በቢሾፕ ኢሳያስ አሻ

የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ም/ዋና አስተዳዳሪ

1ኛቆሮ.13 ላይ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል መልዕክት፡- ‹‹እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው›› ይላል፡፡ የቃሉ መልዕክት ዋናው ትኩረት ፍቅር ላይ ቢሆንም ሦስቱም ነገሮች ጸንተው ሊኖሩ እንደሚገባ ጥቅሱ ያረጋግጣል፡፡

ከምዕመናን ሕይወት ውስጥ እምነትን÷ ተስፋንና ፍቅርን ሊያጠፉ የሚችሉ ሁኔታዎች በቀደሙት ዘመናት ሁሉ የነበሩ ቢሆንም የመጨረሻው ዘመን ሁኔታዎች ግን የባሱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሦስቱ ነገሮች በሕይወታችን ጸንተው እንዲኖሩ ያስፈልጋል፡፡

እምነት እንዳይጠፋብን !

ዕብ.11÷1 ላይ፡- ‹‹እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ÷ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው›› ይላል፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ የሰጠንን ተስፋ ሁሉ የምንረዳው÷ የምናረጋግጠውና የምናገኘው በእምነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሊሰጠን ያለውን ማናቸውንም ነገር ልንቀበል የምንችለው እግዚአብሔርንና ቃሉን ስናምን ነው፡፡

የነፍስ መዳን የሚገኘው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በማመንና በስሙ በመጠመቅ ነው (ማር.16÷16፣ የሐዋ.ሥራ 2÷38)፡፡

የሕይወት ውኃ ወንዝ ሆኖ የሚፈልቀውን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መቀበል የሚቻለው በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን ጋር በሆነ መጠማት ነው (ዮሐ.7÷37-39)፡፡

እግዚአብሔር የሰጠንን የተስፋ ቃል በሙላት መቀበል የምንችለው ፈቃዱን እያደረግን በእምነት ጸንተን መኖርን ስንቀጥል ነው፡፡ ከእምነት ወደ ኋላ ብናፈገፍግ እግዚአብሔር ደስ አይለውም (ዕብ.10÷36-39)፡፡

ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትና ከእግዚአብሔር ዋጋ ማግኘት አይቻልም (ዕብ.11÷6)፡፡

የምዕመናን እምነት ሊጠፋ የሚችለው በሚገጥማቸው ልዩ ልዩ ፈተና÷ መከራና ችግር ምክንያት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል ማግኘት የሚቻለው ደግሞ በፈተና÷ በመከራና በችግር ውስጥም ሆኖ በእምነት ጸንቶ በመኖር ነው፡፡ ፈተና ÷ መከራና ችግር ሁሉም ሰው ይደርሰበታል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ታማኝ ስለሆነ ማንንም ከሚችለው በላይ እንዲፈተን አይፈቅድም÷ ደግሞም ከፈተናው ጋር መውጫውን ያዘጋጃል (1ኛቆሮ.10÷13)፡፡

ፈተና÷ መከራና ችግር ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን እምነታችንን የሚፈትን እንጂ የሚያጠፋን አይደለምና እምነት አይጥፋብን (1ኛጴጥ.1÷6-9፣ 4÷12-16፣ 5÷10)፡፡

ተስፋ እንዳይጠፋብን !

በብሉይ ኪዳንም በአዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር ስለ ሰጠን ተስፋና የተስፋ ቃል በዚህ አጭር ጽሁፍ በስፋት መዳሰስ ስለማይቻል ተስፋ እንዳይጠፋብን የምታሳስብ ጥቂት ነገር ብቻ ለማለት ተሞክሮአል፡፤

ዕንባቆም 2÷3 ላይ ከተጻፈው ቃል ስንገነዘብ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ ራዕይ ወይም እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋ ቢዘገይ እንኳ እስከተወሰነው ጊዜ ነው እንጂ መፈጸሙ ስለማይቀር በእምነትና በትዕግስት እንጠብቀው እንጂ በመዘግየቱ ምክንያት ተስፋ እንቁረጥ፡፡

አብርሃም የአሕዛብ አባት እንዲሆን እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ይዞ አመነ (ሮሜ.4÷18)፡፡ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ (በአዲስ ኪዳን ዘመን ላለነው ለእኛም) የሰጠው የመባረክና የመብዛት ተስፋ ቃል በእግዚአብሔር በኩል በመሐላ የተረጋገጠ ሲሆን በእኛ በአማኞቹ በኩል ደግሞ ታግሠን የምናገኘው ነው (ዕብ.6÷11-15)፡፡

ምሳሌ 13÷12 ላይ፡- ‹‹የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች›› ይላል፡፡ ቃሉ እውነት ነው ማንም ተስፋው ሲዘገይበት ያዝናል፡፡ ነገር ግን ተስፋ መቁረጥ አይገባም፡፡ሐዋርያው ጳውሎስ በ 2ኛ.ቆሮ.4÷8 ላይ በጻፈው መልዕክት፡- ‹‹በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም›› እንዳለው በምንም ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆን እግዚአብሔርንና ቃሉን ተስፋ ማድረግ አይጥፋብን፡፡

ፍቅር እንዳይጠፋብን!

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍቅር የሚያስተምረው ትምህርት በጣም ሰፊና ጥልቀት ያለው በመሆኑ በዚህ አጭር ጽሁፍ መግለጽ አይቻልም፡፡ በዚህ ጽሁፍ የቀረበው ፍቅር ከእምነት ከተስፋም የሚበልጥ ስለሆነ ከሕይወታችን ሳይጠፋ ጸንቶ እንዲኖር የሚያስፈልግ እጅግ በጣም አንገብጋቢ ነገር ስለመሆኑ ነው፡፡ፍቅር ለነፍሳችን መዳንና ለዘላለም ሕይወት ወራሽነት ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱና ወሳኙ ነው፡፡

አንዱን እውነተኛ አምላክ በፍጹም ፍቅር መውደድና ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ከትዕዛዛቱ ሁሉ የሚበልጠውን መፈጸም፣ በሙሉ ከሚቃጠል መስዋዕትና ከሌላው መስዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው (ማር.12÷ 28-34)፡፡ የዘላለምን ሕይወት መውረስ የሚቻለውም ይህ ፍቅር ያለው በመሆን ነው (ሉቃ.10÷25-28)፡፡

ትዕዛዝ ሁሉ በፍቅር ተጠቅልሎአል፤ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው (ሮሜ 13÷8-10)፡፡ ጌታ አምላክን የሚወድድ ትዕዛዛቱን ሁሉ ይጠብቃል (ዮሐ.14÷15)፡፡ ባልንጀራውን እንደ ራሱ የሚወድድ ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፡፡

በልሳናት መናገር፣ ትንቢትን መናገር፣ ምሥጢርን ሁሉና እውቀትን ሁሉ ማወቅ፣ ተራሮችን የሚያፈልስ እምነት ያለው መሆን ፣ ድሆችን ለመመገብ ያለውን ሁሉ ማካፈል፣ ወዘተ… ያለ ፍቅር ከሆነ ከንቱ ይሆናል (1ኛቆሮ.13÷1-3)፡፡

ፍቅርን ሊያቀዘቅዝና ሊያጠፋ የሚችለው ትልቁ ፈተና የዓመጻ ብዛት ነው (ማቴ.24÷12)፡፡ ፍቅር ከውስጣችን እንዳይጠፋ ሊያደርግ የሚችለው ደግሞ እግዚአብሔር በመንፈሱ  በውስጣችን መኖር ነው (ሮሜ.5÷5፣ 1ኛዮሐ.4÷7-12)፡፡

ስናጠቃልል በእምነት፣ በተስፋና በፍቅር እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል፤ የተስፋውንም ቃል ይወርሳል (ማቴ.24÷13፣ ዕብ.6÷9-15)፡፡

ሁላችንንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጸጋው ይርዳን፤ አሜን፡፡

Scroll to Top