ቢሾፕ ብርሃኑ ድጅቆ | የወላይታ ሰበካ ኃላፊ

በእግዚአብሔር ፈቃድና አሠራር በአንዲት የክርስቶስ አካል በምትሆን፤ በእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ቀርበን በውስጧ መኖራችን ከእርሱ የተነሳ ነውና ለእርሱ ከዘለአለም እስከ ዘለዓለም ክብርና ምስጋና ይሁንለት።

ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም የሆነለት አንድ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጠን ለቁጣ ሳይሆን ለመዳን ስለሆነ በዚህ በመጨረሻው ዘመን ላይ የምንገኝ ሁላችንም የእግዚአብሔር ፈቃድ በዚህ ሰዓት ምን እንደሆነ አውቀን እና ተረድተን በእግዚአብሔር ቤት መኖር በእኛ ውስጥ ትልቁን ቦታ ሊይዝ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። ለምን ቢባል ከዚህ በታች በዝርዝር የተጠቀሱትን የእግዚአብሔር ቃል  ክፍሎችን ልብ ብለን ስንመለከት በመጨረሻው ሰዓት የሚቀርና የሚወሰድ፣ የሚነጠቅና የማይነጠቅ፣ የሚገባና የማይገባ፣ የሚመረጥና የማይመረጥ እንዳለ ስለሚያሳይ ይህ ዘመን የመጨረሻ ሰዓት መሆኑን አውቀን መንቃት እጅግ በጣም ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ነው ።

  • 2ኛ ጴጥ. 1፥10 “ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ፤” ይላልና በመጨረሻው ሰዓት ከተጠሩት መካከል ወደ ምርጫ ውስጥ ለመግባት መትጋት እንዳለብን ይህ የእግዚአብሔር ቃል ክፍል ያሳየናል። መጠራትም አለ፤ ከተጠራንም በኋላ መመረጥም አለ።
  • ማቴ. 13፥47 “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤” በማለት መልካምና ክፉም በአንድ መረብ ውስጥ እንደተሰበሰበና በመጨረሻ መልካሙን ወደ ዕቃው ክፉን ደግሞ ወደ ውጭ እንደተጣለ ያሳየናል።
  • ማቴ. 20፥16፦ “. . .የተጠሩ ብዙዎች የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው” ይላል። ከተጠሩት መካከል ጥቂቶች ወደ ምርጫው ውስጥ እንደሚገቡና የተቀሩት ደግሞ ወደ ሀዘን እና ጭንቀት ውስጥ እንደሚገቡ የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ ያስተምረናል።
  • ማቴ. 25፥1-2 “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ።” ይላልና በጥሪ ከመጡት መካከል በመንፈስ ቅዱስ ሙላት ምክንያት መብራታቸው ጠፍቶ የቀሩና ሕያው ሆነው የተመረጡ እንዳሉ ያሳየናል።

ስለዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ወደ እኛ እጅግ በጣም የተቃረበበት ምልክቶች ዛሬ በግልጽ ስለሚታዩና እየሆኑ ያሉት ነገሮች ለምሳሌ ቢጠቀስ፦ የሃሳዊ መሲህ አሰራርና ፕሮግራሞች በየቦታው ብቅ ብቅ ብሎ መታየት (ራዕይ 13፥16-18)፣ የሙሽሪት እንቅልፍ (ማቴ. 25፥1) ፣ የእርስ በእርሳችን ፍቅር መቀዝቀዝ (ማቴ.24፥12)፣ በየቦታው የምንሰማቸውና የምናያቸው ነገሮች ማለትም ሕዝብ በሕዝብ ላይ መነሳት፣ የጦርነትና የሁከት ወሬዎች፣ በየስፍራው የሚሰሙ የምድር መናወጦች፣ የእርስ በርስ እልቂቶችና ፍጅቶች ፣ ድርቅና ርሃብ እንዲሁም ሌሎችም ምልክቶች በዓለማችን ላይ በግልፅ እየታዩ ስለሚገኙ በ2ኛ ጴጥ. 3፥11-12 “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል?” ስለሚለን በዚህ በዘመን ፍጻሜ በ11ኛው ሰዓት ላይ የምንገኝ የዚህ ዘመን አገልጋዮችና ምዕመናን ስለሁኔታዎችና ስለሚሆኑ ነገሮች እንዲሁም ፍጻሜያችን የሰመረ አንዲሆን በሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያዝዘን የፍጻሜ ሰዎች ሆንን መኖር፣ መዘጋጀትና መጠበቅ ይገባናል። በመጠራታችን ብቻ ተጽናንተን መዘናጋት ውስጥ ገብተን ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አውቀን መንቃት ሲገባን ሳንነቃ ቀርተን ተስፋችን እንዳያመልጠን ከመናገር አልፈን ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ውስጥ እንድንገባ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን።

በተጨማሪም በ1ኛ ተሰ. 5፥1-5 “ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። …እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥ ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና።” ስለሚል ከዛሬ 1950 ዓመት በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ የዘመኑን ማለቅና መዘጋጀት እንዳለብን አስረድቷል።

እኛ በፍጻሜ ጫፍ ላይ የምንገኝ የእግዚአብሔር ቤት ሰዎች የተሰጠንን ጊዜ እንደትልቅ ፀጋ በመቀበል ቢያንስ ከዚህ በታች በዝርዝር በሚገኙ ነጥቦች የዘመኑን ማለቅ ተገንዝበን የብርሃን ልጆች እንደመሆናችን መጠን መዘጋጀት ይጠበቅብናል።

ራዕይ 3፥17 “…ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥” ስለሚል ሁልጊዜ በመንፈስ ድሆች ሆነን እንድንዘጋጅ ጌታ ኢየሱስ ይርዳን።

1. የቅድስና ዝግጅት

በዚህ በመጨረሻው ዘመን ላይ የምንገኝ ዓለምን ሳንመስልና ሳንከተል ፣ የማንም ወገን ሳንሆን በዕብ. 12፥1-2 “….የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤” በዕብ. 6፥11 ላይ ደግሞ “… በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ…” ስለሚል ኢየሱስንና የእምነት አባቶታችንን ተመልክተን፤ እርሱንና ቤተክርስቲያንን በሚወክል ሕይወትና መልክ፤ የኢየሱስ በእኛ መካከል መገኘት እየተሰማን መኖር በዚህ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ተገቢ ነው።

በቅድስና የመዘጋጀት ጉዳይ ሲነሳ በ2ኛ ቆሮ. 6፥14 -18 ላይ እንደተጻፈው ከዓለም መንፈስ፣ ጥምረትና አሠራር ጋር ተቀላቅለንና ተደባልቀን ከምንኖርበት ሕያወት ተለይተን እግዚአብሔር በእኛ መካከል ወደ ሚገኝበትና ወደ ሚከብርበት የቅድስና ሕይወት መሸጋገር አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ቃሉ ‘‘ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ!’’ ይለናል፤ ቅድስና መለየትንም ጭምር የሚያጠቃልል ነውና። ተለይተን ካልወጣን ኢየሱስ በመካከላችን እንዴት ይኖራል?

የእግዚአብሔር ቃል በ2ኛ ቆሮ. 7፥1 “በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።” ስለሚለን ፍጹም ዓለማዊ ከሆኑና የባህል ካባ ከለበሱና በዓለም ላይ እየተከበሩ ካሉ፤ ኢየሱስን እጅግ ከሚያሳዝኑና ክብሩንም ከሚጋፉ ጣኦታትና የአጋንንት አሰራሮች ራሳችንን መለየት ያስፈልገናል። በተጨማሪም የክርስቶስ አካል በምትሆን ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለን ሁላችን ሕያው ለሆነው ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ፣ የቤተክርስቲያንን ድምጽ በመስማት፣ የቤተክርስቲያንን የመንፈስ አንድነት በመጠበቅ በዘር፣ በጎሳ፣ በቀለም እና በሌሎችም ነገሮች ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖር እርስ በርሳችን በፍጹም ፍቅር ተሳስረንና ተያይዘን በክርስቶስ አካል ውስጥ እንድንኖር የእግዚአብሔር ቃል ያዝዘናል።

መጽሐፍ ቅዱስ በዕብ. 12፥14 “…ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።” ስለሚለን መንፈሳችንና ሥጋችንን ከሚያረክሱ ከምናያቸውና ከምንሰማቸው ነገሮች ሁሉ ራሳችንን ለይተን ለኢየሱስ ክርስቶስ መቀደስ አለብን። ለምሳሌ በማህበራዊ ሚዲያ [Social Media] የሚለቀቁ ማየትና መስማት የማይገቡንን ነገሮችን ሁሉ ያጠቃልላል። በዘጸ. 39፥30 እንደተጻፈው የአክሊል ምልከታችን “ቅድስና ለእግዚአብሔር” ይሁን!

2. የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ዝግጅት

በዚህ በመጨረሻው ዘመን በእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለን ሁላችንም ተነጥቀን ወደ ሰማይ ለመሄድ በመንፈስ ቅዱስ በኃይል መሞላት ይጠበቅብናል፤ ይህ ካልሆነ የዓለም ኃይል በእኛ ላይ እያየለ ሄዶ ከንጥቀት ወደ ኋላ ቀርተን ለዓለምና ለሰይጣን መጫወቻ እንዳንሆን በጊዜ ወደ መንፈስ ቅዱስ ፍለጋ እና ጥማት ውስጥ መግባት እና መሞላት ያስፈልጋል።

ሕዝ. 47፥3 ላይ “ሰውዬውም ገመዱን በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ ወጣ አንድ ሺህም ክንድ ለካ፥ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃም እስከ ቍርጭምጭሚት ደረሰ።” ስለዚህ ከቁርጭምጭሚት የጀመረ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት እስከ ወገብ ብቻ ደርሶ ካበቃ ተሻግረን በሥጋ እኛ ወደምንፈልግበት ልንሄድ እንችላለን። እስከ ፍጹም ሙላት ደርሰን ስንሞላ ግን በእኛ ክፉ ፈቃድ አቋርጠን ማለፍ ስለማንችል መንፈሱ ወደሚፈልግበት ቦታና ስፍራ እየመራ ይወስደናል። ስለዚህ ምን ጊዜም የመንፈስ ቅዱስ ጥማትና ሙላት በእኛ ሕይወት እያየለ እንዲሄድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።

በዋናነት ይህች የክርስቶስ አካል የምትሆን እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን ከመነጠቋ በፊት የማጠቃለያውን ዘመን የ11ኛውን ሰዓት ሥራ በመስራት እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን የገባላትን የተስፋ ቃሎች ሁሉ እንድትወርስ ከፍ ያለ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ወርዶ በዘካ.10፥1 ላይ እንደተፃፈው “በኋለኛው ዝናብ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዝናቡን ለምኑ፤ እግዚአብሔር መብረቅ ያደርጋል፤” ስለሚል ወደ መንፈስ ቅዱስ መብረቅ ለመሸጋገር በየአጥቢያውና በየቦታው ብርቱ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ጩኸትና ልመና ውስጥ መግባት ያስፈልጋል።

አሁን ባለንበት ዝናብ ውስጥ ዝናብ እየለመንንና እየፈለግን እግዚአብሔር ከዝናብ ወደ መብረቅ ያሸጋግራል፤ የዚህች ቤተክርስቲያን ማጠቃለያዋ ታላቅ የሆነ የመንፈሳዊ እንቅስቃሴ እንደሆነ በዘካ 4፥7 “ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ፤ ሰዎችም፦ ሞገስ፥ ሞገስ ይሁንለት ብለው እየጮኹ እርሱ መደምደሚያውን ድንጋይ ያወጣል…” የሚል የጸና ታላቅ የተስፋ ቃል ስላለን ለዚህ ሥራ ሁሉ የኃያሉ አምላክ መንፈስ በኃይል መውረድ ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ስለዚህ ፊታችን ወደ መንፈስ ቅዱስ ጩኸት ዳግም ማዞር ያስፈልገናል። ሐዋ. 1፥8 “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥” ይላል። (ዮሐ.3፥34፣ ኤፌ. 3፥16-17)

3. በአገልግሎታችን መትጋት

ሉቃስ 12፥37 “ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁአን ናቸው፤” ማቴ 25፥14 “ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ …ለእያንዳንዱ እንደአቅሙ…” ይላል። ወደ እግዚአብሔር ቤት ተጠርተን የመጣን ሁላችንም ባዶ አይደለንምና እንደየፀጋችንና እንደየአቅማችን የተሰጠን የእግዚአብሔር ፀጋ ፍሬ እንዲያፈራ በፍጹም ትጋት፣ ታማኝነት፣ ቅንነትና ፍቅር በእግዚአብሔር እርሻ ላይ ተሰማርተን እየሰራን እንድንገኝ የእርሱ ፈቃድ ነው። ስንሰራ ግን የዘመኑን ማለቅና የሰዓቱን መድረስ እያየንና እተገነዘብን መሆን አለበት። በ11ኛው ሰዓት ላይ ወደ ጌታ እርሻ የገቡት እንዴት ያለ ትጋትና ታማኝነት ቢያሳዩ ነው በ3 ሰዓትና በ4 ሰዓት የተጠሩትን በመቅደም የተከፈላቸው። እኛም ዛሬ በ11ኛው ሰዓት የተጠራን የእግዚአብሔርን ሥራ በፍጹም ትጋትና ቅንነት ብንሰራ ይሳካልናል። ምክንያቱም ለእግዚአብሔር በ11ኛው ሰዓት ላይም ታላቅና መደምደሚያ ስራ አለው።

በአንጻሩ በኤር. 48፥10 “የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያደግ ርጉም ይሁን፥” ስለሚል ከርግማን ለማምለጥ የእግዚአብሔርን ስራ በትኩረትና በአክብሮት እንድንሰራ ስለሚያስፈልግ ነው።

እግዚአብሔር በእኛ ላይ ያስቀመጠውን ፀጋ ቸል ሳንልና ሳንቀብር “አንተ በጎና ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” እንድንባል በራዕይና በሸክም እየሠራን የእርሱን መምጣት መጠበቅ እንጂ ቀብረን እርሱን መጠበቅ ወደ ጨለማ እንድንገባ ስለሚያደርግ ተጠንቅቀንና ነቅተን ለሰዓቲቱና ለቀኒቱ እንድንዘጋጅ የእግዚአብሔር ቃል በጥብቅ ያስተምረናል። ኢየሱስ ይርዳን!

4. በፍጹም ፍቅር ተሳስረን በአካሉ ውስጥ በመኖር መዘጋጀት

ተነጥቀን ወደ ሰማይ መሄድ የምንችለው በፍቅር ተሳስረን በአካሉ ውስጥ ሆነን የቤተክርስቲያንን የመንፈስ አንድነት በመጠበቅና በማክበር በመኖር ነው።

ኢያሱ ረአብን ያንን ቀይ ፈትል አድርጋ እንድትድን ሲያስጠነቅቃት “ከቤትሽም ደጅ ወደ ሜዳ የሚወጣ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፥ እኛም ንጹሐን እንሆናለን፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር በቤቱ ውስጥ ያለውን አንድ እጅ ቢነካው ደሙ በእኛ ራስ ላይ ይሆናል።” (ኢያሱ 2፥19) አለ። ዛሬ ላለን ሰዎች ስለ ቤተክርስቲያንና በአካሉ ውስጥ ስለመኖር ትልቅ ትምህርትን ይሰጠናል። ይህች ቤተክርስቲያን በመጨረሻው ዘመን ሰማይና ምድር ሲቃጠል ለምህረት ኢየሱስ የሰራት ቤት ስለሆነች ከቁጣው ለማምለጥ በአካሉ ውስጥ በፍቅር ተሳስረን ለመኖር ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይልን ይስጠን። የመጨረሻውን ዘመን ቤተክርስቲያን ከሚያጋጥማት ፈተናዎች አንዱና ዋነኛው የፍቅር መቀዝቀዝ (ማቴ. 24፥12 ፣ ራዕይ 2፥4፣ 1ኛ ቆሮ. 13፥2) በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድ ልብና በአንድ መንፈስ በፍጹም ፍቅር እርስ በርሳችን ተያይዘን በአካሉ ውስጥ በመገኘት ለመነጠቅ መዘጋጀት አለብን። ኢየሱስ ይርዳን።

በአጠቃላይ በዘመን ፍጻሜ ላይ የምንገኝ ሁሉ በራዕይ 22፥14 ላይ እንደተጻፈው “ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው።” ስለሚል ሕይወታችንን ቆም ብለን በማየት በቀሩት ጊዜያት ለቀኒቱና ለሰዓቲቱ እንድንዘጋጅ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይርዳን እላለሁ።

Scroll to Top