ዋራ-ቤቴል 2013

የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ዓመታዊ ጉባኤዎችን ከምታደርግባቸው (የዳስ በዓላት) አንዱ የዋራ ጉባኤ ነው። በብዙዎች ዘንድ እጅግ ከባድና አስጨናቂ ተደርጎ በሚቆጠረው አሁን ባለንበት ዘመን ቤተክርስቲያን ወትሮ ከምታካሂደውና ቅዱሳንን ከሚያሳትፈው ጉባኤ በተለየ በተመጠነ ቁጥር ጉባኤውን አካሂዳለች። ቃሉ “. . .ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ዘንድ የዳስ በዓልንም ያከብሩ ዘንድ በየዓመቱ ይወጣሉ” ዘካ. 14፥16 እንደሚል ወራት ለወራት ቀናትም ለቀናት ተራ ሰጥተው የዘንድሮው ዋራ ቤቴል ጉባኤ ጊዜ ደረሰና የጉባኤው ታዳሚዎች በዋራ ተገኙ።

 

መጋቢት 04/2013 ዓ.ም ጠዋት 3፡00 የቤተክርስቲያኒቱ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት፤ ከመላው ሃገሪቱ በሚባል ደረጃ የሰበካ፣ የቅርንጫፍ ሰበካና የንዑስ ሰበካ ሃላፊዎች፣ በዚህ ዓመት የክህነትና የስብከት ፈቃድ የሚቀበሉ 634 አገልጋዮች በዋራ ተገኝተዋል። በዚሁ ቀን ጠዋት ቢሾፕ ጌታሁን ላምቤቦ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ዋና ፀሃፊ የጉባኤውን መጀመር ለማብሠር ከመዝሙር ዳዊት መጽሐፍ ምእራፍ 111፥1 በማንበብ ሃሌሉያ በሚል ከፍተኛ ድምጽ አስተጋብተው ጉባኤውን ከፈቱ።

በመቀጠልም ተከታታይ የአምልኮ መዝሙሮች ተዘምረው ጉባኤው በአምልኮ እሳት ተቀጣጠለ። ከዘፍጥረት 28፥3-4 እና ከዘፍጥረት 48፥3-4 ያለውን ቃል አንብበው ጊዜውን ለቢሾፕ ደጉ ከበደ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ሰጡ። ቢሾፕ ደጉ ከበደም ስለ 2012 ዓ.ም የዋራ ጉባኤ በማስታወስ ስለሃገራችን ሰላም፣ ስለኮሮናው፣ ስለአንበጣው ሁሉ የእግዚአብሔር ምህረትና ስራ በማድነቅ አመሰገኑ። በመቀጠልም በዚህ ጉባኤ አግዚአብሔር አጅግ የከበረና ታላቅ የዓለምን ገጽታ ሊለውጥ የሚችል ስራ እንደሚሰራ እምነታቸውን በመግለጽ በጉባኤው መጀመሪያ “አቤቱ ማረን ስለበደላችንና ስለሃጢኣታችን ይቅር በለን” ሲሉ በመንፈስ ቅዱስ መቃተት ፀለዩ፤ ጉባኤውንም አፀለዩ። የቅዳሜው ጠዋት የመጀመሪያ መልእክት ለሰበካ፣ ለንዑስ ሰበካና ለሚቀቡ አዲስ አገልጋዮች የትምህርት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ በዝርዝር ለአገልጋዮች ሁሉ የሚጠቅም መሰረታዊ ትምህርት ቀርቦ ጉባኤው በጥልቀት ታድሶአል፣ ታንጾአልም። በተጨማሪም የበረከታችን ምንጭ ስለሆነው ስለወንጌል ፍቅር ሊኖረን እንደሚገባ በአጽንኦት ተሰብኮ በምስጋና የጠዋቱ ፕሮግራም ተጠናቆአል።

አዲስ አበባ

በአዲስ አበባ ሰበካ በምሥራቅ ንዑስ የኮተቤ አጥቢያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን የፀሎት ቤት ምረቃ ተካሄደ። ባሳለፍነው ጥር 15/2013 ዓ.ም በተካሄደው የፀሎት ቤት የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ቢሾፕ ደጉ ከበደ፣ የአዲስ አበባ ሰበካ ሃላፊ ቢሾፕ ተረፈ ፈካ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ በሰበካው የሚገኙ የየአጥቢያው መጋቢዎች፣ ምዕመናንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በደማቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ምረቃው ተካሂዷል።

 

ወላይታ ሶዶ – ገንደባ

በኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን የወላይታ ሰበካ ዓመታዊ ጉባኤ ከየካቲት 04-07/2013 ዓ.ም በገንደባ ቤቴል የመሰብሰቢያ ስፍራ ተካሂዷል። በጉባኤው ቢሾፕ ተረፈ ፈካ የአዲስ አበባ ሰበካ ሃላፊና የሃገረስብከቱ ስራ አስፈጻሚ አባል፣ ቢሾፕ ጌታሁን ላምቤቦ የሃዲያ ሰበካ ሃላፊና የሃገረ ስብከቱ አስተዳደር ዋና ፀሐፊ፣ ወንጌላዊ ቴዎድሮስ አልታዬ፣ ወንጌላዊ ሰሎሞን ከበደ ተገኝተው የጊዜውን ቃል መልዕክት በማቅረብ ለጉባኤው መነቃቃትና በረከት ሆነዋል። ባቀረቡትም መልዕክቶች እጅግ ብዙ ሰዎች የመንፈስ መፈታት በንስሐ የመታደስና በአምልኮ የመነቃቃት ዕድል ተቋዳሽ ሆነዋል። ጉባኤው የበረከት ጉባኤ ሆኖ የተጠናቀቀ ሲሆን ከ61 ሰዎች በላይ ንስሐ ገብተዋል፣ ከ90 ሰዎች በላይ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለሐጢአታቸው ስርየት ተጠምቀዋል። እጅግ ብዙ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በሐዋርያት እምነት ላይ ተጨምረዋል።

ከምባታ ጠምባሮ

በከምባታ ጠምባሮ ቅርንጫፍ ሰበካ የሰረራ አጥቢያ ፀሎት ቤት ምረቃ ተካሄደ። ባሳለፍነው ሚያዚያ 10/2013 ዓ.ም በተካሄደው የፀሎት ቤት የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ቢሾፕ ደጉ ከበደ፣ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ቢሾፕ ኢሳያስ አሻ፣ ቢሾፕ አንዱአለም ብርሃኑ፣ ቢሾፕ ጌታሁን ላምቤቦ የቅርንጫፍ ሰበካው ሃላፊ ቢሾፕ ተከተል አብዮ፣ በቅርንጫፍ ሰበካው የሚገኙ የየአጥቢያው መጋቢዎች፣ ምዕመናንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በደማቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ምረቃው ተካሂዷል።

መቂ

በኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በምሥራቅ ሸዋ ንዑስ የመቂ አጥቢያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ጉባኤ ከሐምሌ 9-10/2013 ዓ.ም በመቂ ከተማ ተካሂዷል። ጉባኤው የበረከት የሃይልና የመነቃቃት ጉባኤ የነበረ ሲሆን የቤተክርስቲያኒቱ ተማሪዎችና ወጣቶች የእውነትን ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ ለማዳረስ በከተማው ውስጥ በመዘዋወር ከ 6,200 በላይ ትራክቶችን ለነዋሪዎቹ እጅ በእጅ አድርሰዋል። ከዚሁ ትራክትን የማሰራጨት እንቅስቃሴ በተጓዳኝ የከተማው ነዋሪዎች ወደጉባኤው እንዲመጡ በመጋበዝ ብዙዎች እንዲታደሙ አድርገዋል። በጉባኤው የወላይታ ሰበካ ሃላፊ ቢሾፕ ብርሃኑ ዲጂቆ እና የአዲስ አበባ ሰበካ የወንጌል ስርጭት ክፍል ሃላፊ ቄስ ኤልያስ ሽባባው ተገኝተው ባቀረቧቸው መልእክቶች የብዙዎች ልብ ተነክቶ 36 ሰዎች ለሐጢአታቸው ስርየት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠምቀዋል፤ ብዙዎች በመንፈስ ቅዱስ ተጎብኝተዋል።

ሐዋሳ

በሐዋሳ ቅርንጫፍ ሰበካ እናት አጥቢያ ከሐምሌ 9-10/2013 ዓ.ም የበረከት እና የምስጋና ኮንፍራንስ ተካሄደ። በኮንፍራንሱ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ቢሾፕ ደጉ ከበደ የተገኙ ሲሆን ታላቅ የበረከት ጊዜ ሆኖ 37 አዳዲስ ነፍሳት ወደ ኢየሱስ መጥተዋል። 13ቱ መንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሲሆን 1 ሰው ከአጋንንት እስራት ተፈቷል፤ ሁለት ነፍሳት በንሰሐ ወደ አምላካቸውና ወደ ቤተክርስቲያን ተመልሰዋል። በ 2065 ካ.ሜ ላይ ያረፈውና ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ፈጅቶ ግንባታው 80% የደረሰው የሐዋሳ እናት አጥቢያ ጸሎት ቤት የፊኒሺንግ ስራው ሲጠናቀቅ እንደሚመረቅ የሰበካው ሃላፊ እና የአጥቢያው መጋቢ ቢሾፕ ሞላ ቤዳሞ አስታውቀዋል።

Scroll to Top