ቢሾፕ አዱአለም ብርሃኑ  የኢ.ሐ.ቤ.ክ የዲጂታል ሚዲያ አገልግሎት ኦቨርሲር

ከእውነት ምስክር መጽሔት የተወሰደ

(5ኛ ዓመት ቁጥር 4-ግንቦት 2017 ዓ.ም)

ይህ በጣም ወሳኝ ጥያቄ ነው። ጌታ ኢየሱስም ከመወለዱ ጀምሮ አይነ ስውር የነበረውና የፈወሰውን ሰው በእግዚአብሔር ልጅ ያምን እንደሆነ ጠይቆት ነበር።

ዮሐ. 9፥35 – 38 “. . . አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን? አለው። እርሱም መልሶ፦ ጌታ ሆይ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው? አለ። ኢየሱስም፦ አይተኸዋልም፡ ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው አለው። እርሱም፦ ጌታ ሆይ አምናለሁ አለ፤ ሰገደለትም”።

የተፈወሰው ልጅ ለተጠየቀው ጥያቄ ‘አምናለሁ’ ወይም ‘አላምንም’ የሚል መልስ ከመስጠቱ በፊት “በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” ሲል ለመረዳት ፈልጎ ጠየቀ። ጌታ ኢየሱስም ‘አሁን ከአንተ ጋር ቆሞ የሚነጋገረውና የምታየው እርሱ ነው የእግዚአብሔር ልጅ’ ሲለው ልጁም ከእናቴ ማህጸን ጀምሮ እውር የነበርሁትን የእኔን አይኖች የከፈተውማ እርሱ ከሆነ እንዴት አላምን? ብሎ ‘አምናለሁ’ አለና ጨምሮም ‘ሰገደለት (worshipped him)’ ይላል።

1ኛ ዮሐ. 5፥11 “እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም”።

1ኛ ዮሐ. 5፥13 “የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ”።

በእግዚአብሔር ልጅ ማመን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የዘላለም ሕይወት ማግኘት ለሚፈልግ ሁሉ የተሰጠ የመዳን ግዴታ ነው። ግን ያ ልጅ እንደጠየቀው “በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” ብሎ በእግዚአብሔር ልጅ ማመን እንዴት እንደሆነ ከእግዚአብሔር ቃል ላይ በግልጽ፣ በጥንቃቄና በትዕግስት መማር ይጠይቃል እንጂ።

1. በአንድ አምላክና በልጁ ስለማመን

በኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን የእምነት አንቀጾች ላይ የመጀመሪያዎቹ ሁለት አንቀጾች ከዚህ ጋር የተያያዙ ናቸው። አንቀጽ 1 “አንድ አምላክ” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን “የማይታይ፣ የማይዳሰስ፣ በሁሉ የሚገኝ፣ በስፍራ የማይወሰን፣ መንፈስ የሆነ አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ እናምናለን” በማለት ይጀምርና የጥቅስ ማስረጃዎችን አቅርቦ ያብራራል።

እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ከሁሉ ፊተኛ የሆነችው ትዕዛዝ፦ “እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም በፍጹም ልብህ፡ በፍጹምም ነፍስህ፡ በፍጹምም አሳብህ፣ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ” የምትል ናት (ማር. 12፥29-30፤ ዘዳ. 6፥4-5)። የእስራኤል ልጆች የሚያውቁትና የሚያምኑት አምላካቸው በምንም መልኩ የማይከፋፈልና በቁጥር በነጠላ አንድ ብቸኛ የሆነ አምላክ ነው። ከዚህም የተነሳ ሰዎች Strict Monotheists (የአንድ አምላክ አክራሪ አማኞች) ብለው ይጠሯቸዋል። ይህንን የአምላክ ብቸኛ አንድ መሆን በትክክል ያልተረዳና ያላመነ ሰው “የእግዚአብሔር ልጅ” ወይም ሌሎች ጥልቅ የሆኑ የመለኮት እውነታዎችን ለመረዳት ይቸገራል። ስለዚህ በአንድ ብቸኛ አምላክ ማመን የሁሉ ነገር መሰረት ነው። እርሱም፦ “. . . እኔ ብቻዬን እኔ እንደሆንሁ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ” ብሎአል (ዘዳ. 32፥39)። “እርሱ ግን ብቻውን ነው”(ኢዮብ 23፥13)።

እንዲህ በአንድ ብቸኛ አምላክ አጥብቀው ለሚያምኑ አይሁድ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ለመቀበል በጣም የተቸገሩበት ምክንያት “ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ ስለሚያውቁና ስለሚያምኑ” ነው። ለዚህም ነው “አንተ ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለማድረግህ ነው የምንወግርህ ያሉት” (ዮሐ. 10፥33)። በእውነትም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “በስጋ የተገለጠ የእስራኤል አምላክ” ካልሆነ እንዴት አምላክ ሊሆን ይችላል? እንዴትስ ይሰገድለታል? እርሱ ራሱ ለሰይጣን ሲመልስለት “ሂድ አንተ ሰይጣን፤ ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፥ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል” ብሎ የለ? (ማቴ. 4፥10)። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ልጅ በትክክል ሳያውቁ በማመን ከእውነተኛው ብቸኛ አምላክ ውጭ ያለ ማንነትን ሰጥቶ እርሱን ማምለክና ለእርሱ መስገድ ጣኦትን ማምለክ እንዳይሆን እርሱን ማን እንደሆነና የእግዚአብሔር ልጅነቱም እንዴት እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በእርጋታ መማር ይጠይቃል። ለዚህ ነው ሐዋርያው ዮሐንስ “. . . እርሱ እውነተኛ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው። ልጆች ሆይ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ” ሲል ያስጠነቀቀው (1ኛ ዮሐ. 5፥21)።

በኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን የእምነት አንቀጾች አንቀጽ 2 ላይ የተጻፈው ደግሞ “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን “በአብ ዘንድ የነበረው ቃል ሥጋ በመሆኑ፣ ክርስቶስ በሰውነቱ፣ የሰው ዘር ያልተቀላቀለበት ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እናምናለን” የሚለው የአንቀጹ የመጀመሪያ ዓ/ነገር ሲሆን የጥቅስ ማስረጃዎችን እያሳየ ዝርዝሩን ያቀርባል።

እንግዲህ ማንም ሰው በእነዚህ አንቀጾች ላይ በቀረቡት መግለጫዎች የማመንም ያለማመንም ሙሉ መብት ያለው ሆኖ “የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር ልጅ አታምንም” የሚለው አልፎ አልፎ የሚሰማው የተቃዋሚዎቿ አባባል ግን ያስተዛዝባል። የሚገርመው ነገር ትንሽ ቀደም ባሉት ዓመታት “የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን አማኞች አብንና መንፈስ ቅዱስን ክደው በወልድ (በእግዚአብሔር ልጅ) ብቻ ነው የሚያምኑት” ይባል ነበር። አሁን ደግሞ ተገልብጦ “ኢየሱስን አብ ብቻ ነው ይላሉ፥ በእግዚአብሔር ልጅ አያምኑም” የሚል ተቃውሞ ይሰማል። ሁለቱም አባባሎች የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ በአግባቡ ካለመረዳት የተባሉ ስለሆኑ ሁለቱም ልክ አይደሉም።

ከእምነት አንቀጽም አልፎ የቤተክርስቲያኒቱ አርማ ላይ የተጻፈው “በዚችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ” የሚለው ቃል ራሱ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ ሐዋርያው ጴጥሮስ ለኢየሱስ ክርስቶስ በመለሰለት ሰማያዊ መገለጥ ላይ የተመሠረተች መሆኗን ለመግለጽ የተጻፈ እኮ ነው (ማቴ. 16፥16-18)። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ፣ እንዲሁም እግዚአብሔር አብ ራሱ በስጋ ተገልጦ በምድር ላይ በተመላለሰበት በራሱ የስጋ ሰውነት (በልጁ) “መጽሐፍ እንደሚል ብቻ” ታምናለች። ዝርዝሩን በዚህ ጽሁፍ ለማቅረብ ተሞክሮአል።

2. በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ (only begotten son) ማመን እንዴት?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር አንድያ ልጅ የሚያስተምረውን ትምህርት በአግባቡ መረዳት እንዲቻል በሌሎች የታወቁ የእምነት ክፍሎች ዘንድ ያለውን አስተምህሮ በንጽጽር ማየቱ አስፈላጊ ነው። ይህም የሌሎችን እምነት ለመንካት ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊውን አስተምህሮ በግልጽ ለማሳየት እንዲረዳ ብቻ ነው። በእነርሱ በኩል እግዚአብሔር አብ አንድ አካል እና የእግዚአብሔር ልጅ (እንደነርሱ አባባል እግዚአብሔር ወልድ) ደግሞ ከእግዚአብሔር አብ የተለየ ሌላ አካል ሆኖ ከዘላለም በዚህ መልክ እንዳለ ተደርጎ “ዘላለማዊ ልጅ” ተብሎ ይታመናል። ያ ዘላለማዊ ልጅ ማርያም ከወለደችው ከማርያም ልጅ ጋር ተዋህዶ ወይም ሳይዋሃድ (ይህ ብዙ ክርክር የሚከራከሩበት ጉዳይ ነው) በምድር ላይ ተገለጠ፤ ይህ ነው የእግዚአብሔር ልጅ ብለው ይናገራሉ፣ ያምናሉም። ማንም ሰው ይህንን ማመንም አለማመንም መብቱ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ልጅ ስለማመን የሚያስተምረው ግን እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ከዘላለም ከአብ በተለየ አካል “እግዚአብሔር ወልድ” ወይም “የእግዚአብሔር ልጅ” ተብሎ የሚታወቅ/የሚጠራ ‘ዘላለማዊ ልጅ’ እንደነበረ ፈጽሞ አያስተምርም። ለምሳሌ በሐዋ. 13፥33 “አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ” በሚለው ክፍል ላይ “ዛሬ” ሲል የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ የተወለደው ጊዜ ከተፈጠረ በኋላ በጊዜ ውስጥ እንጂ ከዘላለም እንዳልሆነ በግልጽ ያሳያል።  በተጨማሪም በ ዮሐ. 1፥1 ላይ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ . . . ሁሉ በእርሱ ሆነ” ይላል እንጂ “በመጀመሪያ ልጅ/እግዚአብሔር ወልድ ነበረ፥ ልጅም/ እግዚአብሔር ወልድም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ልጅም/እግዚአብሔር ወልድም እግዚአብሔር ነበረ …” አይልም። ቀጥሎ በቁጥር 14 ላይ “ቃልም ስጋ ሆነ . . .አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን” ሲል “ልጅ” የሚለውን ስያሜ ያገኘው በሰው ምሳሌ ሲገለጥ እንደሆነ በግልጽ ያስረዳል።

እዚህ ጋ “ቃል” ሲባል ከአብ በተለየ አካል የሚኖር “አካላዊ ቃል” ነበረ ወይንስ ከእግዚአብሔር አብ ከራሱ የሚወጣ ቃል”? የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ አስፈላጊ ነው። ይህንን ጥያቄ በግልጽ ለመመለስ “ሁሉ በእርሱ ሆነ” የሚለውን ቃል ማየት ብቻ በቂ ነው። እንዴት ነው ሁሉ በእርሱ/በቃል የሆነው? ማንም ጀማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ በቀላሉ ሊረዳ እንደሚችለው የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍና ፍጥረት ሁሉ ካለመሆን ወደ መሆን እንዴት እንደመጣ በሚያሳየው በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ምእራፍ አንድ ላይ በዝርዝር ተጽፏል። እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣው “ሁን” በሚል የስልጣን ቃል ነው እንጂ አጠገቡ የተቀመጠ አካላዊ ቃልን እያዘዘ አይደለም። በመዝ. 148፥5 ላይም “. . . እርሱ ብሎአልና ሆኑም. . . “ይላል። ደግሞም በኢሳ. 55፥11 ላይ “ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም” ይላል።

በዚህ መሰረት “ቃል” ከእግዚአብሔር አፍ እየወጣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሁሉ የሚፈጽም የእግዚአብሔር የራሱ የስልጣንና የኃይሉ የማንነቱም ጭምር መገለጫ እንጂ ከእግዚአብሔር አብ ተለይቶ በራሱ ልዩ አካል የሚኖር አልነበረም።  ምናልባት እዚህ ጋ በዕብ. 1፥1-3 በተጻፈው ክፍል ላይ “. . . ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ስለሚል እግዚአብሔር አለማትን ሲፈጥር ልጁም በተለየ አካል አብሮት ነበር ብሎ የሚረዳ ሰው ሊኖር ይችላል። ይህንንም በአግባቡ ለመረዳት ራዕይ 13፥8ን ማየት ብቻ በቂ ነው። “ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል” ይላል። ማንም ሊረዳ እንደሚችለው “የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት የሚያስወግደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ. 1፥29) የታረደው በቀራንዮ መስቀል ላይ እንጂ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ አይደለም። ስለዚህ ይህ ጥቅስ የሚያሳየው የበጉ መታረድ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ  በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ የነበረ እንደሆነ ነው። በዚሁ መልክ እግዚአብሔር ቃሉን ስጋ አድርጎ “የእግዚአብሔር ልጅ” በሚል ስያሜ በምድር ላይ እንደሚገለጥ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለና የሚታወቅ አሳብ ስለሆነ ገና ቃል ስጋ ሳይሆን “ልጁ” እያለ ሲጠራው ይታያል።

ይህም ብቻ አይደለም። በኤፌ. 1፥8-9 ላይ “. . . ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር . . .” የሚለውን “who created all things by Jesus Christ” ይላል (የእንግሊዝኛው አነጋገር)። እግዚአብሔር ሁሉን የፈጠረው “በቃሉ”፣ “በልጁ” ወይም “በኢየሱስ ክርስቶስ” ቢልም ትርጉሙ አንድ ነው። እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረው አንድ ጊዜ ስለሆነና የፈጠረበትም ሁኔታ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ በግልጽ የሰፈረ ስለሆነ “በቃሉ”፣ “በልጁ” ወይም “በኢየሱስ ክርስቶስ” የሚሉት አነጋገሮች ቃል ስጋ ሆኖ እንደሚመጣ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ እንደነበር እንጂ ሁለተኛ አካል እንዳለ የሚያሳዩ አይደሉም።

ይህን መሰረታዊ አሳብ ይዘን ወደ ዋናው ጥያቄ ስንመጣ “በእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ማመን እንዴት ነው?”። የእግዚአብሔር አንድያ ልጅስ ማን ነው? በብዙ የእግዚአብሔር ቃል ማስረጃ ማረጋገጥ እንደሚቻለው የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ የሆነውና የሚታመንበት በሰው መልክ የታየው እንጂ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ተብሎ የሚጠራ አካል አልነበረም። በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ “በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” ብሎ ለጠየቀው ልጅ ጌታ ኢየሱስ የመለሰለት “አሁን የምታየው እርሱ ነው” የሚል ነው። የታየው ነው የእግዚአብሔር ልጅ። ቀጥሎ ያሉትም ቃላት ይህንኑ ያስረዳሉ።

ሉቃስ 1፥35 “መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል”።

ገላ. 4፥4 “. . . የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ”።

ማቴ. 16፥13-18 “. . . ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል? . . . አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ . . . ኢየሱስም መልሶ . . . የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብጹዕ ነህ”። ይላል።

እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎችን ስናይ “የእግዚአብሔር ልጅ” ተብሎ የተጠራው ራሱን “የሰው ልጅ” ብሎ የጠራው፣ ከድንግል ማርያም የተወለደውና በስጋ የታየው ነው። ስለዚህ ስለ እግዚአብሔር አብና ስለ አብ ልጅ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ መነጋገር ማለት መንፈስ ስለሆነው እግዚአብሔር አብና ስለ ስጋ ሰውነቱ መነጋገር ነው።

አልፎ አልፎ ሰዎች “የስጋ ሰውነት” የሚለውን አነጋገር መቀበል ሲሳናቸው ይታያል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሰው መቀበል ከተሳነው ወደ እውነት እንዴት መድረስ ይችላል? “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ የሚወድ እግዚአብሔር” በቃሉ ላይ በግልጽ ያስቀመጠው አንድ እግዚአብሔር ብቻ እንዳለና በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ለማስታረቅና ለመካከለኛነት የገባ ሰው/የስጋ ሰውነት/የእግዚአብሔር ልጅ እንዳለ ብቻ ነው።

ቆላ. 1፥19-21 “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና። እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ”። ይለናል።

በሮሜ 5፥10 ላይ “ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን” ብሎ የሚናገረው ቃል “በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቀን” ከሚለው ጋር ትርጉሙ አንድ ነው። የልጁ ሞት ማለትም የስጋው ሰውነት ሞት ማለት ነው። ስለዚህ “ልጁ” ማለት “የሥጋው ሰውነት” መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል። የተጻፈው እንዲህ ነውና።

2ኛ ቆሮ. 5፥18-19 “ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና…”።

ይህንንም ቃል ከላይ ከተጻፉት ጋር አገናዝበን ስናይ አስታራቂው ራሱ እግዚአብሔር (አብ) ሲሆን የታረቅነውም ከራሱ ጋር ነው፤ ማለትም ታራቂውም ራሱ እግዚአብሔር (አብ) ነው ማለት ነው። ከራሱ ጋር ያስታረቀን ደግሞ በስጋው ሰውነት በሞቱ በኩል ወይም በክርስቶስ ወይም በልጁ ሞት (ሮሜ 5፥10) እንደሆነ ነው የሚያስረዳን። ስለዚህ ስለ እግዚአብሔር ልጅ ስንነጋገር ስለ ስጋ ሰውነት፣ “ሰው የሆነ ክርስቶስ” ስለተባለው መሆኑን በሚገባ መረዳት ቁልፍ ጉዳይ ነው።

3. የእግዚአብሔር አብና የልጁ ግንኙነትስ?

ቀጥሎ የሚነሳው ዋና ጉዳይ የእግዚአብሔር አብ (የመለኮት) እና የልጁ (የስጋው ሰውነት) ግንኙነትን እንዴት ነው የምንረዳው? የሚለው ይሆናል። አሁንም በሌሎች የእምነት ክፍሎች የሚነሳውን በንጽጽር በማቅረብ እዚያ ሰፈር ከሚነገረው ጋር ፈጽሞ የተለየ መሆኑን አይቶ ማለፍ የግድ ይሆናል። እዚያ ሰፈር ስለመለኮትና ሰውነት ግንኙነት ሲነሳ እነርሱ “እግዚአብሔር ወልድ” ብለው የሚያውቁት መለኮት እና የማርያም ልጅ ስለሆነው ሰው ግንኙነት ነው። እዚህ ግን ስለ መለኮት ሲነሳ ስለ አብ ሲሆን ስለ ሰውነት ሲነሳ ደግሞ ቃል ስጋ ሆኖ ከማርያምም ሆነ ከማንኛውም የአዳም ዘር ጋ ምንም የዘር ግንኙነት ስለሌለው ሰማያዊ ሰው ወይም የእግዚአብሔር ልጅ ነው (1ኛ ቆሮ. 15፥45-47)። ሁለቱ አሳቦች ፈጽሞ የተለያዩ አሳቦች (እውቀቶች) ናቸው።

በዚህ መሰረት የመለኮትና የሰውነትን ግንኙነት አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው እንዴት ነው? የሚለውን ጉዳይ ትንሽ ዘርዘር አድርጎ ማየት የግድ ይሆናል።

1ኛ ጢሞ. 2፥3-6 “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ”።

“አንድ እግዚአብሔር አለ”፣ “አንድ መካከለኛ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ አለ” ማለት ምን ማለት ነው? “ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ” እና “አንድ እግዚአብሔር” ምንና ምን ናቸው? ሁለት ናቸው ወይንስ አንድ? በአንድ አካል ላይ ያለ ሁለት ማንነቶች ናቸውን? መቼም በዚህ ጥቅስ አግባብ (Context) ‘ሰው የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ’ የሚለው ሐረግ ‘የእግዚአብሔር ልጅ’ ማለት እንደሆነ ለአንባቢ ሁሉ ግልጽ ይመስለኛል። ስለዚህ ይህ ጥያቄ የእግዚአብሔር አብና የልጁ ግንኙነት እንዴት ነው? የሚል ነው።

ለዚህ ጥያቄ ግልጽና ቀጥተኛ መልስ ለመስጠት “ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ” የተባለው ሰው ከመሆኑ በፊት የት ነበር? ምን ነበር? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የሚናገረውን እንይ።

1ኛ ዮሐ. 1፥2 “. . . ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን”።

ዮሐ. 1፥1-3 “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ . . . ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች”።

ዮሐ. 16፥27 – 28 “. . . ከእግዚአብሔርም ዘንድ እኔ እንደ ወጣሁ (came out) ስላመናችሁ አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና . . . ከአብ ወጥቼ (came forth) ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ፡ ወደ አብም እሄዳለሁ”።

በእነዚህ ቃሎች መሰረት ሰው ከመሆኑ በፊት በአብ ውስጥ የነበረ፣ ሁሉ በእርሱ የሆነበት የአብ መገለጫ ቃል የነበረ፥ እንዲሁም ራሱ ሕይወት የነበረ ነው። ያን ጊዜ (ሰው ከመሆኑ በፊት) ማንኛውም ሰው ከራሱ ቃል ተለይቶ ማንነት ሊሰጠው እንደማይቻለውና ቃሉም ከእርሱ ተለይቶ የራሱ ማንነት እንደሌለው ሁሉ አብን ከቃሉ ቃሉንም ከአብ ለይቶ የሚታወቅበት ወይም የተገለጠበት ሁኔታ አልነበረም። ቃል ያለውና የሚናገር/የሚሰራ/የሚፈጥር/ ሁሉን የሚያደርግ አንድ (ብቸኛ) እግዚአብሔር አብ ነበረ እንጂ። ከገዛ ቃሉ ተነጥሎ አምላክ ሊሆን የሚችል አምላክ የለም። ከእግዚአብሔርም ተለይቶ ራሱን የቻለ ማንነት ያለውም ቃል የለም። አብና ቃሉ መለኮትና የመለኮት መገለጫ የሆነ የራሱ ቃል ናቸው። ቃሉና ራሱ “እናንተ” ተብሎም አይጠራም።

እንዲህ ከሆነ በአዲስ ኪዳን ምን ተፈጠረ ታዲያ? መጽሐፍ ቅዱሱ እንደሚነግረን “ቃልም ስጋ ሆነ” (ዮሐ. 1፥14)፤ ወይም ሰው ሆነ። ይህ ነው አዲሱ ነገር። ይህ እጅግ ትልቅ ጉዳይ ስለሆነ ሰው ሁሉ ቆም ብሎ “ለምን እንዲህ ሆነ?” ብሎ ከእግዚአብሔር ቃል ላይ መጠየቅ አለበት። የእግዚአብሔር ቃል በዚህ ዙሪያ ሰፊ ትምህርት አለው።

ቃል ስጋ የሆነበት (ሰው የሆነበት) ምክንያት ከገነት ወጥቶና ከፊቱ ሸሽቶ ጠፍቶ፣ የዘላለም ሞት ፍርድ ተጠብቆለት የአጋንንት መጫወቻ ሆኖ የቀረውን የሰው ዘር የሚከፈለውን ዋጋ ከፍሎ (ቤዛ ሆኖ) ወደራሱ ሊመልስለት/ሊመልስበት የሚችል ሰው ስላጣና እግዚአብሔር ራሱ መፍትሔ ፍለጋ ውስጥ ስለገባ ነው። ቃል ስጋ የሆነው ዓለሙን ለማዳን ሲል ነው። “ሰውም እንደሌለ አየ” የሚለው የነቢዩ ኢሳይያስ የትንቢት ቃል (ኢሳ. 59፥16) ከእግዚአብሔር ሰውን የመውደድ ጥልቅ የፍቅር ጓዳ ውስጥ የሚጮኽ መለኮታዊ ጩኸት ነው። ከፍጥረተ ዓለሙ ውስጥ “ሰው” ሊገኝ ስላልቻለ “የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት” (ኢሳ. 59፥16)። ያ ቃል ስጋ የሆነው ሰው ነው የእግዚአብሔር የገዛ ክንዱ ያመጣው መድኃኒት። ለዚህም ነው ክርስቶስ ሲወለድ መልዐኩ “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” ብሎ ያወጀው (ሉቃስ 2፥11)። “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን” ተባለ (ዮሐ. 1፥14)። ከፍጥረተ ዓለሙ ውስጥ እግዚአብሔር የሚፈልገው አይነት ሰው ስላልተገኘ እግዚአብሔር ራሱ አዘጋጀልን። “እግዚአብሔር ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ሁሉ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው” የተባለውም ለዚህ ነው (ሐዋ. 17፥31)። በዕብራውያን 10፥5 ላይ “መስዋዕትንና መባን አልወደድህም፥ ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ” ያለውም ይህንኑ የሚገልጽ ነው። መንፈስ ቅዱስም ቤተክርስቲያን በተመሰረተችበት በበዓለ ሃምሳ ቀን በጴጥሮስ አፍ ሆኖ “ . . . የናዝሬቱ ኢየሱስ . . . ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ (approved) ሰው ነበረ” ሲል ያወጀውም አዋጅ ይህንኑ የሚያስረዳ ነው (ሐዋ. 2፥22)።

ስለዚህ ይህ “ሰው የሆነ ክርስቶስ” የተባለው ከሴት ተወልዶ ወደ ምድር ሲመጣ “የእግዚአብሔር ልጅ” በሚል ስያሜ በሰውነቱ የእግዚአብሔር አብ ማደሪያ/ቤተመቅደስ ሆኖ በምድር ላይ በሰዎች መካከል ተገኘ።

ዮሐ. 2፥18-21 “ስለዚህ አይሁድ መልሰው፦ ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት። ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ ኣላቸው። ስለዚህ አይሁድ፦ ይህ ቤተመቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት። እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር”።

ኢሳ. 8፥13-15 “ነገር ግን የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት፤ የሚያስፈራችሁና የሚያስደነግጣችሁም እርሱ ይሁን። እርሱም ለመቅደስ ይሆናል፤ ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች ለዕንቅፋት ድንጋይና ለማሰናከያ ዓለት፥  በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሽክላ ይሆናል። ብዙዎችም በእርሱ ይሰናከላሉ፥ ይወድቁማል ይሰበሩማል፥ ይጠመዱማል፥ ይያዙማል”።

እነዚህ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚናገሩት ስለ አንድ እውነታ ነው። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ራሱ እንዴት ለመቅደስ እንደሆነ ነው። ለመቅደስ የሆነው ሌላ ሳይሆን የራሱ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር መገለጫ የሆነው ቃል ስጋ ሆኖ ነው። ብዙዎች የተሰናከሉትም ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነት መጥቶ “እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” እያለ ሲናገር፣ ሲያስተምርና ሲሰራ አይተው ነው። “አንተ ማን ነህ?” ሲሉት “ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ” ይላቸው ነበር (ዮሐ. 8፥25)። “አብን አሳየን” ሲሉት “ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ አብን አሳየን ትላለህ?” ደግሞም “እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ፥ አይታችሁትማል” ይላቸው ነበር (ዮሐ. 14፥7-9)። ከዚህ አይነት አስተምህሮዎቹ የተነሳ ብዙዎች እንደተሰናከሉበት ሐዋርያው ጴጥሮስም በመልእክቱ አረጋግጦአል (1ኛ ጴጥ. 2፥7-8)።

ማቴ. 1፥21-23 “እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ፦ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፡ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው”።

ቆላ. 2፥9 “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና”።

እነዚህን ሁሉ የእግዚአብሔር ቃሎች አገናዝበን ካየን “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚባለው በሰውነቱ መካከለኛ ሆኖ የታየው ሲሆን በመለኮቱ በኩል ደግሞ አንድ መለኮት ስለሆነ ያለው ራሱ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር አብ መሆኑን ብቻ ነው መረዳት የሚቻለው። መለኮት አይታይም፣ አይጨበጥም፣ አይዳሰስም፤ የእግዚአብሔር ልጅ ግን የታየ፣ የተጨበጠና የተዳሰሰው ነው፤ መለኮት አይሞትም፤ የእግዚአብሔር ልጅ ሞትን በሞቱ ኃይል ለመዋጥ ስለ ኃጢአት ለመሞት የተዘጋጀ ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ የሞተው ነው፤ መለኮት በባህርዩ የማይደክም፣ የማይራብ፣ የማይጠማ፣ የማይታመም፣ የማይቆስል . . . ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ ግን ይህን ሁሉ እንዲሸከም በእግዚአብሔር የተዘጋጀ የራሱ ሰው (የእግዚአብሔር መሲሕ/ክርስቶስ (the Lord’s Christ) – መዝ. 2፥2፤ ሐዋ. 4፥26፤ ሉቃስ 2፥26) ስለሆነ ይህንን ሁሉ የከፈለ የዓለም መድኃኒት ነው።

ስለዚህ የእግዚአብሔር አብና የልጁ ግንኙነት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን የስጋ ሰውነት እና በዚያ ስጋ ሰውነት የተገለጠ የመለኮት ሙላት ብቻ ነው። በሰውነቱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ በዚያው የስጋ ሰውነት (በቤተመቅደሱ) በሙላት የተገለጠ አምላክ እንደመሆኑ እግዚአብሔር አብ ነው (የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና)። ስለዚህ ነው ኢየሱስ እውነተኛ አምላክም የዘላለም ሕይወትም (ሕይወት ያለው በልጁ/በስጋው ሰውነት) እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው (1ኛ ዮሐ. 5፥20-21)።

4. ኢየሱስ ራሱ አብ ራሱም ልጅ ነው ማለት ነው?

ምናልባት የመጨረሻ የሰው ጥያቄ የሚሆነው “ራሱ አብ ራሱም ልጅ ሆነ ማለት ነው? እንዲህስ ከሆነ የተወለደው፣ የሞተውና የተቀበረው ራሱ አብ ነው ማለት ነው? ካልሆነስ የሞተውና የተቀበረው የተነሳውስ ማን ነው ልንል ነው?” የሚል ሊሆን ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረን “በስጋ ሞተ፥ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” ብሎ ነው (1ኛ ጴጥ. 3፥18)። ደግሞም “ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሳዋለሁ” ብሎ “ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር” ይላል (ዮሐ. 2፥19-21)። የሞተው በስጋው ሰውነቱ ነው፤ የተቀበረና የተነሳውም እንደዚያው። ማንኛውም ሰው በስጋ ሲሞት መንፈሱ ሞተ እንደማይባለው ሁሉ ክርስቶስም ሲሞት የሞተው በሰውነቱ ነው። ያም ሞት ዓለሙን ለማዳን በፈቃዱ የተቀበለው ሞት ነው (ዮሐ. 10፥17-18)። በዓላማ የሞተ እንጂ ሞት አሸንፎት የሞተ አለመሆኑን በምስማር የተወጉ እጅና እግሮቹን እና በጦር የተወጋ ጎኑን ይዞ መነሳቱ ትልቁ ምስክር ነው (ሉቃስ 24፥36-40)።

እግዚአብሔር ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ መሆኑ እየታመነ ቃሉ እንዲህ በግልጽ የሚናገርለትን በአንድ አካል ላይ የሚሞትና የማይሞት ባህርይ መኖሩ በሰው ልጆች ዘንድ “ስለምን የማይታመን ነገር ሆኖ ይቆጠራል?” (ሐዋ. 26፥8)። ምናልባት ይህንን ሁኔታ ለመረዳት ከጠቀሙ የሚከተሉትን ቃላት ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጨምሮ ማየት ይቻላል።

ዘካ. 12፥10 “በዳዊትም ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የሞገስንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ፤ ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ” (የድሮው አማርኛ – “ወደኔም ይመለከታሉ፥ ወደኔ ወደ ወጉኝ” ይላል –  እንግሊዝኛውንም መመልከት ይቻላል)።

ይህ ቃል የተፈጸመው በዮሐ. 19፥34-37 ላይ ነው። የተወጋውም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ (ሰው የሆነው) ነው። በስጋ ሰውነቱ ተወጋ። በሐዋ. 20፥28 ላይ ደግሞ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን” ሲል የፈሰሰውም ደም የራሱ የእግዚአብሔር (የአብ) ደም እንጂ ሌላ አለመሆኑ ተገልጾአል። ስለዚህ ስጋና ደሙ የራሱ የእግዚአብሔር (አብ) ስጋና ደም ነው። ከአብ ውጪ “እግዚአብሔር” ተብሎ የተጠራ እግዚአብሔር አለመኖሩን መዳንን የሚፈልግ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሱን መመርመር አለበት።

ማቴ. 17፡1-8 “. . . በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ጸሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ . . . ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም”።

ወደ ተራራው ላይ እንደ ሰው አብሮአቸው በእግሮቹ እየተጓዘ የወጣው ኢየሱስ ራሱ ነው እያዩት ፊቱ እንደ ጸሐይ የበራው። ይኸው ኢየሱስ ራሱ ነው ከትንሣዔውም በኋላ በደብረዘይት ተራራ ላይ እያዩት ወደሰማይ ከፍ ከፍ ያለውና ደመና ከአይናቸው ሰውራ የተቀበለችው (ሐዋ.1፥9)።

ሉቃስ 24፥30-31 “ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ እንጀራውን አንስቶ ባረከው፥ ቆርሶም ሰጣቸው ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ” (… he vanished out of their sight)።

ሞትን በሞቱ ኃይል ለመዋጥ፣ ቤዛ ለመሆን፣ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰዎች ሁሉ የታመነ ሊቀ ካህን ለመሆን፣ መካከለኛና አስታራቂ፣ ወደ መለኮት (ወደ አብ) መድረሻ መንገድም ለመሆን . . . ወዘተ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ በሰው መልክ መገኘት አስፈልጎት ለእኛ ሲል ሰው ሆኖ የሰው ልጅ የሚቀበለውን መከራ ሁሉ ሊቀበል ለዚህ ዓላማ የእግዚአብሔር ልጅ እየተባለ መጣ እንጂ በመለኮታዊ ማንነቱ እርሱ “በስጋ የተገለጠ አንድ አምላክ አብ” ነው።

ለዚህም ነው፦ “. . . አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ፥ እነሆም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲዖልም መክፈቻ አለኝ” ሲል ከአርያም የሚያስተጋባው (ራዕይ 1፥17-18)።

በእርግጥ፦ “እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው!” – “በእውነትም ታላቅ ነው የአምልኮት ምስጢር፥ አምላክ በስጋ ተገለጠ” (የድሮው አማርኛ) (1ኛ ጢሞ. 3፥16)። “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ፥ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን” (1ኛ ቆሮ. 8፥6) እና ሌላ አምላክ ስለሌለን፥ ስለማናውቅም ያ “አንድ አምላክ አብ በስጋ ተገለጠ” የሚለው ነው ታላቁ እግዚአብሔርን የመምሰል ምስጢር! ይህም እግዚአብሔር አብ እና የእግዚአብሔር ልጅ በአንድ አካል ያለበት ታላቅ ምስጢር ነው። ይህ የአብና የወልድ ታላቅ ምስጢር ነው! የምስጢሩ ቁልፍም ክርስቶስ ነውና ክርስቶስን በዚህ መልክ መረዳት የቻለ የአምላክ በስጋ መገለጥ ምስጢር በርቶለታል ማለት ነው! ከእግዚአብሔር ቃል ላይ እንደምንማረው በእግዚአብሔር ልጅ ማመንም እንዲህ ነው!

ጌታ ኢየሱስ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን!

Scroll to Top