ቢሾፕ ዘኬዎስ ሳፋይ | የአዶላ ቅ/ሰበካ ኃላፊ

የእግዚአብሔር ቃል በዕብ.10÷37-39 ላይ “ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፣ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፣ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም። እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።” ብሎ እንደሚናገር በዚህ ክፍል ውስጥ “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል” የሚለው ቃል አለመለዋወጥን፣ ስፍራን አለመልቀቅንና ሁልጊዜ በእምነት ጸንቶ መገኘትን የሚገልጽ ነው።

ችግርና መከራ ቢፈራረቁ፣ ፈተናም ቢበዛ፣ ብዙ የሚያናውጡ ነገሮች ቢከሰቱ ጻድቅ አይናወጥም፤ በእምነት ጸንቶ ይኖራል። ይህም ማለት ከሰማው መለኮታዊ ነገር፣ ከእግዚአብሔር ቤት፣ ከቅድስናውና ከመንፈሳዊ ሕይወቱ፣ አምላኩንም ከመከተልና ከማገልገል አይወሰድም፤ ሁልጊዜ እዚያው ይገኛል፣ አይጠፋም አለ ማለት ነው። ጻድቅ ዛሬም በእምነት ጸንቶ ይቆማል፤ ሊመጣ ያለውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ ወደ ፊትም በእምነት ይኖራል።

መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” [ዕብ. 11፥1] ይላል። በዚህ ቃል መሠረት ጻድቅ አሁን በስጋ አይን በሚታየው ተጨባጩ ዓለም ሳይሆን፤ አሁን በስጋ ዓይን የማይታየውን በመንፈሳዊ ዓለም ግን ያለውን መለኮታዊ ነገርን በእምነት በማየትና በመረዳት የሚኖር ነው። ስለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና” ብሎ በ 2ኛ ቆሮ. 5÷6 ላይ የተናገረው።

ሙሴም በዚህ እምነት ነበር የፈርዖንን ቁጣ ሳይፈራ የግብጽን አገር የተወው፣ ምክንያቱም “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።” [ዕብ. 11÷27]። በደረሰበት መከራና ስደት ስለ ክርስቶስ እጅግ መነቀፍ፣ ከእግዚአብሔርም ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን ወዘተ በአጠቃላይ በግብጽ ክፉ ተጽዕኖ ውስጥ ሙሴን ያጸናውና ያኖረው እምነት ነበር። ዛሬ እኛም በዚህች በክፉ በተያዘችና በተሞላች በአታላይዋ ዓለም ስንኖር በዓይናችን በምናየውና በጆሮአችን በምንሰማው እንዳንታለልና ከጽናታችን እንዳንወሰድ ብሎም በክፉ የዓለም ተጽዕኖ ስር እንዳንወድቅ ምንም አማራጭ የሌለው መንገድ በእምነት መኖር ነው።

ጻድቅ ዓለምን የሚያሸንፍበት ትልቁ መሳሪያው እምነት ነው። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው።” [1ኛ ዮሐ. 5÷4]። በተለይም አሁን እኛ ያለንበት ዘመን የመጨረሻው ዘመን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ክፉ ክስተቶች፣ የሐሰተኞች ነቢያት ከልክ በላይ መብዛት፣ መለኮታዊ ነገርን ማወሳሰብና ግራ ማጋባት፣ ራሳቸውን የጽድቅ አገልጋዮች ማስመሰል፣ የሰውን ደካማ ጎን እያጠኑ መስራትና በኢየሱስ ስም መነገድ፣ ጦርና የጦር ወሬ መስማት፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ መነሳት፣ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ፣ የዓመጻ መብዛትና የፍቅር መቀዛቀዝ፣ የሰዎች በዘረኝነት መንፈስ ተይዘው መለያየትና እርስ በርስ በጥላቻ መንፈስ መበላላት [ማቴ.24÷3-8] የማይታየውን ያየንበትን እምነት ከውስጣችን እንዳያጠፋና የእነዚህ ክፉ ክስተቶች ሰለባ እንዳንሆን ነቅተን የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን መያዝና መጠበቅ አለብን። “የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ÷ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና።” [ዕብ. 3÷14]ከፍ ብለን እንዳየነው በዚህ በመጨረሻው ዘመን እየተፈጠሩ ከሚታዩት አስጨናቂና ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ነገሮች ውስጥ ይድናል የተባለለት እስከ መጨረሻ የሚጸና ሰው ነው። [ማቴ. 24÷13]። ያለ እምነትም ጽናት የለም። “ባታምኑ አትጸኑም።” ይላልና [ኢሳ. 7÷9]።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃ. 18÷1- 8 በእምነትና በጽናት መጸለይ እንደሚገባ በአመጸኛ ዳኛና በአንዲት መበለት ምሳሌ ባስተማረው ክፍል ውስጥ የተናገረው አሳሳቢ ቃል “ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?” የሚለው ነገር በመጨረሻው ዘመን ከምድር እምነት እንደሚጠፋ አመላካች ንግግር ነውና ነቅተን እምነታችንን በውስጣችን እንጠብቅ።

እምነት እንደ ጀርባ አጥንት ሊቆጠር ይችላል። አንድ ሰው ወይም ሌላም እንስሳ ቢሆን ያለ ጀርባ አጥንት ቀጥ ብሎ መቆምና መሄድ እንደማይቻለው ሁሉ እንዲሁ ሰው በክርስትና ሕይወት ያለ እምነት ጸንቶ መቆምና መመላለስ አይችልም። አንድ ወገቡ ወይም የጀርባ አጥንቱ የተጎዳ ማንኛውም ሰው ወይም እንስሳ ሽባ እንደሚሆንና በሌላ አካል ድጋፍ እንደሚንቀሳቀስ እንዲሁ እምነት የሌለበትን ሕይወት ሰይጣን ወደ ፈለገው አቅጣጫ በራሱ አሰራር እያሽከረከረ ሊነዳው ይችላል። ምክንያቱም እምነት የሌለው ሰው መንፈሳዊ ሕይወቱ ሽባ ነውና።

ዲያብሎስን መቃወም የሚቻለው በእምነት ነው። “በመጠን ኑሩ ንቁም ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።” [1ኛ ጴጥ. 5÷8-9]። እዚህ ጋ ማስተዋል የሚገባን ነገር እምነታችን የተተከለበትና የቆመበትን ወይም እምነታችን ማንን መሠረቱ እንዳደረገ ነው። ዲያብሎስን ልንቃወም የምንችልበት እምነት ማለት በክርስቶስ የሱስ ላይ የተመሠረተና የጸና ነው። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ “… ሥርዓታችሁንም በክርስቶስም ያለውን የእምነታችሁንም ጽናት እያየሁ ደስ ይለኛል።” [ቆላ. 2÷5]።

የዚህች ጽሑፍ አንባቢያን ቅዱሳን ወንድሞችና እህቶች ሆይ በስጋ አይን ሳይሆን በእምነት አይን እንኑር! በእምነት አይን ማለት የማይታየውን ያየንበት አይን እምነት ነው። ሊመራን የሚገባ እምነት እንጂ የስጋ አይናችን መሆን የለበትም። በስጋ እይታ ስንመራ ነገሮች ሁሉ የሚከብዱ ይሆናሉ፤ በእምነት ስንመራ ግን ለሰው ልጆች ከባድ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ለእኛ ቀላል ይሆናሉ። እምነት የእግዚአብሔርን እጅና ክንድ የሚያንቀሳቅስ ስለሆነ በሕይወታችንና በመንገዳችን ሁሉ የአምላካችንን ድንቅና ተዓምራት እያየን እንኖራለን።

በእምነት ስንኖር የጊዜው [የአሁኑ] መከራችን ቀላል ይሆናል እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ “የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘላለም ነው።” [2ኛ ቆሮ. 4÷17-18]። በእምነት ስትኖር የጊዜው መከራ ቀላል ይሆናል። አንተ ግን በመከራ ላይ ከባድ ወይም ተጽዕኖ ፈጣሪ ትሆናለህ። ያለ እምነት ስትኖር ደግሞ የጊዜው መከራ በአንተ ላይ ከባድ ይሆናል፤ አንተ ግን በመከራ የምትሸነፍ ቀላል ትሆናለህ።

እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት የምንችለው በእምነት ነው በዕብ. 11÷6-7 “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ በዚህም ዓለምን ኮነነ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።” ይላልና።

እምነት ለዓለም ወይም ለፍጥረታዊ ሰው ሞኝነት ይመስላል። ለመዳን ደግሞ በስብከት ሞኝነት ማመን ያስፈልጋል። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፦ “በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና።” 1ኛ ቆሮ. 1÷21። እምነትን በውስጣችን ከሚጋፉ ነገሮች አንዱ ምድራዊ ጥበብና እውቀት ነው።

እውቀትና ጥበብ አስፈላጊ ናቸው፣ ነገር ግን እምነትን መዋጥና መሸፈን የለባቸውም።

በእውቀት ብቻ እንኑር ካልን እድሜ ልካችን ፍርሃትንና ጥርጣሬን እያስተናገድን እንኖራለን። ሰው እውቀቱ በጨመረ ቁጥር በዚያው ልክ በልቡ ውስጥ ፍርሃትና ጥርጣሬም እየጨመሩ ይሄዳሉ። ፍርሃትና ጥርጣሬ የሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ ናቸው። ምን እሱ ብቻ? ብዙ ሕይወታችን የሚያጠቁና የሚጎዱን ነገሮች ሁሉ በሽታንም ጨምሮ በዚያ ቀዳዳ ገብተው ያጠቁናል።

ሐዋርያው ጴጥሮስም በውኃ ውስጥ መስመጥ የጀመረው የነፋሱን ኃይል አይቶ ሲፈራ ነበር አድነኝ ብሎ ወደ ኢየሱስ ሲጮኽ ኢየሱስም “አንተ እምነት የጎደለህ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው።” [ማቴ. 14÷29-31]። እውቀት በእምነት ይሸፈን እንጂ እምነት በእውቀት አይሸፈን! እምነት እንደ ጋሻ ስለሚቆጠር እምነት ያለው ጠላት በሚወረውረው ልዩ ልዩ ፍላጻ አይጠቃም [አይወጋም] በእምነት ይከላከላል። በእምነት ፈንታ በልቡ ፍርሃትና ጥርጣሬ ካሉ ግን ጠላት ዲያብሎስ የሚወረውረው ፍላጻ በዚያ ቀዳዳ ሊያገኘውና ሊያጠቃው ይችላል።

ስለ እምነት ካነሳን አይቀር በእምነት የተከናወኑ አንዳንድ ተዓምራቶችን በጥቂቱ ላከፍላችሁ!

አንድ ወንድም ትኋን አሰቃይቶት ትኋን ለማጥፋት አሉ የሚባሉ የተባይ ማጥፊያ መድኃኒቶችን ሁሉ ቢጠቀምም ጭራሽ እየባሱ ይሄዳሉ። ሌሎች የተቻለውን ጥረት ቢያደርግም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ ሄዱ። በመጨረሻ አንዷን ትኋን በፌስታል አስሮ ወደ ዋራ ቤቴል ወስዶ በመሰዊያው ስር ጥሎ ካስረገጣት በኋላ ቤት የቀሩት ትኋኖች በሙሉ ጠፍተው ጠበቁት። ከቤቱ ጠፍተው ስላገኛቸው ከአገር ሁሉ የጠፉ መስሎት ሌሎችን ሲጠይቅ፤ ከእርሱ ቤት ብቻ እንጂ ከሌሎቹ እንዳልጠፉ አረጋግጦ በተአምራቱ ተደነቀ። ክብር ለኢየሱስ ይሁን!

ሌላም አንድ የወንጌል አገልጋይ በሞተር ሳይክል ለአገልግሎት ወደ ገጠር ሄዶ ከመንገዱ አስቸጋሪነት የተነሳ በመጨነቁ ግፊት ነበረበትና ለመታየት ወደ አንድ ክሊኒክ ጎራ አለ። ግፊቱ ሲለካ እጅግ በጣም ከፍ ከማለቱ የተነሳ ሀኪሙ ደንግጦ “አንተ ምን አይነት ሰው ነህ? ቶሎ ከቤቴ ውጣልኝ” ብሎ ቤቱ ውስጥ ወድቆ እንዳይሞት አስወጣው። ያ አገልጋይ እምነት ስለነበረው የሰማውን ከምንም ሳይቆጥር ተዝናንቶ ወጣለት። ያ ግፊት ሁሉ ምንም መድኃኒት ሳይጠቀም ኖርማል ሆኖ እስከ አሁን ድረስ በሰላምና በጤና እየኖረ ይገኛል።

አስተውሉ! ተመልከቱም! እውቀት ከባድ የሚያደርገውን ነገር እምነት ቀላል አድርጎ ያሳያል። ያ አገልጋይ እምነት ባይኖረው እንደ ማንኛውም ሰው ወዲያው ወድቆ መሞት ይችል ነበር። እምነቱ በሕይወት አኖረው ጻድቅ በእምነት ይኖራልና በእምነት እንኑር።

እምነት ቅዱስ ድፍረት ነው እንጂ ትዕቢት አይደለም፣ እምነት ጀግንነት ነው። ሁላችን እንደምናውቀው የጥንቱ ቅዱሳን ሰዎች ፍርሃትን አያውቁም፤ ሞትን፣ መከራን፣ ስደትን፣ እስራትን፣ ረሃብን፣ ጥማትን፣ እርዛትን፣ ልዩ ልዩ አጋንንታዊ አሰራርን፣ ልዩ ልዩ በሽታን፣ ዲያብሎስን ወዘተ አይፈሩም ነበር።

በነገራችን ላይ የመጨረሻው አስፈሪ የሆነ ሞትም አይቀርም። ፈሪ ሆኖ ከመሞት አምኖ መሞት ይሻላልና በእምነት እንኑር! እንዳመንንም እንሙት። “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፣” [ዕብ.11÷13] ይላልና።

Scroll to Top