ወንድም ኃይለየሱስ ወሰን | ከምስራቅ አያት አጥቢያ 

 (የእውነት ምስክር 3ኛ ዓመት ቁጥር 1-ነሐሴ 2014 ዓ.ም መጽሔት የተወሰደ)

ዘላለማዊው አምላካችን እግዚአብሔር ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን የማዳን ሥራውን በዘመናትና በትውልዶች ቅብብል ቀጣይነት ባለው መልኩ እያከናወነ ወደ ፍጻሜ የሚያመጣ አምላክ እንደሆነ ቅዱስ ቃሉ ያስተምረናል። (መዝ. 93፥2፣ ኢሳ.40፥28፣ መዝ. (102)፥12)

የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ገና ከጥንት ትውልድን በሚጠራና በሁሉም ዘመናት በሚነሱ ትውልዶች ዘንድ ህያው ሆኖ በሚኖር በህያው እግዚአብሔር የሚከወን በትውልድ መፈራረቅ ሳይናወጥ ቀጥ ብሎ የሚዘልቅ መለኮታዊ ሥራ ነው።

“ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር፥ ፊተኛው በኋለኞችም ዘንድ የምኖር እኔ ነኝ።” ኢሳ. 41፥4

ይህ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ በአንድ ትውልድና ዘመን ተለኩሶ ያ ትውልድ ሲያልፍ የሚቆምና የሚከስም የሰው ሥራ ሳይሆን ህያው እግዚአብሔር በተመደበላቸው ጊዜ መጥተው በሚሄዱ ብዙ ትውልዶች መካከል አጽንቶ የሚያስቀጥለው በትውልድ ቅብብል እያየለ የሚዘልቅ ሰማያዊ የእግዚአብሔር አሳብ መሆኑን ማወቅና ማስተዋል በእጅጉ ጠቃሚ እውነታ ነው። መዝሙረኛው ዳዊትም ይህን ተረድቶ በመዝ. (145)፥ 3-6 እንዲህ ሲል ዘምሮለታል፦

“እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም። ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፥ ኃይልህንም ያወራሉ። የቅድስናህን ግርማ ክብር ይናገራሉ፥ ተኣምራትህንም ይነጋገራሉ። የግርማህንም ኃይል ይናገራሉ፥ ታላቅነትህንም ይነጋገራሉ፥ ብርታትህንም ይነጋገራሉ።”

በቤተክርስቲያን በኩል ተገልጦ የሚፈጸመው መለኮታዊው የአምላካችን የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ባለቤትነቱ የራሱ የእግዚአብሔር ቢሆንም በየትውልዱና በየዘመናቱ የእኔ ብሎ መርጦ ለራሱ ስራ በለያቸውና ሠርቶ በሚያሰራቸው ባሪያዎቹና ህዝቡ በኩል የሚገለጥ በመሆኑ ሥራው ቀጣይ ሆኖ እያሸነፈ እንዲሄድ ግን በየዘመናቱ የእግዚአብሔር ሆኖ በሚነሳ ትውልድ መካከል የራዕይና የተልዕኮ ቅብብል እና ሽግግር መኖሩ ደግሞ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል።

እግዚአብሔር አምላካችን በአንድ ትውልድ ላይ የሚሰራው ሥራ በቀደሙት ዘመናት በነበሩ ትውልዶች ከሠራው ሥራ ጋር ተያያዥነት ኖሮት እንዲቀጥል በብርቱ የሚሻ አምላክ በመሆኑ ራሱን “የአብርሃም፣ ይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ” ኋላም በአብርሃም ቃል ኪዳን እስራኤል ተብለው ለሚነሱ ትውልዶች ሁሉ አምላክ ይሆን ዘንድ “የእስራኤል አምላክ” ብሎ በመጥራት የትውልዶች ሁሉ አምላክ መሆኑን አውጇል።

እንግዲህ በዚህ የእግዚአብሔር ሥራ ባህርይ እንደምንረዳው አንድ ለዘመኑና በዘመኑ የሚነሳ መንፈሳዊ ትውልድ አውራሽ እና ወራሽ እንዳለው መረዳት ይኖርበታል ማለት ነው። እግዚአብሔር በየዘመናቱ ብልጭ ብሎ እንደሚጠፋ “የእሳት ራት” ብርሃን አይነት ሥራ ስለማይሰራ አባት አልባ ሆኖ የሚነሳ እና ወራሽ አልባ ሆኖ የሚደመድም መንፈሳዊ ትውልድን ማየት አይሻም። በመሆኑም አንድ ተተኪ ትውልድ በብርቱ መንፈሳዊ አቅም ታጥቆና ፈርጥሞ ፈጥኖ በመሮጥ ተነሳሽነት ውስጡ ቢነሸጥም ብዙ የእግዚአብሔር ኃያላን እርሱ በተጠራበት የእግዚአብሔር መንገድ ከእርሱ በፊት ሮጠው ተልዕኮው የእርሱ ዘመን ድረስ የመጣበትን ረቂቅ ጥበብ ለማስተዋል ወደኋላው ዞር ብሎ የዱሮውን ዘመን እንዲያስብና የብዙ ትውልድን አመታት እንዲያስተውል በቅዱስ ቃሉ ይመከራል።

የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በዘመኑ የተሰጠውን የእግዚአብሔር አሳብ አገልግሎ ተልዕኮውን እያገባደደ ባለበት ወቅት ለተተኪው ትውልድ ያስተላለፈው ይህ ወሳኝ መለኮታዊ መርህ ዛሬም እግዚአብሔር በዘመኑ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስነሳው ተተኪ ትውልድ መንፈሳዊ ሩጫው የተሳካ እንዲሆን ሊያስተውለውና ሊከተለው የሚገባ መንፈሳዊ እውነታ ነው። ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል፦

“የዱሮውን ዘመን አስብ፥ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ፥ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።” ዘዳ.32፥7

በዚህ ቃል እግዚአብሔር በባሪያው በኩል ለህዝቡ እያስተላለፈለት ያለ በተለይ ተተኪ ሆኖ የሚነሳ ወራሽ ትውልድ ሊያስብበት የሚገባ እጅግ ውብና ድንቅ የእግዚአብሔር መንግስት ባህርይ አለ። ይኸውም ትውልድ ተሻጋሪ ሆኖ የሚቀጥለው የእግዚአብሔር ሥራ በክብር እንዲቀጥል በትውልዶች መካከል የመንፈስና የራዕይ እንዲሁም የተልዕኮ መያያዝ መኖሩ የግድ አስፈላጊ መሆኑ ነው። ይህም እንዲሆን ደግሞ መጽሐፉ ተተኪውን ትውልድ የድሮውን ዘመን አስብ፣ የብዙ ትውልድንም አመታት አስተውል፣ አባትህን ጠይቅ፣ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ የሚል ብርቱ ማሰብ፣ ማስተዋልና መጠየቅን የሚሻ ትዕዛዝን ሰጥቶታል። እንዲሁም ምን እንደሚያስብ፣ ምን እንደሚያስተውል፣ ማንን መጠየቅ እንደሚገባው ጭምር ግልጽ መርህ ያስቀምጣል። በዚህ ቃል የዱሮውን ዘመንና የብዙ አመታትን ትውልድ በማለት ትውልድ እንዲያስብና እንዲያስተውል የተቀመጠለት ጉዳይ ከእርሱ በፊት ባለፉት ዘመናትና ትውልዶች የነበረውን የእግዚአብሔር ሥራና አሠራር ሲሆን መጠየቅ የሚገባው ደግሞ አባቶችህንና ሽማግሌዎችን በማለት በየዘመናቸው የእግዚአብሔር እጅ አርፎባቸው ፈቃዱን ያገለገሉ የእምነት አባቶችን ነው፤ በተጨማሪም ዕብ. 13፥ 7-8 እንመልከት።

ይህም አንድ ትውልድ ከእርሱ በፊት የነበረውን የእግዚአብሔር ሥራ በማሰብና በማስተዋል እግዚአብሔርን ማወቅ እንዲሁም ከመንፈሳዊ አባቶቹ ጋር የመንፈስ መያያዝ እንዲሆንለት ይረዳዋል። ትውልድ የሚያስብና የሚያስተውል ሲሆን የእምነት አባቶችን በመጠየቅና የእግዚአብሔርን መንግስት ምስጢር፣ መንገዱንና አደራረጉን በማወቅ ከአባቶቹ ጋር ከሠራው እግዚአብሔር ጋር መያያዝ ይሆንለታል።

አባቶችንና ሽማግሌዎችን በተመለከተ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በመስበክ ብቻ በኩል ሳይሆን አስቦና አስተውሎ ለሚጠይቅ ትውልድ የሚያስታውቁት እና የሚያስተላለፉት እግዚአብሔር በእነርሱ ህይወት የሠራው ከእነርሱም ጋር የሠራው የከበረ መንፈሳዊ ጥሪት እንዳለ እናያለን። ዛሬ መካሪና ተው ባይ አባትና ሽማግሌ አጥቶ ፈር በለቀቀ ምድራዊና ሥጋዊ አካሄድ በሚነዳው መንፈሳዊ ነኝ ባይ ትውልድ መካከል እየኖረ ቆም ብሎ የእግዚአብሔርን መንግስት ሥራ ባህርይ በማስተዋል በትሁት ልብና መንፈስ ተውቦ ከእውነተኞች የእምነት አባቶቹ ራዕይና ተልዕኮ ጋር ራሱን አስተሳስሮ የእግዚአብሔርን መንገድና የአደራረግ ጥበብ የሚካፈል ተተኪ ትውልድ፥ እርሱ በዘመናት የተጠበቀውና ትውልዶች የቃተቱለት የመጨረሻው ዘመን የክብር መንፈሳዊ እንቅሰቃሴ መጎናጸፊያ የሚያርፍበት ይሆናል።

የእግዚአብሔርን ቃል በመሳፍንት መጽሐፍ ምዕራፍ 6 ላይ ስንመለከት ጌዴዎን ምንም እንኳን በድካም ህይወት ተይዞ ከጠላቶቹ ተሸሽጎ በወይን መጥመቂያው ስንዴ ሲወቃ ቢገኝም እርሱ ያለበት የክብር ያልሆነ ሥፍራ እና የህይወት ይዘት ድረስ ድንገት ዘው ብሎ በመግባት “አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” ብሎ ላስገረመው የእግዚአብሔር መልዕክተኛ የመለሰለትን መልስ ስንረዳ በዚህ ጎበዝ ላይ የእግዚአብሔር አይኖች እንዲያርፉ የሆነበትን አንድ እውነት እንረዳለን። የጌዴዎን መልስ እንዲህ ነበር፤ “አባቶቻችንስ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ?” ጌዴዎን አቅም አጥሮት እና ጊዜ እየጠበቀ ሆኖ እንጂ በውስጡ ለካ የዱሮውን ዘመን፣ የብዙ ትውልድንም አመታት ማሰብና ማስተዋል ችሎ ነበር ማለት ነው። “አባቶቻችን ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ?” በማለቱም ከአባቶቹ ጠይቆ የሰማው እነርሱም ያሳወቁት የእግዚአብሔር አደራረግ እንደነበረ እናስተውላለን። በመሆኑም ይህ ወጣት ምንም እንኳ በወቅታዊ ሁኔታው ከጠላቶቹ ተሸሽጎ በወይን መጥመቂያው ስንዴ ሲወቃ ይገኝ እንጂ አንድ ወደ ኋላ ዞር ብሎ የሚያስበውና የሚያሰላስለው፣ አባቶቹንም ጠይቆ ያወቀው የእግዚአብሔር ተዓምራቶች ብሎ የሚያወሳው የቀደመ የእግዚአብሔር ሥራ በልቡናው የነበረ በመሆኑ መንፈሱ ከአባቶቹ መንፈስ ጋር መያያዝ እንደሆነለት እናያለን።

በመሆኑም በመሳፍንት 6፥14 ላይ እንደምናየው እግዚአብሔርም ወደ ጌዴዎን ዘወር ብሎ “በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ” ብሎ እርሱ ደግሞ በራሱ ዘመን የሚሮጥበትን በእግዚአብሔር ጸጋ የሚፈጽመውን ራዕይና ተልዕኮ ሲሰጠው እናያለን።

ይህን ራዕይና ተልዕኮ ከእግዚአብሔር ከመቀበሉ በፊት ግን መንፈሱ ከአባቶቹ መንፈስ ጋር በቅንነትና በንጽህና የተያያዘ መሆኑ በእግዚአብሔር መረጋገጡን ልብ ይሏል። በመሆኑም እግዚአብሔር ለአንድ ትውልድ በፊቱ ሊሮጥለት ያለ ቀጣይ ራዕይና ተልዕኮ ከመስጠቱ አስቀድሞ ያ ትውልድ ከእርሱ በፊት በእግዚአብሔር መስመር የሮጡትንና የቀደሙትን ትውልዶች በማሰብና በማስተዋል ሽማግሌዎችን ጠይቆ በሚያውቀው መንፈሳዊ እውነት ከአባቶቹ መንፈስ ጋር በመንፈስና በራዕይ መያያዘ እንደሚኖርበት እናስተውላለን።

ጌዴዎን አባቶቹ ይነግሩት የነበረው የእግዚአብሔር ተዓምራት ውስጡን ተቆጣጥሮት አሳቡና መንፈሱ ሁሉ “ያ አባቶቻችን ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ?” በሚል የፍለጋ መንፈስ የተያዘ ነበረ፤ እግዚአብሔር በዚህ ሰው ያየውና ጌዴዎንን ተተኪ የእስራኤል መስፍን ሆኖ እንዲነሳ ጽኑዕ ኃያል ሰው ያስባለው፣ በዚህ በጉልበትህ ሂድ የተባለበት ያ ጉልበት እግዚአብሔር በቀደሙት ዘመናትና ትውልዶች የሰራውን በማሰብና በማስተዋል ከአባቶቹ ጠይቆ በማወቅ መንፈሱ ሄዶ ከአባቶቹ መንፈስ ጋር በመያያዙ እንደሆነ ማየት ያስፈልጋል።

የዛሬው ጌዴዎንስ ምን ታስባለህ? ምንስ ታስተውላለህ? ማንንስ ጠይቀህ ምን እየሰማህና እያወቅህ ነው? መጽሐፍ ግን እንዲህ ይልሃል፤ “የዱሮውን ዘመን አስብ፥ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ፥ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።” ዘዳ. 32፥7

አዎ! የጌዴዎን አባቶች ለእርሱ የነገሩት እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋርና በእነርሱ የሠራው ተዓምራት እንደነበረ ሁሉ እንዲሁ እግዚአብሔር ከሠራባቸውና እየሠራባቸው ካሉ የእምነት አባቶች ምን እየጠየቅህ ይሆን? በፍጹም አትጠራጠር! በዚህ ዘመን የእግዚአብሔርን የክብር ሥራ ለመስራት እግዚአብሔር በበቀል ቅባት የሚያስነሳቸው ተተኪዎች አሉ፤ እጅግ ብዙ በጣምም ብዙ የተትረፈረፈ ጸጋና ቅባት ፈሶባቸው የእግዚአብሔርን መንግስት ውበት ገልጠው መደምደሚያውን የሚሠሩ ተተኪዎች ይነሳሉ! ፈጽሞ እንዳትጠራጠር! ብዙ ተተኪዎች ፍጥረትን ጉድ በሚያስብል ጸጋና ቅባት ተሸልመው ይነሳሉ! አንተ ከእነርሱ መካከል አንዱ ለመሆን ታዲያ ቁልፉ ማሰብና ማስተዋል ችለህ ከቀደሙት ትውልድ እና ከአባቶችህ መንፈስና ራዕይ ጋር መያያዝ መቻልህ ነው፤ ከአባቶችህ መንፈስ ጋር ተያያዝ፤ ያኔ አንተም በዘመንህ የምትሮጥለት ራዕይ በአሸንዳ እንደሚፈስ ውሃ ሆኖ ፈጥኖ ያገኝሃል።

አዎን! ይህ ነው የወራሽ ትውልድ ባህርይ፣ ከእምነት አባቶችህ መንፈስና ራዕይ ጋር ተያያዝ! ያኔ እነርሱን ከያዛቸው መንፈስ ከምንጩ ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር በእውነት ትያያዛለህ። የአባቱን የኤልያስን እጥፍ መንፈስ ተቀብሎ ያስቀጠለውና መጎናጸፊያውን በመውረስ በእጥፍ ቅባት የእግዚአብሔርን ጦርነት በዘመኑ የመራውን ኤልሳዕን ተመልከት፤ ከአባቶቹ መንፈስ በፍጹም አልለይም ብሎ እንዴት እንደተያያዘ! ኤልያስ ራሱ እንኳን ሶስት ጊዜ በተልዕኮ የሚሄድበትን ሥፍራ እየጠቀሰ እንዲለየው አጥብቆ ቢጠይቀውም እርሱ ግን “ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፥ አልለይህም” እያለ መንፈሱን ከአባቱ መንፈስ ጋር ላይለያይ እንዳያያዘ አስብ፣ አስተውልም! ኤልሳዕ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” በማለቱ ከኤልያስ ጋር የሠራ እግዚአብሔር ከኤልሳዕም ጋር በእጥፍ መንፈስ ቀጥሏል። ዛሬም “የአባቶቼ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” ብሎ ከሚነሳ ትውልድ ጋር በብዙ እጥፍ መንፈስ መሥራቱን ይቀጥላል።

እንዲህ አይነት መያያዝ ነው የአባቶችን እጥፍ መንፈስ ወራሽ አድርጎ ትውልድን የሚስነሳው። ይህን መንገድ የሚያስተውሉና የሚጠብቁም ድልና ማሸነፍ የእነርሱ ይሆናል፤ የእግዚአብሔርንም የተስፋ ቃል ወራሾች ይሆናሉ።

Scroll to Top