
ጸሃፊ፡- ፓስተር ኤልያስ ሽባባው (seeliyahu@gmail.com)
የታተመበት ቦታና ዓ.ም.፡- 2008 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ
አሳታሚ፡- የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን፣ ፖ.ሳ.ቁ. 4442፣ ስልክ 251-114-660086
አታሚ፡- ሪላ አታሚዎች የገጽ ብዛት፡- 347
መጽሐፉ በአስራ አምስት ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበ ነው፡፡ መጽሐፉ የጥናታዊ ጽሁፎች መድብል አይነት ሲሆን በርካታ ቁምነገሮችን ያዘለ ነው፡፡ በምዕራፍ ሁለት ላይ የሥላሴን ትምህርት ብዥታዎች ነቅሶ ያወጣና በምዕራፍ ሦስት ላይ የሥላሴ አማንያን ‹‹ሥላሴ›› ምንም እንኳ ሦስትነትን ቢገልጽም አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አናመልክም ቢሉም የተለያዩ የእምነቱ አስተማሪዎች የጻፏቸውን መጻሕፍት በማጣቀስ እምነቱ በሦስት አማልክት ወደማምለክ እንደሚስባቸው በዝርዝር ያቀርባል፡፡
ምዕራፍ አራት እና ምዕራፍ አምስት በአረማውያን አስተምህሮ ውስጥ ያሉትን የትምህርተ ስሉስ አይነቶችን ይዘረዝራሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የባቢሎናውያን ሥሉስ፣ የአሶራውያን ስሉስ፣ የግብጻውያን ሥሉስ፣ የግሪኮች ሥሉስ፣ የሮማውያን፣ የሂንዱ፣ የቡድሂዝም፣ የስዊድን፣ የቻይና፣ የፋርስ፣ የጃፓን፣ የሽንቶ፣ የሜክሲካውያን፣ የአይሪሽ፣ የብሪታንያ፣ የዓረብ ሴት እና ሌሎች የአረማውያን የሥሉስ አምልኮ አይነቶች ይገኙበታል፡፡ ታዋቂው የግሪክ ፈላስፋ ፕሌቶም የአረማውያን ሥላሴ ትምህርት አባት እንደሆነ በማስረጃ ተደግፎ ቀርቦአል፡፡
የመጽሐፉ ዋና ርዕሰ-ጉዳይ በክርስትናው ዓለም ያለው የትምህርተ ሥሉስ አስተምህሮ ከእንደነዚህ አይነት የአረማውያን አስተምህሮዎች ሾልኮ የገባ እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ ያለው አለመሆኑን በማሳየት ሰዎች ነፍሳቸውን እንዲያድኑ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው አንድ ብቸኛ አምላክ ብቻ እንዳለ እንዲረዱና እንዲያምኑ ለመርዳት ነው፡፡ ስለሆነም የአረማውያን አስተምህሮ በክርስትና ላይ ያሳደራቸውን ተጽዕኖዎች፣ ሥላሴ በክርስትናው ዓለም እንዴት እንደተከሰተ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ አንድ ብቸኛ አምላክ ብቻ በግልጽ እንደሚያስተምር፣ በምድር ላይ ሥላሴ የማይታመንበት ጊዜ እንደሚመጣ፣ የመጽሐፉ ጸሃፊ ደግሞ ለምን በሥላሴ እንደማያምኑ ያስቀመጧቸው 101 ምክንያቶች እና ሌሎችም ከርዕሱ ጋር የተያያዙ በርካታ አስተማሪ ቁም ነገሮች ተካትተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ቢሾፕ ደጉ ከበደ በመቅድሙ ላይ ‹‹መጽሐፉ በሽፍንፍን የሰውን አዕምሮ አስረው የያዙ መልስ አይገኝላቸውም የተባለላቸውን ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ሰው ማየት ያለበትን እንዲያይ ያስችላል የሚል ብርቱ እምነት አለኝ›› በማለት ጽፈዋል፡፡