ቢሾፕ ጌታሁን ላምቤቦ 

የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ዋና ጸሐፊ

በኦሪት ዘኁልቁ 24፥4 “የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦” በማለት ባለ ራእይ ሰው የሚያየው የራሱን ህልም ሳይሆን አምላክ የሚያሳየውን ራዕይ እንደሆነና ለራዕዩም ዓይኖቹ የተከፈቱለት መሆኑን ያስረዳል።

ዮሐንስ ወንጌል 4፥35 “እናንተ፦ ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ፥ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራውም አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ።” በማለት የራሳቸውን አስተያየት ትተው የአምላክን ጊዜ አውቀው መከሩ እንደነጣ እንዲመለከቱ ሲነግራቸው እናያለን።

በተለያዩ መዝገበ ቃላት እንደተገለጸው ወደፊት ሊሆን ወይም ሊደረግ የሚችለውን ነገር ቀድሞ በማየት በሃሳብ ወይም በዕቅድ ደረጃ አስቀምጦ በሂደት ትኩረት ሰጥቶ ያንን ጉዳይ ተከታትሎ የሚፈጽም ሰው የራዕይ ሰው ይባላል።

እንግዲህ የራዕይ ሰው መሆን ማለት ከላይ እንደተቀመጠው ወደፊት ሊሆን ያለውን ነገር ከእግዚአብሔር ተቀብሎ በራሱ ደረጃ በትኩረት እየተከታተለ ከውጤት ላይ ለማድረስ ዕለት በዕለት የሚተጋ ሰው ነው ማለት ይቻላል።

በቅዱስ ቃሉ፦ “ራዕይ የሌለው ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ሕግን የሚጠብቅ ግን የተመሰገነ ነው።” (ምሳሌ 29፥18) በማለት ራዕይ ማጣት የሚያመጣውን ከባድ ጉዳት (ከንቱነት፤ ልቅነት) በግልጽ አስቀምጦአል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ራእይ ለትጉህ ነው እንጂ ለሰነፍ ሰው አይታየውም፤ አይሰጠውምም።

ዕብ. 11፥25-26፦ “ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቶአልና።” እንደ ሙሴ ከጊዜያዊው ይልቅ የዘላለሙን መምረጥም ሆነ አርቆ ማየት የሚችሉ ባለ ራዕይ ሰዎች ናቸው ቤተክርስቲያንን ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያደርሱት። ባለ ራዕይ ከመሆናቸው የተነሳ ጊዜያዊ ስሜትን ተቆጣጥረው የእግዚአብሔርን ራዕይ ማየት በመቻላቸው ካሰቡበት ወይም ካለሙበት ቦታ በድንቅ ሁኔታ የደረሱ ብዙ ሰዎችን እናያለን። የተምታታ ሕይወት ያላቸው፤ በረባ ባልረባ ሁሉ እየተወሰዱ፤ ወዲህም ወዲያም እየተንሳፈፉ፤ በንፋስ የሚነዱ ሰዎች ለተጠሩበት ዓላማ ሳይበቁ፤ እግዚአብሔር ወደሚያሳያቸው ራዕዮቻቸውም ሳይደርሱ በመሃል ይቀጫሉ።

እግዚአብሔር ኢያሱን ያስጠነቀቀው ወደፊት እንጂ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ወይም ዘወር እንዳይል በጥብቅ የመከረው ይህን ስለተረዳ ነው (ኢያሱ 1፥7)።

ሐዋርያው ጳውሎስም እግዚአብሔር ያሳየውን ራዕይ እንዳለ ተቀብለው ለቀጣይ ትውልድ ሊያስተላልፉ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን ወጣት አገልጋዮችን በተለይም ጢሞቴዎስንና ቲቶን እጅግ ሲያደፋፍርና ሲያበረታታ፤ ሲያስጠነቅቅም ይታያል።

ያዕቆብም ምርጫቸውን ባበላሹት ልጆቹ ፈንታ ራዕይ ያላቸውን የዮሴፍን ልጆች እንደተካቸው፤ ዕድላቸውን በማበላሸት ማለትም የራእይ ሰው ባለመሆን የፍጻሜውን ድል ያጡ እንደ ዮናስ እና ዴማስ አይነቶች ብዙ አሉ። እኛም እንደ ነቢዩ ዮናስ፤ እንደ ዴማስም ሆነን ራዕያችን በመጨረሻ እንዳይበላሽብን በብዙ መልኩ ልናስብበት፤ ልንጠነቀቅም ይገባል። አራት ምዕራፎች ብቻ ያሉትን የትንቢተ ዮናስን መጽሐፍ ስናነብ፦በምዕራፍ አንድ ዮናስ ከእግዚአብሔር ሲሸሽ አይተን፤ በምዕራፍ ሁለት ደግሞ ዮናስ ወደ እግዚአብሔር ሲመለስ እናያለን፤ በምዕራፍ ሶስት ላይ በሚገርም ሁኔታ ዮናስ ከእግዚአብሔር ጋር ሲሰራ እናይና፤ በምዕራፍ አራት ላይ ግን ዮናስ ከእግዚአብሔር ሲለይ ያበቃል፤ የመጨረሻ ውጤቱ ፍጻሜው ተበላሸበት። ስለዚህ ሁላችንም ‘አቤቱ ፍጻሜዬን አሳምርልኝ’ እያልንና የእግዚአብሔርን ራዕይ እየተከተልን በተጠንቀቅ ልንኖር ይገባናል ማለት ነው።

በመሆኑም የራዕይ ሰው የመሆን ፍላጎት እና መንፈስ ያለው ሰው የሚከተሉት ባሕሪያት ሊኖሩት ይገባል።

1. የራዕይ ሰው እንደ ንስር እስከ ሩቅ ያያል፤ ወደፊት ይዘረጋል!

ዘፍ. 22፥4 ላይ ተጽፎ እንደምናነበው ባለራዕዩ አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን እንዲሰዋ በተጠየቀ ጊዜ “በሦስተኛውም ቀን አብርሃም ዓይኑን አነሣና ቦታውን ከሩቅ አየ” ይላል። ይህንንም ተከትሎ በዕብራውያን መልእክት አርቆ የሚያይ መሆኑን ስለ እምነቱ ሲናገር፦ “እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያስነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፥ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው።” ተብሎ ተተረከለት።

በመጽሐፈ ኢዮብ ከተጠቀሱት አዕዋፍና አራዊት አንዱ የሆነው ንስር በሩቅ ሆኖ የማየት ችሎታው ተደንቆለታል። “በዚያም ሆኖ የሚነጥቀውን ይጐበኛል፤ ዓይኑም በሩቅ ትመለከታለች፤” (ኢዮ 39፥29)።

እንዲሁም ስለ ጉንዳን ሲናገር “ገብረ ጕንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው፥ ነገር ግን በበጋ መኖዋቸውን ይሰበስባሉ።” በማለት የወደፊትን ሁኔታ አይተው በቅድሚያ የመዘጋጀት ችሎታቸውን ያደንቃል። (ምሳ. 30፥25)

ሮሜ 4፥19 ደግሞ የአብርሃምን ሩቅ ተመልካች የራዕይ ሰው መሆኑን “የመቶ ዓመትም ሽማግሌ ስለሆነ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሳራ ማኅፀን ምውት መሆኑን በእምነቱ ሳይደክም ተመለከተ፤” በማለት ይመሰክርለታል።

ዘጸ. 2፥4 ላይ የተጠቀሰችው የሙሴ እህት ራእይ ባይኖራት ኖሮ የዛሬን ሙሴ አናገኘውም ነበር። እርስዋ ግን “እኅቱም የሚደረግበትን ታውቅ ዘንድ በሩቅ ቆማ ትጎበኘው ነበር።” በማለት መልካም ሥራዋ የራዕይ ሰው መሆንዋ ተመሰከረላት።

ራዕይ ያለው ሰው ካጋጠመው ከባድ ነገር የተነሳ ወዲያውኑ ተስፋ ቆርጦ ከዓላማው አይመለስም፤ እንደ ጴጥሮስ ፍጻሜውን ያይ ዘንድ ይጣጣራል እንጂ። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው፦ “ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፥ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ።” (ማቴ. 26፥58)

በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ላይ ታሪኩን የምናገኘው የጠፋው ልጅ ራዕይ አልነበረውም። ከጊዜ በኋላ ግን የመከራው ብዛት ሲያጦዘው ወደ ልቡ ተመለሰና ማሰብ ጀመረ። በትንሽም ቢሆን አርቆ ለማየት ሞከረና ህይወቱ ሲታደስ፣ ታሪኩም ሲቀየር እናያለን። እንዲህ ይላል፦ “ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ።” (ሉቃስ 15፥17-19)

ሐዋርያው ጳውሎስ ያን ሁሉ ቢለፋም፣ ቢንከራተትም እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ያለው ራዕዩ ወደ ፊት መዘርጋት መሆኑን “አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤” (ፊልጵ. 3፥12-15) በማለት ሁላችንም እንደዚህ ወደፊት የምንዘረጋ ባለራዕይ እንድንሆን ይጋብዛል።

2. የራዕይ ሰው በየጊዜው ያድጋል! 

የራዕይ ሰው ቋሚ ምልክቱ በሁሉም ነገር ሁልጊዜ ማደግን ማእከል ማድረጉ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በወንጌል የወለደውን ልጁን ጢሞቴዎስን የሚያስጠነቅቀው ይህን እንዲያዘወትር ነው። “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፥ ይህንም አዘውትር” እያለው (1ኛ ጢሞ. 4፥15)። በመጽሐፈ ምሳሌ ስለ ልባም ሴት በምሳሌነት የተጠቀሰችው ሴት አንዱ ችሎታዋ ባለ ራእይ ሆና እስከ ሩቅ አገር ድረስ ሄዳ ምግብን መሰብሰብ መቻሏ ነበር:: “እርስዋ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፤ ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች።” (ምሳ 31፥14) በማለት ያደንቃታል። በ1ኛ ሳሙ. 3፥19 ላይ “ሳሙኤልም አደገ፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከቃሉም አንዳች በምድር ላይ አይወድቅም ነበር። እስራኤልም ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ነቢይ ይሆን ዘንድ የታመነ እንደ ሆነ አወቀ። እግዚአብሔርም ደግሞ በሴሎ ተገለጠ፤ እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ቃል ለሳሙኤል በሴሎ ይገለጥ ነበር። የሳሙኤልም ቃል ለእስራኤል ሁሉ ደረሰ።” ብሎ ሳሙኤል ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መገለጥ/ራዕይ ለህዝቡ ለማድረስ ዕውቅና ባለው ደረጃ ማደጉን በትክክል ያሳያል። ምክንያቱም ሳሙኤል ከቤተመቅደስ ካለመጥፋት የጀመረው ራእይ ነበረውና።

ሉቃስ ወንጌል 1፥80 ላይ የተጠቀሰው ዮሐንስ አድጎና በመንፈስ ጠንክሮ ለእስራኤል እንደታየ ቃሉ ያስረዳል “ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ፥ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።” በምድረ በዳ ያኖረው ራዕዩ ነበር።

በዚሁ መጽሐፍ 2፥40 ላይ ደግሞ ስለ ኢየሱስ ሁለንተናዊ ዕድገት ሲገልጽ “ሕፃኑም አደገ፥ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ ጠነከረ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።” በማለት ያስረግጥና በ2፥52 ላይ ደግሞ “ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።” ብሎ ዕድገቱ ተራ ዕድገት ሳይሆን ጥበብና ሞገስ ያለበት መሆኑንም ጭምር ያስረዳል።

ሉቃስ 13፥19 ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ዕድገት በምሳሌ ሲጠቅስ “ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ አደገችም ታላቅ ዛፍም ሆነች፥ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ” እስከ ማለት ማደጉን ይገልጻል። ሰውዬው ሰናፍጭን የጣላት ወደፊት ብዙ በማፍራት ራዕይ ስለነበረ ራዕዩ ተፈጸመለት። በመጽሐፈ ምሳሌ 3፥4 ላይም “በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ” በማለት ሰው ባለ ራዕይ ሆኖ በእግዚአብሔር መንገድ ሲተጋ ውጤቱ በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስንና መልካም ዝናን እየተጎናጸፈ የሚሄድ ዕድገት ላይ የሚያደርስ መሆኑን ያሳያል።

3. የራዕይ ሰው ከፊት ይልቅ ይተጋል፤ በትጋቱ እየጨመረ፣ እየታወቀ ይሄዳል! 

1ኛ ቆሮ. 8፥22 “ብዙ ጊዜም በብዙ ነገር መርምረን ትጉ እንደ ሆነ ያገኘነውን፥ አሁንም በእናንተ እጅግ ስለሚታመን ከፊት ይልቅ እጅግ ትጉ የሚሆነውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር እንልካለን።” ተብሎ የተጠቀሰውን ቲቶን እንዲተጋ ያደረገው ራእይ ያለው ሰው መሆኑ ነው ። ራዕይ ሰውን ከስንፍና ወደ ትጋትና ጥንካሬ የሚያሸጋግር ድልድይ ነው ።

አንድ ቀላል ምሳሌ ልጥቀስ! ከአንደኛ ደረጃ ት/ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ተማሪዎች ጠንክረው እንዲሰሩ የሚያደርጋቸው ለሚደርሱበት ቦታ ባለ ራእይ መሆናቸው ነው። አንድ ወቅት ሃይ ስኩል ተማሪ በነበርኩ ጊዜ የክፍል ጓደኛዬ በሚገባ እንድናጠና ፈልጎ ከምንማርበት ትምህርት ቤት የጠዋት ፈረቃ ተማሪዎች ሲወጡና የከሰዓት ፈረቃ ተማሪዎች ሲገቡ በር አካባቢ ላይ ቆመን እንድናያቸው አደረገኝና፦ “ይሄን ሁሉ ተማሪ ያየነው በእኛ ትምህርት ቤት ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ሁሉ ሊኖሩ የሚችሉትን በዓይነ ህሊና ብንመለከት ብዙ ሺህ ናቸውና ከነዚህ ሁሉ ጋር ስለምንወዳደር ተግተን እናጥና” ያለኝ ጊዜ ትዝ ይለኛል። ጓደኛዬ ያሳየኝም ነገር ከራሴና ከትምህርት ቤቴ አሻግሬ እንዳይና ባለ ራዕይ ሆኜ እንዳጠና ጠቅሞኛል።

2ኛ ጴጥ. 1፥10 “ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤ እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና። እንዲሁ ወደ ዘላለሙ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት መግባት በሙላት ይሰጣችኋልና።” የሚለውን ስንመለከት እያደገ የሚሄድ ትጋት መጨረሻው መንግሥተ ሰማያትን በሙላት ወደ መውረስ ያደርሳል ማለት ነው።

4. የራዕይ ሰው ለሁሉም ነገር ሁልጊዜ ይጠነቀቃል!

1ኛ ጢሞ. 3፥1-5 እና በቲቶ 1፥5-9/2፥7- 8 እንደተገለጸው ራዕይ ያለው ሰው ከምንም አስቀድሞ ለራሱ፣ ለቤተሰቡ እና ለትምህርቱ/ ለአገልግሎቱ/ መጠንቀቅ እንዳለበት፣ የሚያሙ ሰዎች ምክንያት አጥተው እስኪያፍሩ ድረስ እጅግ ጠንቃቃ ሊሆን እንደሚገባ ያስረግጣል።

ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ. 9፥27 ላይ “ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።” በማለት ለራሱ ምን ያህል ጠንቃቃ መሆኑን ያሳያል። ሌሎችንም እንደሚከተለው መክሮአል፦ “ለአክሪጳም፦ በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽመው ተጠንቀቅ በሉልኝ።” (ቆላ. 4፥17)፤ ለጢሞቴዎስ፦ “እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ።” (1ኛ ጢሞ. 4፥13)፤ “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥”(4፥16)፤ ዕብ. 8፥5 “…በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና።” ወዘተ እያለ ሁሉም አገልጋዮች ራዕያቸው እንዳይበላሽ ሁሉን ነገር ተጠንቅቀው እንዲሰሩ ራሱን በምሳሌነት እያቀረበ ትኩረት ሰጥቶ ያስተምር ነበር።

ዕብራውያን መልእክት 12፥13 ላይም “ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።” እያለ ቅድስና አምላክን ለማየት የሚያስችል ኃይል እንዳለው በማስረገጥ የቅድስና ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ያስገነዝባል።

እግዚአብሔር ሙሴንም ካስጠነቀቃቸው ነገሮች አንዱና ዋናው በዘጸ. 25፥40 ላይ “ በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ።” የሚለው ነበር።

5. የራዕይ ሰው በመከራ ውስጥ ሆኖ እንኳን ተስፋ ያደርጋል!

ሮሜ 4፥19 ላይ ስለ አብርሃም አባታችን የራእይ ጽናት ሲመሰክር “ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ  በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም።” ይላል።

ሐዋርያት ሥራ 7፥55 ላይ በድንጋይ እየተወገረ እያለ እንኳን ባለራዕዩ እስጢፋኖስ ያየው ሰማይን ነበር። “መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፦ እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ።” ብሎ ቃሉ ይመሰክራል።

ሐዋርያው ጳወሎስ በዚያ ሁሉ ተዘርዝሮ በማያልቅ መከራ፣ ስደትና ችግር ውስጥ ሆኖ እንኳን “የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።” (2 ቆሮ 11:28) እያለ ከመከራው ይልቅ በክርስቶስ ላገኛቸው ክርስቲያኖች ይጨነቅ ነበር። ከዚህም የተነሳ የመከራው ብዛት ውጫዊ ሰውነቱን ቢያጎሳቁልም ለውጫዊው ሰውነቱ ሳይሳሳ ስለውስጣዊ ማንነቱና ስለመንፈሳዊ ሕይወቱ ብርታት እንዲህ ይላል፦ “ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል።”(2ኛ ቆሮ. 4፥16)

6. የራዕይ ሰው ጸጋውን ለማሳደግ ሁልጊዜ ይጥራል፤ ይዘጋጃል!

ሮሜ 1፥14 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ጸጋውን ለማሳደግ ምን ያህል ጥረት እንደሚያደርግ የተጻፈው ቃሉ ይመሰክራል “ለግሪክ ሰዎችና ላልተማሩም፥ ለጥበበኞችና ለማያስተውሉም ዕዳ አለብኝ፤ ስለዚህም በሚቻለኝ መጠን በሮሜ ላላችሁ ለእናንተ ደግሞ ወንጌልን ልሰብክ ተዘጋጅቼአለሁ”።

2ኛ ቆሮ. 6፥3-10 በግልጽ እንደተጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱ ላይ አንዳች ነቀፋ እንዳይታይበት በሁሉም ነገር ልቆና ብቁ ሆኖ ለመገኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርግ እንደ ነበር ነው። “አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፥ በመከራ፥ በችግር፥ በጭንቀት፥ በመገረፍ፥ በወኅኒ፥ በሁከት፥ በድካም፥ እንቅልፍ በማጣት፥ በመጦም፥…”

7. የራዕይ ሰው ጊዜውን በአግባቡ ይጠቀማል!

የዘላለምን ሃሳብ ዘርግቶ የሚሰራው እግዚአብሔር ጊዜን በአግባቡ እንደሚጠቀም በቃሉ በብዙ ሥፍራዎች ተጽፈው እናገኛለን። ለአብነት ያህል የሚከተሉትን ክፍሎች እንመልከት።

ኤፌ. 3፥11 “ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ፥”

ሐዋ. 17፥30 “እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀን ቀጥሮአልና፥”

ገላ.4፥4 “ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤”

ኤፌ. 1፥10 “በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።”

ኢሳ. 2፥2 “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ።”

ሚክ. 4፥1 “በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።”

መክ.3፥11 “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው።”

ሁሉን በአንድ ጊዜ ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር እንኳን አስቦ እና አቅዶ፣ ፕሮግራም አውጥቶ የሚሰራ ከሆነ እኛ በሁኔታዎች የተወሰንን የሰው ልጆች ምን ያህል ተጠንቅቀን ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም እንዳለብን ማወቅ የግድ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱሳችን የያዕቆብ መልእክት 4፥15 “ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል።” በማለት ለሁሉም ነገር ጊዜን በአግባቡ እንድንጠቀም ይጠቁመናል።

ከሁሉ በፊት የዘላለምን ሃሳብ በፕሮግራም ነድፎ የሚሠራው አምላካችን ትልቁና ዋና ምሳሌያችን ነው። በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድ ላይ የምናገኘው የአፈጣጠር ታሪክ የእግዚአብሔርን በመርሀ ግብር ላይ የተመሰረተ ተግባር በግልጽ ያመለክታል። ይኸውም በ1ኛ ቀን ብርሃን፤ በ2ኛ ቀን ጠፈር፤ በ3ኛ ቀን የብስ፤ በ4ኛ ቀን ብርሃናት፤ በ5ኛ ቀን ፍጥረታት፤ በ6ኛ ቀን ሰው፤ በ7ኛ ቀን እረፍት። አይገርምም? እኛም ተረጋግተን ለመስራትና የሚቀድመውን ለማስቀደም፣ የሚከተለውንም ለማስከተል የግድ በተዘረጋ ፕሮግራም መመራት ይኖርብናል።

በአጋጣሚና በዘፈቀደ የመሥራትን ልማድ ከእኛ አርቀን በዓላማና በዕቅድ ፕሮግራም አውጥተን ብንሠራ እንደዳዊት እኛም በዘመናችን የእግዚአብሔርን ሃሳብ በሙላት አገልግለን እናልፋለን፤ አሜን።

Scroll to Top