
ጸሃፊ፡- ቢሾፕ ደጉ ከበደ (degukebe@yahoo.com)
የታተመበት ቦታና ዓ.ም.፡- 2012 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ
አሳታሚ፡- የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን፣ ፖ.ሳ.ቁ. 4442፣ ስልክ 251-114-660086
አታሚ፡- ርኆቦት አታሚዎች የገጽ ብዛት፡- 227
መጽሐፉ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የቀረበ ነው፡፡ አንደኛው ክፍል ስለመዳን ምንነትና መዳን እንዴት እንደሚገኝ የሚያስረዳ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የተገኘውን መዳን አጥብቆ በመረዳት እስከመጨረሻ መጽናት እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ ነው፡፡ መጽሐፉ ማንኛውም አንባቢ መልእክቱን እንዲረዳ በማሰብ በቀላል አቀራረብ የተጻፈ ሲሆን ያዘለው እውቀት ግን ጥልቅ የሆነውን የእግዚአብሔር የማዳን አሰራር የሚያበራ ነው፡፡
‹‹መዳን›› የሚል ርዕስ በተሰጠው በመጀመሪያው ክፍል የሰው ዘር ሁሉ በኃጢአት እንደወደቀና ያለምንም ልዩነት ሰው ሁሉ መዳን የሚያስፈልገው መሆኑ፣ እግዚአብሔር ደግሞ በበኩሉ የመዳንን የተስፋ ቃል እንደሰጠ፣ ያም የተስፋ ቃል ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ ሲመጣ እንደተገለጠ፣ ይህም የተገለጠው የተስፋ ቃል በወንጌል ስብከት ለሰው ልጆች ሁሉ እንደሚደርስና በወንጌል የሚታወጁት የመዳን መልእክቶች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ እነዚህ በአምስት ምዕራፎች ተከፋፍለው የቀረቡ ሲሆን በአምስተኛው ምእራፍ ላይ የዳግም ልደትና የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎች ምስጢራት ተብራርተዋል፡፡ እነዚህም በወንጌል የሚታወጁት የመዳን መልእክቶች ናቸው፡፡ ይህ የመጀመሪያው ክፍል የመጽሐፉን የመጀመሪያ 142 ገጾች ወይም 63% ያህሉን ይሸፍናል፡፡
ሁለተኛው ክፍል ‹‹መዳንን መኖርና መፈጸም›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን የመጽሐፉን ቀሪ 85 ገጾች ወይም 37% ያህል ይሸፍናል፡፡ በውስጡ ያካተታቸው ጉዳዮችም መዳንን በጥልቀት ስለመረዳት፣ መዳንን በእምነትና በኃላፊነት ይዞ ስለመኖር፣ መዳን የሚቻለው ደግሞ በአካሉ (በቤተክርስቲያን) ውስጥ ሆኖ እንደሆነ፣ መዳንን በንስሐ ሕይወት መኖር እና ለመዳን እስከመጨረሻ መጽናት እንደሚያስፈልግ የሚያስረዱ ናቸው፡፡
ሰው የነፍሱን መዳን ለማግኘት የወንጌል ዋና ዋና ነገሮች ከተነገሩት በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹እነሆ የመዳን ቀን አሁን ነው›› (2ኛ ቆሮ. 6፡2) ስለሚል በችኮላ ወደ መዳን ይመጣል፡፡ የመዳን ነገር ጊዜ የማይሰጠውና በችኮላ የሚከናወን ነው፡፡ መዳን ከተገኘ በኋላ ደግሞ የተገኘው መዳን ምን ያህል አስደናቂ እንደሆነ መረዳቱ ይበልጥ እያደገ ያንን መዳን እስከመጨረሻ አጽንቶ በመያዝ መዳን እንደሚቻል ይኼኛው የመጽሐፍ ክፍል በስፋት ያብራራል፡፡