ሐዋ. 4፡12፤ 20፡28፤ 22፡16፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡18-19)
  •  ከሞተ ስራ ንስሃ መግባት (ዕብ. 6፡1)
  • የሰው ልጆች ኃጢአት የሚሰረየው በኢየሱስ ስም ሲጠመቁ ብቻ እንደሆነ (ሉቃስ 24፡47፤ ሐዋ. 2፡37-38)
  • ምልክቱ በአዲስ ቋንቋ (በልሳን) መናገር በሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት መሞላት እንደሚያስፈልግ (ሐዋ. 2፡1-4፤ 10፡44-46)፤ እና
  • ጌታ ኢየሱስ ለቤተክርስቲያኑ ዳግመኛ እንደሚመጣላት እየተጠባበቁ በቅድስናና በጽድቅ እያገለገሉ መኖር (ዕብ. 12፡14፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡51-52፤ 1ኛ ተሰ. 4፡13-18፤ ፊልጵ. 3፡20)

የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ‹‹የጥንቱን ሃይማኖት ሰጠኝ›› ከሚል ዝማሬ ጋር የቀደሙትን ሐዋርያት የወንጌል መልእክት አንግባ በዚህ በመጨረሻው ዘመን ወደ መኖር የመጣችበትን ሁኔታ መለስ ብለን ስንቃኝ ሁኔታው በመጀመሪያ ከተለወጡትና ቀደምት የእምነት አባትና ሐዋርያ ከሆኑት ከቢሾፕ ተ/ማርያም ገዛኸኝ ጋር በቅርበት የተያያዘ ሆኖ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ1950ዎቹ መግቢያ አካባቢ ተ/ማርያም ሰዎች የሚድኑበትን እውነት ለማወቅ በከፍተኛ ረሃብና ጥያቄ ውስጥ ሆኖ በወቅቱ በነበረው መረዳት መጠን እግዚአብሔርን ሲማጠን ከእግዚአብሔር የመጣለት ሰማያዊ መልስ ‹‹ጴጥሮስ አልዳነምን? ጳውሎስ አልዳነምን? ሐዋርያቱስ ሁሉ አልዳኑምን? እነርሱን ያዳነ መንገድ አንተንም ያድንሃል›› የሚል ነበር፡፡ ከተለወጠም በኋላ የእውነትን ወንጌል በታላቅ ራዕይ፣ በመንፈስ እየተቀጣጠለ እና በከፍተኛ መስዋዕትነት በመላ ሃገሪቱ ላይ የሰበከ ሲሆን በእርሱና ከእርሱም በኋላ ወደ አገልግሎት በተቀላቀሉ ሌሎች አገልጋዮች አገልግሎት አማካይነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነፍሳት ወደ መዳን መጥተዋል፡፡

Scroll to Top