በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 17 እና 18 ላይ ‹‹ታላቂቱ ባቢሎን››፣ ‹‹የጋለሞታዎችና የምድር ርኩሰት እናት›› ተብላ የተጠራችና በግምባርዋ ላይ ምስጢር የሆነ ስም የተጻፈባት አንዲት ‘ሴት’ ተጠቅሳለች፡፡ በመንፈሳዊ እይታ ይህች ምስጢራዊት ‘ሴት’ የረቀቀውንና እርስ በርሱ የተሳሰረውን የንግድ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካና ተዛማጅ የሆኑ የማኅበራዊ ውስብስብ የዓለም ስርዓትን የምትወክል ስትሆን የእግዚአብሔርን መንግሥት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ትቃወማለች፡፡ ‹‹ባቢሎን›› ምኞቷን በሰው ልጆች ውስጥ የምታሰርጽባቸው ልዩ ልዩ መንገዶች ቢኖሩም ኢንተርኔት ወይም በይነ-መረብ አንዱና ምናልባትም ዋናው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ቢሾፕ ፖል ቶማስ ‘Beware The Curiosity of The King of Babylon’ በሚል ርዕስ ያቀረቡትን አጭር ፅሁፍ ‹‹የባቢሎን ንጉሥ ጉጉት››  በሚል ተተርጉሞ እንደሚከተለው ቀርቦአል፡፡ ጸሃፊው ለዚህ ትውልድ በተለይም ለወጣቶች ካላቸው ከፍተኛ የመዳን ፍቅርና ሸክም ተነስተው በሐዋርያት እምነት ውስጥ ያሉ ወጣቶች በሙሉ የኢንተርኔት አጠቃቀማቸውን ማስተዋል ያለበት አድርገው ራሳቸውን ከባቢሎን ንጉሥ ጉጉት እንዲጠብቁ አበክረው ይመክራሉ፡፡ ጌታ ኢየሱስ ጸሃፊውን አብዝቶ ይባርክ!


 

በይነ መረብ (Internet) እና ክርስቲያን (ቢሾፕ ፖል ቶማስ)

“እርሱም፦በቤትህ ያዩት ምንድር ነው? አለው፤ ሕዝቅያስም፦በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤በቤተ መዛግብቴ ካለው ያላሳየኋቸው የለም አለው።” 2ኛነገሥት 20፥15

ሕዝቅያስ በታመመ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ለእርሱ ያዘነ ጠያቂ በሚመስል አቀራረብ የይሁዳን መንግስት ጥንካሬና በንጉሡ ቤተመዛግብት የነበሩትን የሃገሪቱን ምስጢሮች በጠቅላላ ለመሰለል መልእክተኞቹን ወደ ኢየሩሳሌም ልኮ ነበር። ንጉሥ ሕዝቅያስም የባቢሎንን ንጉሥ ድብቅ አላማ ሳይረዳ የእግዚአብሔር ንብረት የሆነውን ነገር ሁሉ ግምጃ ቤቱን፥ ብሩንና ወርቁንም፥ ቅመሙንና የከበረውንም ዘይት፥ መሣሪያም ያለበትን ቤት በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው።

ለመሆኑ ባቢሎን ማን ናት? ይህ ጽሁፍ የባቢሎንን ወይም የንጉሥዋን ማንነት ለመተንተን ያለመ ስላልሆነ ወደ ዝርዝር ባይገባም በመንፈሳዊ እይታ ሲታይ ግን የባቢሎን ንጉሥ ሰይጣን ከጀርባ ሆኖ የሚዘውረው የአሁኑ ዓለም ምሳሌ መሆኑን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ባቢሎን ከስድሳ ስድስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የመጀመሪያ በሆነው በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እና በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በዮሐንስ ራዕይ ላይም በልዩ ሁኔታ ጎልታ ተጠቅሳለች፡፡ ይህ ትልቅ ትርጉም አለው።

በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ላይ የኖህ ልጆች ተሰባስበው ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ሰርተው ስማቸውን ለማስጠራት ፈለጉ። እግዚአብሔርም ዓላማቸውን ስላልወደደው አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማ ቋንቋንቸውን ደባልቆ በምድር ላይ በተናቸው፤ የቦታውም ስም ባቢሎን ተባለ፤ ትርጓሜውም ግራ መጋባት (Confusion) ማለት ነው።

“ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና፤ ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በትኖአቸዋል።” ዘፍጥረት 11፥9

ይህ ቃል ባቢሎን ገና ከጅምሩ ሰዎች የገዛ ስማቸውን ለማስጠራት ሲሉ ያቋቋሙት ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር በተቃርኖ የቆመ ሥርዓት መሆኑን ያሳያል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ክፍል በሆነው በዮሐንስ ራዕይ ላይም ‹‹ባቢሎን›› በልዩ ሁኔታ ተጠቅሳለች፡፡

“ሁለተኛ መልአክ፦አሕዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቍጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች እያለ ተከተለው።” ራእይ 14፥8

በዚህ መሰረት ባቢሎን አንዲት ታላቅ የሆነች፣ የዓለምን ሕዝብ ያበላሸች፣ በመጨረሻም እግዚአብሔር መልዓኩን ልኮ ‹‹ወደቀች››፣ ‹‹ወደቀች›› እያለ ፍርዱን የሚያውጅባት እንደሆነች ይታያል፡፡ ለመሆኑ ይህች ባቢሎን ማን ናት? ይህች ጌታ ኢየሱስ ‹‹ባቢሎን›› ብሎ የሚጠራት ‘ሴት’ በሃሳዊ መሲሁ ቁጥጥር ስር ውላ በእርሱ ተጽእኖ የምትመራዋን አለም ስርአት የምታራምድ ናት።

የዮሐንስ ራእይን በአግባቡ ያጠና ሰው በዚህ ዘመን ያለውን የኦንላይን ግብይትና በኢንተርኔት የሚከናወኑትን ሌሎች ተግባራት በሚገባ የሚያውቅ ከሆነ የምድር ርኩሰት እናት›› የተባለችውን ምስጢረኛዋን ባቢሎንን በዚህ ዘመናዊ የመገናኛ አውታር በኩል በግልጥ ሊያያት ይችላል፡፡ በዮሐንስ ራዕይ18፥10-13 ላይ በባቢሎን ውስጥ የተለያዩ ሸቀጦችና ምርቶች ግብይት እንደሚካሄድ በግልጽ ተቀምጦአል። ከሚሸጡትና ከሚገዙት ሸቀጦች ውስጥም የሚከተሉት ይገኙበታል፦

“ጭነትም፣ ወርቅና ብር፣ የከበረም ድንጋይ፣ ዕንቁም፥ ቀጭንም የተልባ እግር፣ ቀይ ሐርም፣ ሐምራዊም ልብስ፣ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም፣ ቅመምም፣ የሚቃጠልም ሽቱ፣ ቅባትም፣ ዕጣንም፣ የወይን ጠጅም፣ ዘይትም፣ የተሰለቀ ዱቄትም፣ ስንዴም፣ ከብትም፣ በግም፣ ፈረስም፣ ሰረገላም፣ ባሪያዎችም፣ የሰዎችም ነፍሳት ነው።” ራእይ 18፥12-13

በአሁን ዘመን ያለውን የኦንላይን ግብይትና እጅግ የረቀቀ የመረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂ ቆም ብለን ብናጤን ይህ ሲስተም ባቢሎንን ሊወክል እንደሚችል ማስተዋል እንችላለን፡፡ ዛሬ ብርና ወርቅ፣ ቅመምና ማንኛውም ቁሳቁሶች፣ የሰዎች ነፍስ ሳይቀር (ወሲብ፣ ፖርኖግራፊ ወዘተ) በኢንተርኔት ገበያ ላይ እንደፈለጉ መሸመትን ዓለም ተያይዞታል። ይህ ሁኔታ ሲታይ ከንግድና ከመረጃ ልውውጥ ጋር ተያይዞ አለም በኢንተርኔት እያገኘች ያለውን ጥቅም በገንዘብ ለመተመን ያስቸግራል፣ እጅግ ከፍተኛ ነው። አንድ ቀን ጌታ ኢየሱስ ድንገት መጥቶ ኢንተርኔትን ጥፍት ቢያደርገው ምን ሊሆን እንደሚችል ገምቱ! የምድር ባለጠጎችና ነጋዴዎች ስለ ንብረታቸው በታላቅ ድምጽ ዋይ ዋይ ማለታቸው አይቀርም!

የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ታዲያ ክርስቲያን የሆንን ሁሉ ኢንተርኔትን በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን ስንጠቀም ነገሩን መጽሐፍ ቅዱስ በሚያይበት ዐይን እያየን መሆን እንዳለበት ለማሳሰብ ነው። ከመግቢያው ላይ እንደተገለጸው ‹‹ባቢሎን›› ማለት ‹‹ግራ መጋባት›› ማለት ሲሆን የኢንተርኔት በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የምድር መንግሥታትን እጅግ የመጥቀማቸውን ያህል እንዲሁ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ፖለቲካዊና በአጠቃላይ የሰውን ልጅ ኑሮ እያቃወሰ ያለም ጉዳይ ሆኖአል፡፡ እግዚአብሔር መቼም ቢሆን ሕዝቡ ሕይወቱን ውጥንቅጡ በወጣ፣ በተምታታበትና ግራ በተጋባ የአኗኗር ስርአት እንዲመራ አይፈልግም።

ንጉሥ ሕዝቅያስ የባቢሎንን ንጉሥ ስውር አጀንዳ ባለመገንዘቡ መልእክተኞቹን ወደ ቤተ መንግስቱ አስገብቶ ሁሉን ነገር አስጎበኛቸው። ዛሬም ልክ እንደ ንጉሥ ሕዝቅያስ የእግዚአብሔር ልጆች በንዝህላልነት የግል ምስጢራቸውን በኢንተርኔት አማካይነት ለባቢሎን ንጉሥ እየገለጡለት ይገኛሉ። ባቢሎን እኛ ራሳችንን ገልጠን ካሳየናት ከእኛ ፍላጎት፣ ባህርይ፣ ማንነትና የመሳሰሉት መረጃዎች ተነስታ የራሷን ልዩ ልዩ ሸቀጦች ትዘረግፍብናለች፡፡ የእርሷ ሸቀጦች ደግሞ ስጋ፣ ነፍስና መንፈሳችንን ሊያረክሱ የሚችሉ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስ ቤተ መንግስቱና የኢየሩሳሌም ከተማ የእግዚአብሔር ንብረት መሆናቸውን፤ እስራኤልም እግዚአብሔር ከምድር ህዝብ ሁሉ ለራሱ የለየው ሕዝብና መንግሥት መሆኑ ላይ እንደተዘናጋ ዛሬም እኛ ለእግዚአብሔር የተለየን ቅዱሳን መሆናችንን መዘንጋት የለብንም፡፡

“ነገር ግን ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ የምትገቡባት ምድር ኮረብታና ሸለቆ ያለባት አገር ናት፤ በሰማይ ዝናብ ውኃ ትረካለች። አምላክህ እግዚአብሔር የሚጐበኛት አገር ናት፤ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዓይን ሁልጊዜ በእርስዋ ላይ ነው።” ዘዳግም 11፥11-12

ሕዝቅያስ በታመመ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ለእርሱ ያዘነ መስሎ ደብዳቤና እጅ መንሻ አስይዞ መልእክተኞቹን ወደ እርሱ ሲልክ ንጉሥ ሕዝቅያስ በዚህ ጉዳይ ላይ እግዚአብሔርንም ሆነ ነቢዩ ኢሳይያስን ሳያማክር ቤቱን ለጠላቱ ያለምንም ማመንታት ወለል አድርጎ ከፍቶ አሳየው። በኋላም ባቢሎን ይሁዳን ማርኮ ሲወስድ ቀድሞ ያየው ነገር ሁሉ ለብዝበዛው እንዳመቻቸለት አያጠራጥርም፡፡ ዛሬም ከጌታ ኢየሱስ የተቀበልነው መልካም ነገራችን በባቢሎን ንጉሥ እንዳይበዘበዝና እኛም ውለን አድረን ምርኮኞች እንዳንሆን ራሳችንን መጠበቅ ያስፈልገናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የቤተክርስቲያናችን ወጣቶች ኢንተርኔት ውስጥ ገብተው ስሜትና አሳባቸውን፣ ያላቸውን ፍላጎትና እቅዳቸውን … ወዘተ ከስክሪኑ ጀርባ ቁጭ ብሎ ለሚያጠናቸው ማንነቱን ለማያውቁት አንድ አካል በዘፈቀደ ከመግለጻቸው በፊት ጥቅምና ጉዳቱን አስመልክቶ እረኞቻቸውን (መንፈሳዊ መሪዎቻቸውን) እና ታላላቆቻቸውን ቢያማክሩ ራሳቸውን ያድናሉ!

በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ‹‹የባቢሎን ንጉሥ›› እግዚአብሔርን የማያውቀውና እርሱን መፍራት የሌለበትን ዙሪያችንን ከብቦ ያለው የአሁኑ አለም ምሳሌ ነው። የባቢሎን ንጉሥ ክፋትና ተንኮል ያኔ ለሕዝቅያስ እንዳልታየው ሁሉ ዛሬም ለእኛ ላይታየን ይችላል፡፡ ክፉ የሆነው የአሁኑ ዓለም (ገላ. 1፡4) ኢንተርኔትን ተጠቅሞ ነገሮችን ቀላልና ምቹ አድርጎ በማቅረብ በተቻለው አቅም ከኛ የሚፈለገውን መረጃ እንደሚሰበስብ መረዳት ያስፈልጋል። እኛ የህያው እግዚአብሔር ቤተመቅደስ ነንና የኢንተርኔት መስኮትን ከመክፈታችን እና የአየር ላይ ባህር ውስጥ ገብተን ለመቅዘፍ ገና ጣታችንን ከማንቀሳቀሳችን በፊት ምን ውስጥ ልንገባና ምን ልናስተላልፍም እንዳለን ማስተዋልና መመርመር፣ ራሳችንንም ማጠር (Circumspect) አለብን።

“የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።” 1ኛ ቆሮንቶስ 3፥16-17

ይህ ጉዳይ እንደ እኛ ስለክርስትና ሕይወት ወይም ስለመዳን የሚጨነቁትን ብቻ ሳይሆን በዓለም የሚኖሩ ለነገሩ ቅርበት ያላቸውን ምሁራን ሳይቀር የሚያሳስብ ከሆነ ውሎ አድሮአል፡፡ በቨርጂኒያ ዩኒቨርስቲ የሚዲያና ሕግ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ሲቫ ቬይድያናታን እ.ኤ.አ በ2011 በታተመውና The Googlization of Everything በተሰኘው መጽሐፋቸው የምርጫና ራስን የመግለጽ ነጻነትን የሚያቀነቅኑትን፣ ኢንተርኔትንም ሳንጨነቅ በነጻነት በመጠቀም ‘ራሳችንን እንድንሆን’፣ የሆንነውን፣ ያለንንና የግል ፍላጎታችንን ሁሉ ምንም ምስጢር ሳናደርግ በግልጥ እንድናሳይ የሚያደርጉንን ለዘብተኛ የሆኑ መንግስታትን አስጠንቅቀዋል። እንደነዚህ ያሉት መንግስታት አስጨናቂ ከሆኑት የራሺያው KGB እና ከቀድሞው Stasi ከሚባለው የምስራቅ ጀርመን የስለላ ድርጅቶች ስህተት ትምህርት እንደወሰዱ ጸሐፊው ጠቁመዋል።

የቀድሞው የምስራቅ ጀርመን የስለላ ድርጅት Stasi መሪ የነበረው Erich Honecker በቅድመ-ኢንተርኔት ዘመን በነበረው በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሰዎች አድራሻቸውን፣ ፎቶግራፎቻቸውን፣ ዝንባሌዎቻቸውን፣ የየቀን ውሎዎቻቸውንና ልማዶቻቸውን በፈቃደኝነት የሚያጋሩበት አንድ ስርአት ቢኖር ይመኝ ነበር። ይኸው ዛሬ የዚህ ሰው ምኞት በGoogle, Facebook, Instagram እና ሌሎች ዲጂታል መድረኮች መፈጠር እውን ሆኗል። “በምን አይነት መንገድ አየታየን (እየተሰለልን) እንዳለን፣ መረጃዎቻችን እየታዩና ጥቅም ላይ እንደዋሉ በሙላት ባይገባንም ይህ ግን አየተከናወነ መሆኑን እናውቃለን። እኛም በሌሎች ሰዎች እንዲህ በትኩረት እየተመረመረ ያለውን ባህሪያችንን አንቆጣጠርም፣ ራሳችንን ማሳየቱንም ቀጥለናል፣ ግድም የሰጠን አንመስልም።” (Vaidthyanathan, 2011, p. 112)። ከኢንተርኔት ላይ ብዙ መረጃዎችና ልዩ ልዩ የኮምፒውተር መተግበሪያዎች ያለ ምንም ክፍያ በነጻ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ምድር ላይ ሁሉ ነገር ገንዘብ የሚከፈልበት ሆኖ ሳለ እነዚህ ሁሉ በነጻ የሚገኙት ለምን ይመስላችኋል? አላማው በምንደዋወልበት፣ የአጭር የጽሑፍ መልእክት በምንለዋወጥበት፣ ፎቶግራፎችን በምንለጥፍበትና በምንጭንበት ጊዜ ስለ እኛ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ነው።

Luke Harding የተባለ ጋዜጠኛም እ.ኤ.አ. በ 2013 በታተመውና The Snowden Files በተሰኘው እውቅ መጽሐፉ Edward Snowden ለሚባለው የቀድሞው የስለላ መኮንን ቃለ መጠይቅ አድርጎለት የሚከተለውን አስፍሮአል፡-

የሚያየው ነገር ሁሉ አጥብቆ እንደሚያስጨንቀው አልሸሸገም፡፡ “ምንም ስህተት ባይኖርብህም እንቅስቃሴህ በጠቅላላ ክትትል እየተደረገበት ይመዘገባል›› በማለት The Guardian ለተባለው ታዋቂ ጋዜጣ ምላሽ ሰጥቶአል፡፡ “የምዝገባ ስርዐቱና መረጃዎቹ የሚቀመጡባቸው ቋቶች በየዓመቱ የሚያድጉበት መጠን ከልኬት በላይ ነው፡፡ ስህተትህን ብቻ ሳይሆን የምትሰራቸውን ነገሮች ሁሉ መዝግበው ለመያዝ አቅምና ብቃት ያላቸው ናቸው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ አንድ የተሳሳተ የስልክ ጥሪ ቢደርስህ በዚያ መነሻነት ብቻ አጠራጣሪ ሰው ተደርገህ ተቆጥረህ በአንድ ግለሰብ የክትትል መረብ ውስጥ ትገባለህ፡፡ አንድ የተሳሳተ የስልክ ጥሪን ምክንያት በማድረግ ወደኋላ ሄደው በሕይወትህ መቼ ምን አይነት ውሳኔ እንደወሰንክ፣ ከማን ጋር ምን እንደተነጋገርክ ያዘጋጁትን የኮምፒውተር ስርዓት ተጠቅመው በማጥናት ይመዘግባሉ፡፡” (Harding, 2013, p.149)።

በዓለም ያሉ የእውቀት ሰዎች ሳይቀር የሰዎች የግል ሕይወት አላግባብ መገለጡ እንዲህ እንደሚያስጨንቃቸው ስናይ ‹‹እኛስ?›› ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡ ከላይ በአጭሩ እንደተመለከትነው የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ዕቃዎች የሆኑ ሁሉ ስለራሳቸው ያላቸውን የግል መረጃዎች ዝም ብለው በንዝህላልነት አስፈላጊ ላልሆኑ ጉዳዮች ማጋራት አይገባቸውም፡፡ ቢያጋሩ ግን መረጃው ተመልሶ እነርሱን ለመጉዳት ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችል መረዳት ያስፈልጋል ፡፡ ክርስቲያኖች የኢንተርኔት አጠቃቀማቸውን አስተውለው እንዲመረምሩ ግድ የሚልበት ሌላም ምክንያት አለ፡፡ ይኸውም ሰይጣን ኢንተርኔትን ተጠቅሞ የትዕቢትን ዘር በልባቸው ውስጥ ሊዘራ/ሊተክል የሚችል መሆኑ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ኢንተርኔት ሰይጣን ይህንን በቀላሉ ማድረግ እንዲችል ምቹ ዕድል ይፈጥርለታል፡፡

“ንጉሡም፦ ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን? ብሎ ተናገረ።” ዳንኤል 4፥30

የባቢሎን ንጉሥ እንዲህ አይነት የትዕቢት ቃል ይዞ መቆሙን ተመልከቱ! ‹‹እኔ ያሰራኋት!›› ብሎ የትምክህት ቃል ይዞ ነው የሚታየው፡፡ Will Storr የተባለ ጋዜጠኛ በቅርቡ ያሳተመው Selfie – How We Became So Self-Obsessed and What It’s Doing to Us (2019) ለዚህ አንዱ ምስክር ነው። ጸሐፊው በዚህ መጽሐፉ የሰውን ልጅ ግለኝነትና ቅጥ ያጣ ራስ ወዳድነት ምንጩ ምን እንደሆነ መርምሮ ኢንተርኔት በዚህ ውስጥ ያለውን ድርሻ አስፍሮአል።

የማህበራዊ ትስስር ገጾች ሰዎች በሌሎች ዘንድ ታዋቂነት ለማትረፍ ያላቸውን ጥልቅ ምኞት በሚገባ ይጠቀሙበታል። ምኞታችንን ተጠቅመው ልንሸከመውና ፈጽሞ ልንደርስበት የማንችለውን ወይም ያልሆንነውን ሆነን ለመገኘት እንድንታትር ከባድ ጫና ያሳድሩብናል። ይህም ሳይሳካ ሲቀር ጭንቀታሞችና ደስታ የራቃቸው ሰዎች እንሆናለን፡፡ በክርስቲያናዊ እይታ ካየነው ታዲያ ሰይጣን እንዲህ እንድንሆን ስለሚፈልግ ሁል ጊዜ ከማህበራዊ ትስስር ገጾች ጋር ተቆራኝተን እንድንኖር ነው ምኞቱ። ምኞቱ ተሳክቶ ማንነታቸውን ከማናውቃቸው በኃጢአትና በልዩ ልዩ ርኩሰት ተዘፍቀው ከሚኖሩ እንግዶች ሰዎች ጋር ጓደኝነት ከመሰረትን በኋላ ቀስ በቀስ በእነርሱ ተጽእኖ ስር በመውደቅ ሳናውቀው ተለውጠን እንደነርሱ መሆናችን አይቀርም። ኢየሱስ ክርስቶስን ከማያውቁ ከተዋወቅናቸው እንግዶች ሰዎች ጋር ቀስ በቀስ ተመሳሳይ ፍላጎት፣ ዝንባሌና ስሜት ያለን ሰዎች ሆነን ራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ እነርሱን የሚያስፈራና የሚያስጨንቃቸው ነገር እኛንም ሊያስፈራንና ሊያስጨንቀን ይጀምራል፡፡ ታዲያ ይህ የጌታ ፈቃድ ነው ትላላችሁ? ፈጽሞ አይደለም! የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ይላል፦

“ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?” 2ኛ ቆሮንቶስ 6፥14

የስነ-ልቦና ምሁራን ኢንተርኔት በተለይም የማህበራዊ ትስስር ገጾች ከአትኩሮት አቅም (attention span) ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጥናት ላይ ይገኛሉ። የተማሪዎች የትኩረት አቅም መቀነስ ያሳሰባቸው የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮችና መምህራን በጉዳዩ ላይ ጥናት በማድረግ የጥንቃቄ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ ወጣቶች የማህበራዊ ትስስረ ገጾች ሱሰኞች ሆነው አፍላ የመንቃት ሰአታቸውን በዲጂታሉ አለም የሚያጠፉ ሆነዋል። የጽሑፍ መልእክት ሲለዋወጡ፣ ጓደኞቻቸው ያስተላለፉአቸው የተለያዩ ጽሑፎችና ፎቶግራፎች ላይ አስተያየት ሲሰጡና የዜናዎችን አርእስት ሲያገላብጡ ውድና የየቀኑ ምርጥ ሰዓታቸውን በከንቱ ያባክናሉ፡፡ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ አንዱንም ነገር በትኩረት አያዩም፤ ነገሮችን በጥልቀት የማየትና የመረዳት እድላቸው ይመክናል፤ እንዲህም አይነት ጠባይም ያዳብራሉ። በቅርቡ እ.ኤ.አ በ2018 ለህትመት በበቃ Anti-social Media: How Facebook Disconnects Us and Undermines Democracy በተባለው ሌላ መጽሐፋቸው Professor Vaidhyanatahan የሚከተለውን አስፍረዋል።

Facebook የተሰራበት መንገድ ተጠቃሚው በእርሱ ላይ ተጥዶ ምን ያህል እንደቆየ ለማወቅ እስከማይችል ድረስ እንዲቆጣጠረው ተደርጎ ነው፡፡ በምእራቡ አለም የሚታወቁት የተለያዩ የቁማር ጨዋታዎች ለተጫዎቾቹ ማበረታቻዎችን እየሰጡ ዘወትር ከዚያ እንዳይጠፉ ተደርገው እንደተቀረጹት ይህም እንዲሁ ነው። የማበረታቻዎቹም ዓላማ አንድ ጊዜ የ Facebook ደምበኛ ሆኖ የተሸለመ ሰው ሁል ጊዜ የኢንተርኔትን መስኮት ከፍቶ ከ Facebook ላይ እንዳይጠፋ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሱስ የተለከፈ ሰው ሌሎች ብዙ የተሻሉ ሊያስደስቱ፣ ሊያንጹና ሊጠቅሙ የሚችሉ ተግባሮች ቢኖሩም ከእነዚያ ይልቅ ጊዜውን በ Facebook ላይ እንዲያጠፋ ይገደዳል፡፡ በሌላ አነጋገር የ Facebook እስረኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ታስቦና ተጠንቶ የተደረገ እንጂ በአጋጣሚ የሆነ አይደለም። ይህም ማለት የማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘጋጁ ሆን ተብሎ ሱስ እንዲያሲዙ ተደርገው ነው ማለት ነው። አላማቸውም ሰውን የዲጂታሉ አለም ሱሰኛ ማድረግ ነው።

ወደ እግዚአብሔር ቃል መለስ ብለን በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10፡38-42 የተጻፈውን ስናነብ ማርታ ጌታ ኢየሱስን በቤትዋ እንግድነት ተቀብላ ለእርሱ የሚሆን ምግብ በማዕድ ቤትዋ ውስጥ በማዘጋጀት ደፋ ቀና እያለች በሥራ ተጠምዳ ትታያለች፡፡ ኢየሱስም፡-

“ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት።” ሉቃስ 10፥41-42

በዚህ ቃል ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ረጋ ብሎ በጨዋነት ማርታን ከስህተቷ ሲያርማት እናስተውላለን። በብዙ ነገር ከመጨነቅና ከመታወክ ይልቅ ማርያም እንደመረጠችው በኢየሱስ እግር ስር ቁጭ ብሎ ቃሉን መስማት ከሁሉ የሚበልጥ መልካም ነገር መሆኑን ነገራት፡፡ ኢየሱስን ለማስተናገድ ብላ ስለባከነችበት ስለዚህ መባከን እንኳ ማርታን እንዲህ ያረመ አምላክ በዚህ ዘመን አጭር ጽሑፍ በመላላክና ቻት በማድረግ፣ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የተለቀቁ ነገሮች ላይ ጥሩ ነው ወይም መጥፎ ነው እያሉ አስተያየት በመስጠት፣ የሚረቡም ሆነ የማይረቡ የተለያዩ መረጃዎችን ለሌሎች በማስተላለፍ አለ ቅጥ የተጠመድንና እረፍት የሌለን፤ በነዚህም ጥቅም በሌላቸው ነገሮች ላይ ብዙ ጊዜ እያጠፋን ከጌታ ኢየሱስ ጋር ግን ጥቂት የጽሞና ጊዜ እንኳን ያጣን እኛን እንዴት ባለ ቁጣ ይገስጸን ይሆን?

ለማጠቃለል ያህል ከመግቢያችን ላይ ያነሳነውን የባቢሎንን ንጉሥ ጉጉት እናስታውስ፡፡ ንጉሥ ሕዝቅያስ ጓዳውን ወለል አድርጎ ከፍቶ የእግዚአብሔርን ዕቃ በሙሉ ያሳየው የባቢሎን ንጉሥ ላይ ላዩን ለሕዝቅያስ አዝኖ እርሱን ለመጠየቅ መልእክተኞቹን የላከ ቢመስልም ጉጉቱ ግን ይሁዳንና በይሁዳ የነበረውን የከበረ ነገር ሁሉ ወደ ባቢሎን መማረክ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝቅያስ ከእርሱ በኋላ ለመጡት ልጆቹና ለዘሩ እርግማንን አስቀምጦ የባቢሎን ንጉሥ ምኞት ተፈጸመ። ይህ አሳዛኝ ታሪክ ነው!

በአሁኑ ዘመን ቤተክርስቲያን ወጣት ልጆቿ ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ሊመጣ ከሚችል አደጋ ራሳቸውን እንዲጠብቁ በጸሎት፣ በትምህርትና በምክር መምራት አለባት። ኢንተርኔት ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ግልጽ ቢሆንም በረቀቀ ሁኔታ ነፍስን ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮች በውስጡ እንደሚተላለፉ ተረድተን ከነዚያ ነገሮች እንድንርቅ የጌታ ኢየሱስ መንፈስ እንዲመራን ያስፈልጋል። ወጣቶች ከኢንተርኔት በራቁ ቁጥር “እኔ” “እኔ” የሚለውን ራስ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚያደርገው የትውልዱ ጫና እየቀነሰላቸው ይሄዳል።

በኢየሱስ ክርስቶስ ነገር ላይ ጉጉ ሆነን ከባቢሎን ንጉሥ ጉጉት ራሳችንን እንጠብቅ! አሜን!

Scroll to Top