በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ለምትገኙ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናንና አገልጋዮች፤ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ ሰላምና በረከት ይብዛላችሁ፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል የምናስተላልፈው ይህ መልዕክት በያላችሁበት ይድረሳችሁ፤ እናንተ ደግሞ ለሌሎች አስተላልፉት፡፡
የእኛ አኗኗርና አካሄድ ስለ እኛ እንደተጻፈው ይሁን
ወንድሞችና እህቶች፡- በእግዚአብሔር ቃል ስለ እኛ የተጻፈው የእኛን ማንነት፣ ከእኛ የሚጠበቀውን አካሄድና አኗኗር ከሌሎች የተለየ ያደርጋል፡፡ ሌሎች ልዩ ልዩ ወቅታዊ ሁኔታዎችንና የመጨረሻውን ዘመን የሚያስተናግዱባቸው የየራሳቸው አካሄድ አላቸው፡፡ እኛ ግን ሁኔታዎችንና ዘመኑን ማስተናገድ ያለብን በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ እኛ ማንነት፣ ስለሚጠበቅብን አኗኗርና አካሄድ እንደተጻፈው ነው፡፡ በገላ. 3፡26-29 ላይ ስለ እኛ ማንነት የተጻፈው “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና፡፡ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፤ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፤ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና፡፡ እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ፡፡” ይላል፡፡ በ2ኛ.ቆሮ.5፡17 ላይ ያለው ቃል፡-“ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል” ይላል፡፡
በዚህ መሠረት የእኛ የቀድሞ ማንነታችን ተለውጦ፣ ልዩነቶቻችንም ተወግደው፣ በክርስቶስ አዲስ ሰውና በአንድ አካል ያለን ብልቶች ተደርገናል፡፡ ስለዚህ እኛ መመላለስ የሚገባን ስለ እኛ እንደተጻፈው ነው፡፡
በ1ኛ.ጴጥ.1÷23 ላይ የተጻፈው እኛን “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም÷ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡” ይለናል፡፡ እንዲሁም በ1ኛ.ጴጥ.2÷9-10 ላይ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ÷ የንጉሥ ካህናት÷ ቅዱስ ህዝብ÷ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምህረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምህረትን አግኝታችኋል፡፡”ይለናል፡፡
ስለዚህ ከእኛ የሚጠበቀው እንደ ተመረጠ ትውልድ፣ እንደ ንጉሥ ካህናት፣ እንደ ቅዱስ ሕዝብ፣ እንደ እግዚአብሔር ወገን ስለ እኛ እንደተጻፈው አካሄድ መኖር ነው፡፡
የምንኖርበት ዓለም በልዩ ልዩ ነባርና አዳዲስ ክስተቶች የተሞላ ነው፡፡ አሁን ያለንበትና የሚመጣው ዘመን በእግዚአብሔር ቃል ስለዘመኑ የተጻፈው ሁሉ በየተራው የሚፈጸምበት ነው፡፡ በእነዚያ ክስተቶችና በዘመኑ ሁኔታዎች መካከል እኛ መኖርና መመላለስ የሚገባን እንደ ሌሎች እና እንደ ሁኔታዎቹ እየተለዋወጥን ሳይሆን ስለ እኛ እንደተጻፈው ነው፡፡
በማቴ.5÷13-16 የተጻፈው “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ… እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ….. መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡” ይለናል፡፡
ስለዚህ አካሄዳችን፣ አኗኗራችንና ተግባራችን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለሰዎች የሚገልጥ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በፊል.2÷14-16 የተጻፈው “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጎራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ….” ይለናል፡፡ ስለዚህ ከእኛ የሚጠበቀው ስለ እኛ እንደተጻፈው መኖር ነው፡፡
እኛ በኤፌ. 5÷8-10፤ ከቁጥር 15-17 እንደተጻፈው እንመላለስ፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ እኛ ደግሞ የብርሃን ልጆች ነን፡፡ እኛ ስለ እኛ እንደተጻፈው ለጌታችን ደስ የሚያሰኘውን እየመረመርን እንደ ብርሃን ልጅነታችን እንመላለስ፡፡ እንዲሁም እኛ ይህን የመጨረሻውን ዘመን እንዋጀው፡፡ እኛ ዘመኑን እንቆጣጠረው እንጂ ዘመኑ እኛን አይቆጣጠረን፡፡ እኛ ዘመኑን እንግዛው እንጂ ዘመኑና የዘመኑ ሁኔታዎች እኛን አይግዙን፡፡
ይህ የመጨረሻው ዘመን ሁለት ገጽታዎች ያሉት ነው፡፡ አንዱ የዘመኑ ገጽታ በኢሳ. 60÷1-3 እና በማቴ.24÷ 3-14 እንደተጻፈው ምድርን ድቅድቅ ጨለማ የሚሸፍንበትና ብዙ የሚያሰምጡ ክስተቶች የሚፈጸሙበት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእግዚአብሔር መንግስት ወንጌል በዓለም ሁሉ የሚሰበክበት ነው፡፡
አንዱ መጥፎና ፈታኝ ገጽታ ሲሆን ሁለተኛው እጅግ በጣም ደስ የሚያሰኝ ብዙ የእግዚአብሔር ተስፋ ቃሎች የሚፈጸሙበት ገጽታ ነው፡፡ ስለዚህ እኛን የዘመኑ ክፉና ፈታኝ የሆነው ገጽታ ሊገዛን አይገባም፤ ይልቁንስ እኛ የእግዚአብሔርን ተስፋ ቃሎች ይዘን ለእኛ እንደሚገባን እየተመላለስን ዘመኑን መግዛት ይገባናል፡፡ እኛ ይህን የመጨረሻውን ዘመን መዋጀት የምንችለው ስለ እኛ እንደተጻፈው በመመላለስ መኖር ስንችል ነው፡፡
ዘመኑ ከእንቅልፍ የምንነሳበትና በአግባብ የምንመላለስበት ነው (ሮሜ 13÷11-14)፡፡
ዘመኑ መንቃት ያለብንና በመጠን መኖር ያለብን ነው (1ተሰ.5÷1-8)፡፡
ዘመኑ የጌታ ቀን ድንገተኛ እንዳይሆንብን የምንጠነቀቅበትና ሁልጊዜ በጸሎት መትጋት ያለብን ነው (ሉቃ.21÷34-36)፡፡
ዘመኑ የሚያስቱ መናፍስትና የአጋንንት ትምህርት የበዛበት በመሆኑ እኛ በመልካም ትምህርት መጋቢነት መትጋት ያለብን ነው (1ጢሞ.4÷1-6)፡፡
ዘመኑ እኛ እግዚአብሔርን ለመምሰል መትጋት ያለብን ነው (1ጢሞ.4÷7-10)፡፡
ዘመኑ ራሳችንንም የሚሰሙንንም ለማዳን ለራሳችንና ለትምህርታችን መጠንቀቅ ያለብን ነው (1ጢሞ. 4÷11-16)፡፡
ዘመኑ ለአስጨናቂነቱ ምክንያት ከሆኑት ክፉ ሰዎችና ከአካሄዳቸው መራቅ ያለብን ነው (2ጢሞ.3÷1-5)፡፡
ዘመኑንና ሁኔታዎችን በድል አድራጊነት ለመሻገር እኛ ስለ እኛ እንደተጻፈው እየተመላለስን እንኑር፡፡ ለሁኔታዎች በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ተገቢውን ምላሽ እንስጥ፡፡
- በመዳን ትምህርታችን እንጽና (2ጢሞ.3÷14-17)፡፡
- የእግዚአብሔር ሰዎችን መልካም ምሳሌነት እንከተል (2ጢሞ.3÷10-12)፡፡
- ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አንጠመድ (2ቆሮ.6÷14-18)፡፡
- እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በልባችን መታደስ እንለወጥ እንጂ ይህን ዓለም አንምሰል (ሮሜ 12÷2)፡፡
- ምን እንድንሰማ እንጠበቅ፤ ለራሳችንም እንጠንቀቅ (ማር.4÷24፣ ሉቃ. 21÷25-36)፡፡
- እኛ በክስተቶች አንፍራ÷ አንጨነቅ፤ ይልቁንስ ሊመጣ ካለው ሁሉ ለማምለጥና በጌታችን በኢየሱስ ፊት ለመቆም እንድንችል ሁልጊዜ በጸሎት እንትጋ (ሉቃ.21÷25-26)፡፡
በማቴ.24÷12 የተጻፈው የመጨረሻው ዘመን የዓመፃ ብዛት ፍቅራችንን እንዳያቀዘቅዝብን እንጠንቀቅ፡፡ እኛ ስለ እኛ እንደተጻፈው እናድርግ፡፡
- እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንት ሁሉ ሳንታክት እንጸልይ (1ጢሞ.2÷1-2)፡፡
- በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣናት በአገባቡ እንገዛ (ሮሜ 13÷1-7)፡፡
- ክፉውን ነገር እንጸየፈው፤ ከበጎ ነገር ጋር እንተባበር (ሮሜ 12÷9)፡፡
- ቢቻለን ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንኑር (ሮሜ.12÷18)፡፡
- ጊዜ ካገኘንና መልካም ማድረግ ሲቻለን ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተሰዎች መልካም እናድርግ (ምሳ.3÷27-28፣ ገላ.6÷10)፡፡
- ድሆችን እናስብ (ገላ.2÷10)፡፡
- ወላጆች የሌላቸውን ልጆችና ባልቴቶችን በመከራቸው እንጠይቅ (ያዕ.1÷27)፡፡
- ለተራቡትና ለስደተኛ ድሆች ከእንጀራችን እንቁረስላቸው (ኢሳ. 58÷7)፡፡
ለወቅታዊ ችግሮች በጊዜያዊ መፍትሔነት የሚወሰዱት ጊዜያዊ እርምጃዎች ስለ እኛ የተጻፈውን እንዳያዘናጉን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
ሁኔታዎች ቀስ በቀስ ወደ ነበሩበት እስኪመለሱም ሆነ ሙሉ በሙሉ ሲስተካከሉ እኛም ስለ እኛ እንደተጻፈው ልንኖርና ልንመላለስ ይገባናል፡፡
- ወቅታዊ ችግሮችን ለማለፍ ለሰዎችና ለመንግሥት ሥርዓት እንገዛ (1ጴጥ.2÷13-17)፡፡
- ወቅታዊ ችግሮች ሲያልፉ በዕብ.10÷25፣ በ1ቆሮ.16÷20 እንደተጻፈው በየአጥቢያዎቻችን፣ በየኮንፈረንሶቻችንና በየሥራ ስብሰባዎቻችን መሰብሰብን አንተው፤ በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችን ሰላምታ ወደ መሰጣጣትም እንመለስ፡፡
በልዩ ልዩ ክስተቶች፣ በወቅታዊ ችግሮችና በዘመኑ ሁኔታዎች ሳንወሰን ሃይማኖታዊ ተግባራቶቻችንንና ተልዕኮአችን ሳንታክት እንፈጽም፡፡
- በጊዜውም አለጊዜውም ቃሉን እንስበክ፣ ነገርን ሁሉ በልክ እናድርግ፣ አገልግሎታችንን እንፈጽም (2ጢሞ.4÷1-5)፡፡
- ከዕለታዊ ተግባሮቻችን ጋር ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም መምጣት ተዘጋጅተን እንኑር (ማቴ.24÷36-44)፡፡
- በተጠራንበት መጠራታችን እንደሚገባ እንመላለስ (ኤፌ.4÷1-16)፡፡
- ልባሞች ሆነን፣ መብራታችንን እያበራን፣ ከመብራታችን ጋር በመቅረዛችን ዘይት ይዘን፣ በተሰጠን ልዩ ልዩ መክሊት እየተጋን ነቅተንና ተዘጋጅተን እንኑር (ማቴ.25÷1-17)፡፡
- ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ (ዕብ.4÷14-16)፡፡
- መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት (2ተሰ.3÷6-13)፡፡
ዘመኑን እየዋጀን÷ በውጭ ባሉት ዘንድ በጥበብ እንመላለስ (ቆላ.4÷5)፡፡
እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንደምንመላለስ በጥንቃቄ እንጠበቅ (ኤፌ.5÷15)፡፡
ጌታም በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን፡፡ (2ጢሞ.2÷7)
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ለሁላችንም ይብዛልን፡፡ አሜን!!