ወንድም ኢዮቤድ ሰለሞን

የሰው ፍጥረት ከአዳም ጀምሮ በውስጡ ያለውን ምኞት ወይም ሃሳብ ለማሳካት ብዙ አይነት መንገዶችን ይመርጣል፤ ይጠቀማል። አዳምና ሔዋን ዓይኖቻቸው እንዲከፈቱ መልካምና ክፉውን እንዲያውቁ (ዘፍ. 3)፣ ቃየን የእርሱ መስዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲታይና ተቀባይነትን እንዲያገኝ (ዘፍ. 4)፣ ከጥፋት ውሃ በኋላ በሰናዖር የተቀመጡት ስማቸውን ለማስጠራት (ዘፍ. 11) የተከተሉት እግዚአብሔራዊ ያልሆኑ መንገዶች ነበሩ።

ሰዎች በህይወታቸው መድረስ የሚፈልጉበትን ቦታ ለመሄድ የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ። በዚህ አማራጭ ፍለጋ ውስጥ መደበኛውን ሂደት መከተል አሰልቺ፣ ቀርፋፋ እና ተስፋ አስቆራጭ የሚመስልበትም የሚሆንበትም ጊዜ አለ። ታዲያ መንገድ ሁሉ ትክክለኛና እግዚአብሔራዊ አይደለምና “ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች። ፍጻሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው።” (ምሳሌ 14፥12) የሚለውን ምክር ማስተዋል ያስፈልጋል።

እግዚአብሔርን ለሚፈሩት፣ ለሚወዱት ደግሞም እንደ ሃሳቡም ለተጠሩት ግን እርሱ የመረጣት ቅን፣ ንጹህ እና ፍፁም የሆነች መንገድ አለች። ቃሉ “የአምላኬ መንገድ ፍጹም ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው።” (መዝ. 18፥30) ይላልና።

መጽሐፍ ቅዱሳችን በመዝ. 37፥7 “ለእግዚአብሔር ተገዛ ተስፋም አድርገው። መንገድም በቀናችለትና ጥመትን በሚያደርግ ሰው አትቅና።” ይላል። አሁን ያለንበት ዘመን ሰዎች የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት ብዙ አቋራጮች የሞሉበት ጊዜ ነው። ለምሳሌ ሰዎች በአጭር ጊዜ ብዙ ሃብት ለማግኘት ጉቦ፣ የተለያዩ ዓይነት ቁማሮች፣ ኮንትሮባንድ፣ ሃሰተኛ ነብያት፣ ጥንቆላ አልፎም አካልን ስጋን እስከመሸጥ ይደርሳሉ። ለፈውስ ከበሽታ፣ ከኃጢያት ወይም ከሱስ ለማምለጥ ማይገባ ቦታ ይገኛሉ። ለስራ ከመወዳደር ይልቅ ዘመድን መመልከት፣ ታዋቂነትን ለማትረፍ በየሶሻል ሚዲያው ሲለምኑ መዋል፣ ብዙ እህል ለማምረት ወይም ያለ አግባብ የደለቡ የእንስሳት ርቢን ለማግኘት ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ኬሚካሎችን ይጠቀማሉ። እውነተኛውንና መንገድ ከመጠቀም ይልቅ አቋራጭ መንገድ ይመረጣል። በዚህም መንገድ የተሳካላቸው ሚመስሉ ሰዎችን ደግሞ ስንመለከት በነዚህ አቋራጭ መንገዶች በቀላሉ እንማረካለን። ነገር ግን መዝሙረ ዳዊት 37፥9 “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ።” ይላል።

ማቴ. 4፥1 ጀምሮ እንደምናገኘው ዲያቢሎስ አዳም ላይ እንደለመደው የተለያዩ አቋራጮችን ለኢየሱስ ይዞ ሲመጣ እናየዋለን። ለርሃብ ድንጋዩን ዳቦ ማድረግ፣ “በቤተ መቅደስ ዙሪያ ያሉት ሰዎች ለማሳመን የመጣህበት ዓላማ ሰዎችን በአንተ አምነው እንዲድኑ ከሆነ ከመቅደስ ጫፍ ራስህን ወርውር። ከዚያ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል።” እያለ የመጣህበትን ዓላማ በቀላሉ አሳካ የምን መሰቀል የምን መከራን መቀበል ነው እያለ ሲሞግተው ይህም አልሳካ ሲል “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህንን ያሳየሁህን ሁሉ ሃብት እሰጥሃለው” ሲለው እንመለከታለን። ጌታ ኢየሱስ ግን መከራ ያለበትን እውነተኛውን መንገድ መረጠ፤ በዚህም ዓለምን አዳነ። ቃሉ ይህንን ሲመሰክር “ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ።” (ዕብ.5፥8)፤ “ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል። ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና።” (ኢሳ. 53፥12) ይላል።

በእስራኤል ያልተደረገ ተሰምቶ ማያቅ የዘመኑ ሰው ‘brand new’ እንደሚለው ዓይነት ኃጢያት መስራት ፉክክር ውስጥ በገባበት ጊዜ (“የዘንበሪም ልጅ አክዓብ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም ኃጢአት መሄድ ታናሽ ነገር መሰለው፥” (1 ነገ 16፥30)) በዚያኑ ጊዜ እግዚአብሔር ኤልያስን ሊገልጠው ፈለገ። እግዚአብሔር በኤልያስ ህይወት ለመግለጥ የፈለገውን ነገር በጊዜው እስኪገልጠው ድረስ አስቀድሞ መሸሸግ ነበረበት።

“ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፥ በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ።” (1ኛ ነገ. 17፥3)። ምንም እንኳ ኤልያስ ከቁራ አፍ ሥጋ የመብላት ጸጋ እየሰራበት ቢሆንም እንኳ በእግዚአብሔር አሰራር ሰው ጸጋ ስላለው ብቻ ወደ አደባባይ ይወጣል ማለት አይደለም። ብቻውን ከእግዚአብሔር ጋር ማንም ሳያየው የሚያሳልፈው ጊዜ ያስፈልገዋል።

ቀጥሎ ኤልያስ ያሳለፈው የህይወት ክፍል መቀመጥ ነበር። “ተነሥተህም በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፥ በዚያም ተቀመጥ።” (1ኛ ነገ. 17፥8)። ሰዎች በዚህ ዘመን እጅግ ጥቂት ነገራቸውን ለማሳየት በሚጣጣሩበት በዚህ ዘመን ትልቅ ትምህርት ሚሰጠንን ነገር እግዚአብሔር ለኤልያስ ሲያዘው እናያለን። ለ3 ዓመት የተጠጋ ጊዜን ዱቄት እና ዘይትን የማባዛትን የመሰለ እጅግ ድንቅ የሆነ ተዓምር በእጁ እየተካሄደ ነገር ግን ያንን ጸጋ ከሁለት ሰዎች ጋር ለዛውም ማንም በማያይበት ቦታ ተቀመጥ የሚልን ድምጽ ሰምቶ የሚቀጥለውን የእግዚአብሔርን ምሪት ሲጠብቅ ነበር።

በስተመጨረሻም የእግዚአብሔር ዓላማ ሚፈጸምበት፣ የበዓል አምልኮ የሚዋረድበት፣ ነቢያቶቹም ሚታረዱበት፣ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር እርሱ ብቻ አምላክ እንደሆነ ኤልያስም ደግሞ የእርሱ ባሪያ እንደሆነ ለእስራኤል ሁሉ ሚገለጥበት ጊዜ መጣ። ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ዓለማ እርሱ አምላክ እንደሆነ መግለጥ ቢሆንም ቀጥታ ግን ወደ መገለጥ አልሄደም፤ ኤልያስ ሊያልፍበት ሚገባው መንገድ ነበር። ተሸሸግንና ተቀመጥን ካለፈ በኋላ ነው ተገለጥ የተከተለው። “ከብዙ ቀንም በኋላ በሦስተኛው ዓመት። ሂድ፥ ለአክዓብ ተገለጥ፥ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ።” (1ኛ ነገ. 18፥1)

አሁንም በዚህ ዘመን ላለን ትውልድ ትልቅ ትምህርት የሚሆነን እግዚአብሔር ምንም ትልቅ ነገር በማናቸውም ሁኔታ በእኛ ቢያስቀምጥ ጊዜው እስኪደርስ ተሸሸግና ተቀመጥ የሚሉት መንገዶች እንደማይቀሩ፤ ያለዚያ ጊዜው ሳይደርስና ሳይበስል እንደተቀጠፈ አትክልት ጣዕም የሌለን እንድንሆን ያደርገናል።

Scroll to Top