ቢሾፕ አንዱአለም ብርሃኑ | የኢ.ሐ.ቤክ ፋይናንስ ሃላፊ

(የእውነት ምስክር መጽሔት 2ኛ ዓመት ቁጥር 1 ነሐሴ 2013 ዓ.ም)

“አቤቱ አንተ ጠብቀን፣ ከዚህችም ትውልድ ለዘላለም ታደገን።” መዝ. 12፥7

“ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ ብሎ መከራቸው” ሐዋ. 2፥40

“ይህች ትውልድ እርሱን የምትፈልግ ናት፣ የያዕቆብን አምላክ ፊት የምትፈልግ” መዝ.24፥6

“እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ … ናችሁ፤” 1ኛ ጴጥ. 2፥9

እነዚህን የእግዚአብሔር ቃላት ስናይ በሁለት አይነት የሚመደቡ ትውልዶች እንዳሉ እናስተውላለን። አንደኛው ከጽድቅ በተቃራኒ የቆመና ለሚድኑት እንቅፋት ወይም አሰናካይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የጽድቅ ወዳጅ የሆነ የተመረጠ ትውልድ ነው። ዳዊት በ 12ኛው መዝሙሩ ላይ “ከዚህችም ትውልድ ለዘላለም ታደገን” ሲል ከጽድቅ በተቃራኒ በቆመው ትውልድ እንዳንበላሽ ሸሽገን፣ ሰውረን፣ ሸፍነን ማለቱ ነው። ላለመበላሸት ከእርሱ ሊያመልጡ የሚገባ ትውልድ አለ፤ አምልጦ የሚወጣና ለትውልዱ የሚተርፍ ትውልድ ደግሞ አለ። ለመሆኑ ከእርሱ ሊያመልጡ የሚገባው አሰናካይ ትውልድ ገጽታዎች ምንድናቸው?

ምሳሌ 30፥11-14 “ (1) አባቱን የሚረግም፣ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ አለ። (2) ለራሱ ንጹህ የሆነ የሚመስለው ከርኩሰቱ ያልጠራ ትውልድ አለ። (3) ከፍ ከፍ ያሉ ዓይኖች ያሉት፣ ሽፋሽፍቶቹም ወደላይ የሚያዩ ትውልድ አለ። (4) ድሆችን ከምድር ላይ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ያጠፋና ይጨርስ ዘንድ ጥርሶቹ ሰይፍ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ አለ”።

እነዚህ አራት ላይጠመዱባቸው የሚገቡ የትውልድ አይነቶችን (ወይም የትውልድ ገጽታዎችን) በአጫጭር አገላለጽ ማስቀመጥ ቢያስፈልግ:-

1. የአባቶች መልካም ታሪክ ፈለግ የሌለው ወይም የማይከተል (A generation with no Legacy)፤

2. ራሱን በትክክል እንዳያይ የተታለለ (A deceived Generation)፤

3.ትዕቢተኛ ወይም ትምክህተኛ (A puffed up Generation)፤ እና

4. በድሆች ላይ ጨካኝና አረመኔ (A cruel and brute Generation) የሆነ

ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል። “ከዚህች ትውልድ ለዘላለም ታደገን” የሚባለው የዚህ አይነቶቹን ያካትታል። አሁን ባለንበት የመጨረሻ ዘመን ጌታ ኢየሱስ በታላቅ ምህረቱ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራው “የተመረጠው ትውልድ” ከዚህች ትውልድ ታደገኝ ብሎ ለዚያ ትውልድ መገለጥ መቻል አለበት።

1. አባቱን የሚረግም፣ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ!

የዚህ አይነቱ አባቱን የሚንቅና የሚያቃልል፣ እናቱንም የማይቀበልና የማያመሰግን በአጠቃላይ ከአባትና ከእናቱ ጋር ቁርኝት የሌለው ትውልድ ነው። ለእርሱ በጣም ቅርብ ከሆኑት ከስጋ ወላጆቹ ጀምሮ ወደኋላ ላለው ትውልድ ስፍራ የማይሰጥም ነው። እንዲህ አይነቱን ትውልድ ለመነሻው ወይም ለመሰረቱ ስፍራና ክብር የማይሰጥ ትውልድ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ስለ አባቶችና እናቶች ወይም ስለቀደመው ትውልድ ሲነሳ በስጋና በመንፈስ ለይቶ ማየት የግድ ነው፤ የእግዚአብሔርም ቃል እንዲሁ ያስቀምጥልናልና።

ማንኛውም ሰው በስጋ የወለዱትን አባትና እናቱን ማክበር፣ መንከባከብ፣ በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ መርዳት እንዳለበት የእግዚአብሔር ቃል ያስተምረናል። ወደ መንፈሳዊው ዓለም ስንመጣ ደግሞ በእግዚአብሔር አሰራር በዳግም ልደት የእግዚአብሔር ልጆች እንዲገኙ በጾም፣ በጸሎት፣ በብዙ ምጥ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በማካፈል የተጋደሉ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “በወንጌል የወለዱ” አባቶችና እናቶች አሉ። ለእነርሱ ተገቢውን ክብርና ስፍራ መስጠት፣ የተከሉአቸውን ሃይማኖታዊ የድንበር ምልክቶች (ዶክትሪኑን፣ ቅድስናውንና ስርዓቱን) መጠበቅ፣ እነርሱን መባረክ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክብርና ሞገስ ያለበት ተግባር ነው።(ኤፌ. 6፥2-3፣ ምሳሌ 30፥17፣ ምሳሌ 22፥28)

በስጋ ወላጆችና ትውልድ እንዳለ ሁሉ በመንፈስም በወንጌል የወለዱ መንፈሳዊ ወላጆችና ትውልድ አለ! በስጋ የወለዱንን ወላጆችና ትውልድን በስጋ ስናከብር በመንፈስ የወለዱንን አባትና እናቶች ደግሞ በመንፈስ እንድናከብር ነው የቃሉ መልእክት። ከዚህ ውጭ ሆኖ አባቱን እያቃለለ እናቱንም ሳያከብር (እንደ አገባቡ በስጋም በመንፈስም) የሚኖር ትውልድ መነሻ የሌለው ወይም መነሻውን የዘነጋ ወፍ ዘራሽ ይሆናል። ለቁም ነገር የሚበቃም አይሆንም።

2. ለራሱ ንጹህ የሆነ የሚመስለው ከርኩሰቱ ያልጠራ ትውልድ

አንድ ሰው ቆሽሾ እያለ ለራሱ ንጹህ የሆነ የሚመስለው እንዴት ነው? ይህ ትንሽ ጥያቄ አይደለም። ከርኩሰት ነጽቶ ራሱን ማዳን የሚፈልግ ክርስቲያን ሁሉ ሊያስብበት የሚገባ ጥያቄ ነው። መልሱ በአጭሩ ከእይታ ችግር የተነሳ ነው የሚል ነው። ራሱን የሚያይበትን መነጽር ማስተካከል ነው ያለበት። በገሃዱ ዓለም አጉልቶ ወይም አሳንሶ የሚያሳይ፣ አቅርቦ ወይም አርቆ የሚያሳይ፣ ከለር ቀይሮ የሚያሳይ … ብዙ አይነት መነጽሮች አሉ። በመንፈሳዊው ዓለምም ሰው ራሱን የሚያይበትን መነጽር ካላስተካከለ ንጹሁ ቆሻሻ፣ ቆሻሻው ንጹህ፣ የከበረው የተዋረደ፣ የተዋረደው የከበረ፣ ትክክሉ ስህተት፣ ስህተቱ ትክክል፣ ጽድቁ ኃጢአት፣ ኃጢአቱ ደግሞ ጽድቅ … ሆኖ ሊታየው ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ አይነት የተበላሹ እይታዎችና ምክንያቶቻቸውም ጭምር ለትምህርት ተጽፈውልናል። አልፎ አልፎ የእስራኤል ልጆች ከእግዚአብሔር ጋር ሳይቀር “የአንተ መንገድ ልክ አይደለም፣ የእኛ መንገድ ልክ ነው” ብለው ሲከራከሩ ጭምር ታይቶአል። (ሕዝ. 18፥25፣ ምሳሌ 16፥2፣ ራዕይ 3፥17-18፣ ኢሳ. 44፥20፣ ሕዝ. 44፥23)

ለሁሉም ሰው የራሱ መንገድ በዓይኖቹ ፊት ንጹህና የቀና መስሎ ይታየዋል። ይህንንም ኃጢአት ወደ ዓለም ከገባ በኋላ በሰው ልጅ ላይ የተጣበቀ የሰው ድካም አድርገን እንውሰድና ከዚህም በተጨማሪ የልብ መታለል ደግሞ አለ። ከተሳሳተ አምልኮ ጋር በተያያዘ አመድ መብላት ትክክል እንደሆነ እስኪያስብ ድረስ የሰው ልብ ሊታለል እንደሚችል የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል። ከእግዚአብሔር ጋር ሳይቀር “እግዚአብሔር ሆይ አንተ የምትለው ትክክል አይደለም፤ እኔ የምለው ነው ትክክል” ብሎ እስከመከራከር ድረስ መድረስም አለ! ይገርማል!

ስለዚህ ሰው በኃጢአትም ሆነ በሰይጣን ሳይታለል በትክክል ራሱን ማየት እንዲችል የትምህርትና የምክር እርዳታ ያስፈልገዋል። ለዚህ ነው እግዚአብሔር በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ይለዩ ዘንድ ሕዝቤን አስተምሩልኝ ያለው። ለእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛ ስፍራ በመስጠት ልቡን ከፍቶ የሚሰማ ሰው ቃሉ ትክክለኛ መስተዋት ሆኖ ራሱን በሚገባ ያሳየዋል። ለዚህ ነው ከእኔ በላይ ጻድቅ የለም ብሎ የሚኖር ሰው ወንጌል (የእግዚአብሔር ቃል) በትክክል ተሰብኮለት ልቡን ከፍቶ ሲሰማ ኃጢአቱ ታይቶት ንስሃ ገብቶ የሚድነው። ከቃሉ በተጨማሪ የእግዚአብሔር መንፈስ የሆድ ጉርጆች ድረስ ዘልቆ ጥልቅ የሆነ ውስጣዊ ማንነትን እስከመፈተሸ ድረስ እንዲሰራ የተሰጠ ታላቅ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። በእግዚአብሔር ቃልና በእግዚአብሔር መንፈስ ራሱን የማያስፈትሽ ሰው ራሱን በትክክል የማየት ዕድሉን ይዘጋል።

“ለራሱ ንጹህ የሆነ የሚመስለው ነገር ግን ከርኩሰቱ ያልጠራ” የሚባለው ትውልድ እንዲህ የእይታ ችግር ውስጥ የወደቀና የተታለለ ትውልድ ነው። “አቤቱ ከዚህች ትውልድ ለዘላለም ታደገን!”።

3. ከፍ ከፍ ያሉ አይኖች ያሉት፣ ሽፋሽፍቶቹም ወደላይ የሚያዩ ትውልድ

ይህ በትዕቢተኝነት ወይም በትምክህተኝነት የሚገለጥ ትውልድ ነው። በትውልድ ደረጃ መጠቀሱ ካልሆነ በቀር ትዕቢት ኃጢአት ወደ ዓለም ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ ላይ ያለ መንፈሳዊ በሽታ ነው። አንድን ትውልድ በሚገልጥ ደረጃ ለምን ተጠቀሰ? የሚለውን ለመረዳት ግን የትዕቢት ወይም የትምክህት መነሻ የሚሆኑትን ነገሮች ማየት ይጠቅማል። (ኤር. 9፥23፣ ዳን. 12፥4፣ 2ኛ ጢሞ. 3፥1-4፣ 2ኛ ተሰ. 2፥4) ከላይ ባሉት ጥቅሶች ውስጥ ያሉትን ቃላት አዋድደንና አስማምተን ስናይ የሰው ፈጣሪ የሆነው አምላክ ጥበብ፣ ኃይል እና ብልጥግና የሚባሉት ሦስት ነገሮች ለሰው ልጅ ዋና የትዕቢት/የትምክህት መነሻ ምክንያቶች እንደሆኑ ነግሮናል። በመጨረሻው ዘመን ደግሞ እውቀትና ከዚህ ጋር ተያይዞም ሃብት/ ባለጠግነት እንደሚጨምር ጠቁሞናል። ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመጨረሻው ዘመን የሰው ልጅ ትዕቢት ወይም ትምክህት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ብዙ አያጠያይቅም። የመጀመሪያው ትዕቢተኛም ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስተካከል የሞከረው ሰይጣን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያውቅ ሁሉ ያውቀዋል። በመጨረሻው ዘመን እርሱ በአካል የሚገለጥበት ሃሳዊ መሲህ መገለጫም በእግዚአብሔር መቅደስ ውስጥ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎ አምላክ ከተባለውና ሰዎች ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ ማድረግ ነው። ሰማይ የነካ ትዕቢት! “አቤቱ ከዚህች ትውልድ ለዘላለም ታደገን!”

ምንጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር አብዝቶ የረዳው ካልሆነ በቀር ሰው ሃብት/ባለጠግነት፣ እውቀት/ጥበብ፣ ኃይል/ችሎታ/ብርታት ሲያገኝ ልቡን ከእግዚአብሔር ላይ አንስቶ በሚታዩት በእነዚህ ነገሮች ላይ ለማድረግ ያዘመመ ተፈጥሮ ያለው ነው። ምናልባት አንድ ማሳያ ቢሆን ዛሬ ከፍተኛ ስልጣኔ ላይ የደረሱት የአውሮፓ ሃገሮች ከጥቂት 100 አመታት በፊት በጣም እግዚአብሔርን የሚፈልጉ፣ የሚያገለግሉ፣ ወንጌልን ለዓለም ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ፣ ሚሽነሪዎችን በዓለም ዙሪያ የሚልኩ፣ የቅድስና ወዳጆች … እንደነበሩ አንዳንድ የታሪክ መጻሕፍት ያሳያሉ (ያኔ በደረሱበት መረዳት ልክ ቢሆንም)። ዛሬ ግን በእውቀት፣ በሃብትና በኃይል አደጉና ከፍተኛ የዓለም ርኩሰት መናኸሪያ ከመሆናቸውም በላይ ቀድሞ የነበሩት የጸሎት ስፍራዎቻቸው ቱሪስት የሚጎበኛቸው ሕይወት አልባ ካቴድራሎች ብቻ እንደሆኑ ይነገራል። ጌታ ኢየሱስን ማምለክም ሆነ መፈለግ ፈጽሞ ሞኝነት ተደርጎ የሚቆጠርባቸው ሃገራት ሆነዋል። ይህ ሃብት፣ የስጋ እውቀት/ጥበብ፣ ኃይል/ችሎታ ያመጣው ነገር ነው። “አቤቱ ከዚህች ትውልድ ለዘላለም ታደገን!”

4. ድሆችን ከምድር ላይ፣ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ያጠፋና ይጨርስ ዘንድ ጥርሶቹ ሰይፍ፣ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ

ሰው መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን አሟልቶ ለመኖር ታታሪ ሰራተኛ እንዲሆን የእግዚአብሔር ቃል ቢያስተምርም፣ ሰውም ምንም ቢጣጣር ሁሉም እኩል ሳይሳካለት ይቀርና አንዳንዱ በስጋው በድህነት ይኖራል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን እግዚአብሔር ለድሃ የሚራራ ሲሆን ልጆቹም እንደርሱ እንዲሆኑለት ይፈልጋል። (ገላ. 2፥10፣ መዝ. 10፥17፣ ዘዳ. 24፥19፣ ምሳሌ 21፥13)

ነገር ግን ድኅነትን ብቻ ሳይሆን ድሃንም ጭምር የሚጠላ ጨካኝ ትውልድ እንደሚኖር ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ይነግረናል። የሚታረሰው መሬትና ሌላም ጥቅም ላይ ሊውል የቻለው የምድር ሃብት በአንድ በኩል እና የሕዝብ ብዛት ካልተመጣጠኑ ብዙ በምድር ላይ የመኖር ስርዓት (የአየር ጠባይ፣ የምድር ዙረት … ወዘተ) ሊቃወስ እንደሚችል የተለያዩ የማኅበረሰብ ሳይንስ አጥኚዎች ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ። ከዚህም በመነሳት ምድር ልትሸከም የምትችለውን ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ከ 9 – 13 ቢሊየን ቢሆን ነው ብለው ግምታቸውን ይናገራሉ። በዚህ የማይስማሙ ቢኖሩም ዋናው ነጥብ ሁሉም ስጋት አላቸው። ስለዚህም የዓለምን ሕዝብ ቁጥር መቀነስ ይገባል በማለት ቁጥሩን ለመቀነስ ብዙ ስውር የጭካኔ ተግባራት በድሃው ላይ ለማድረግ ላይመለሱ ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል። በዚህ ርዕስ ከዚህ በላይ ሳንሄድ በአንድ ዓረፍተ ነገር እግዚአብሔር እንዳስቀመጠልን “ድሆችን … ችግረኞችን … ያጠፋና ይጨርስ ዘንድ ጥርሶቹ ሰይፍ፣ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ” አለ። ማለትም የሰውን ልጅ ለማጥፋት የማይራራና ጨካኝ ትውልድ አለ ማለት ነው። “አቤቱ ከዚህች ትውልድ ለዘላለም ታደገን!”

ማጠቃለያ

ወደ ተነሳንበት ዋና ነጥብ መለስ ስንል አሁን ባለንበት በመጨረሻው ዘመን በትውልድ ላይ እየሰለጠነና ለመሰልጠንም እየሰራ ያለውን መንፈስ ስናጤን እነዚህ ከላይ ዘርዘር ተደርገው የቀረቡትን ነገሮች በጉልህ እንመለከታቸዋለን።

ከዚህም በተጨማሪ በአሁን ጊዜ ያለው ተግባራዊው የክርስቲያን ሕይወት (የወጣቱን ጨምሮ) ከሚጠቃባቸው ነገሮች መካከል ትዕግስት የለሽነት፣ ራስን መግዛት አለመቻል፣ ስልቹነት፣ እግዚአብሔርን መጠበቅ ወይም በእግዚአብሔር ፊት መቆየት አለመቻል የሚጠቀሱ ናቸው። ይህም ዘመኑ ላይ ከተጫነው የፍጥነት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው። አዕምሮ እረፍት የለውም። የሚታዩ ነገሮች በፍጥነት ይቀያየራሉ። እውቀት ቶሎ ይሻራል፣ ቶሎም ይሻሻላል። የልዩ ልዩ አይነት ቁሳቁሶች (የመኪና፣ የኮምፒውተር፣ የልዩ ልዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች … ወዘተ) ሞዴሎች በፍጥነት ይለዋወጣሉ። የልብስ ፋሽን በፍጥነት ያረጃል፣ በፍጥነት ይተካል። የመኖሪያ ቤት ቀለም አንድ አይነት ሳይሆን 3 እና 4 አይነት ከሆነ ቆይቶአል። እርሱም ቶሎ ቶሎ ቀይሩኝ ይላል። አሳብም እንደዚያው ነው፤ አይረጋም። የዘመኑ የኮምፒውተርም ሆነ በአጠቃላይ የሚዲያው ቴክኖሎጂ ይህንኑ የሚያግዝ ነው። የመረጃ ምንጮችና አይነቶች እንዲሁም የማስተላለፊያ መንገዶች ለቁጥር ያታክታሉ። ሁሉንም በእጅ ላይ ባለ ስልክ በኩል ማግኘት ይቻላል። ብቻ በአጠቃላይ ዝም ብሎ ለጥቂት ጊዜ እንኳ በጥሞና ለመቀመጥ እጅግ ፈታኝ የሆነ ዘመን ውስጥ ነን። የችኮላ፤ የፍጥነት! በዚህ የኑሮ ስርዓት ተጽዕኖ ስር የወደቀ ክርስቲያንም ቢሆንለት እግዚአብሔርንም በዚሁ አይነት ቢያፋጥነው ሳይመርጥ አይቀርም። በጣም አሳሳቢ ነው!

2ኛ ጢሞ. 3፥1-5 “በመጨረሻው ቀን … ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ … ገንዘብን የሚወዱ… ትምክህተኞች… ትዕቢተኞች… ተሳዳቢዎች … ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ… ቅድስና የሌላቸው… ፍቅር የሌላቸው… ራሳቸውን የማይገዙ… ችኩሎች… ጨካኞች… በትዕቢት የተነፉ… የአምልኮ መልክ ‹ያ›ላቸው ኃይሉን ግን ‹የካዱ› … ይሆናሉ” ይላል።

በዚህ ዘመን ባለው ያኛው ትውልድ መካከል ደግሞ የእግዚአብሔር የተመረጠ ትውልድ አለ። በዚያኛው ትውልድ (ከጽድቅ በተቃራኒ ያለው) ውስጥ ይኼኛው ትውልድ (የጽድቅ ወዳጅ የሆነው) አለ። ይኼኛው ትውልድ የእውነትን እውቀት የተቀበለ፣ በቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ ተሞልቶ ሰማይን ያሸተተ፣ በቅዱስ አጠራር ተጠርቶ ቅድስናን ልብሱ አድርጎ በቅድስና የሚመላለስ፣ በመንፈስ  እውነተኛውን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያመልክና የእርሱን ቃል ሲሰማ ለዘላለም ከዚህ መንፈስ እንዳይወጣ ሁልጊዜ አምላኩን የሚማጠን፣ በአጠቃላይ አንድ መለኮታዊ ብርሃን የበራለት ትውልድ ነው። ያኛው ትውልድ ደግሞ ዘመኑ ከሚያመጣው ሁሉ ጋር የሚከንፍ፣ አባቱን የሚረግምና እናቱንም የማይባርክ (a generation with no legacy)፣ ለራሱ ንጹህ የሆነ የሚመስለው ግን ከርኩሰቱ ያልጠራ (a deceived generation)፣ በትዕቢትና በትምክህት ተነፍቶ ከእኔ በላይ ላሳር የሚል (a puffed up generation)፣ ማንኛውንም አይነት ጭካኔና አረመኔያዊ ስራ ለመስራት የማይመለስ ትውልድ (a cruel and brute generation) ነው። ይህንን ሁሉ ሲያከናውን ደግሞ ከዘመኑ ፍጥነት ጋር አብሮ እየከነፈ የሚሰራ ትውልድ ነው። “አቤቱ ከዚህች ትውልድ ለዘላለም ታደገን!”

ዳን. 12፥10፣ 2ኛ ጢሞ. 3፥13፣ ሮሜ 8፥21- 22 ላይ ካሉት ክፍሎች የምንረዳው ነገር ሁለቱም የትውልድ አይነቶች በየመንገዳቸው በትጋት እንደሚጓዙ ነው። ያኛው ትውልድ ባያስተውለውም ክፋት እያሰቃየው ነው የሚጓዘው። ሰው ሊያዳምጠው የማይችለው አንድ የነፍስ መቃተት አለው። ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነጻነት ለመድረስ የሚደረግ መቃተት! እግዚአብሔር ፈጣሪው ስለሆነ ነው የእርሱን የውስጡን ድምጽ መስማት ችሎ “ፍጥረት ሁሉ … በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለን” ያለው። ይኼኛው ትውልድ ሁኔታውን ካልተረዳ ያኛውን ትውልድ በሚነዳው መንፈስ ተጽዕኖ ስር ሊወድቅ ይችላል። ከተረዳ ግን ሁለት ነገር ማድረግ ይችላል። አንድም ከዚያኛው ትውልድ ራሱን ለመጠበቅ ይነሳሳል። ሁለተኛም ለዚያኛው ትውልድ ለመትረፍ ይንቀሳቀሳል።

በዚያኛውም ሆነ በዚህኛው ትውልድ ላይ በጎም ሆነ ክፉ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚታትረውና ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው ደግሞ ሚዲያ የሚባለው አካል ነው። ሚዲያው በሚዲያ የሚቀርበውን ዝግጅት ከታዳሚው ጋር የሚያገናኝ ድልድይ እንጂ በራሱ ሕይወት ያለው ነገር አይደለም። ታዳሚው በሚዲያ የሚቀርበውን ዝግጅት እንጂ የዝግጅቱን ምንጭ ወይም ባለቤት የማየት፣ የማወቅም ሆነ የማግኘት ዕድል የለውም። ትውልዱ ለእርሱ እንደሚመች ሆኖ የቀረበለትን “የአዕምሮ ማዕድ” ተቋድሶ ሳያውቀው የምንጩን ዓላማ አስፈጻሚ ወይም ተሳታፊ ይሆናል።

በጭካኔ የመገዳደል ትርዒቶችን አዘውትሮ የሚመለከት ታዳሚ ውሎ አድሮ ራሱም ጨካኝ ሊሆን ይችላል፤ ካልሆነም ቢያንስ በስሜቱ ጭካኔን የሚታገስ ይሆናል። ፖርኖግራፊክ ትርዒቶችን የሚከታተል ታዳሚ በስሜቱ ይረክሳል፣ ያየውንም በተግባር ወደመተርጎም ይሸጋገራል። ሌላም ሌላም።

መልካም ትምህርት የሚሰጡ የሚመስሉና በተለያዩ ሚዲያዎች በኩል የሚሰራጩትንም ነገሮች እንኳ ብንመለከት የሚቀርቡት መረጃዎች “የተራው” ሰው አዕምሮ አገናዝቦና አሰላስሎ የሚጠቅምና የሚጎዳውን ለይቶ ሊጠቀምበት ከሚችለው በላይ በቁጥርም በዓይነትም ብዙ ናቸው። ስለዚህ ይጥቀመውም አይጥቀመው፣ በአግባቡ ይረዳውም አይረዳው ሰው ሁል ጊዜ ያለዕረፍት የጉግል ሱሰኛ እንዲሆን ሆኖአል። እዚህ ላይ “የተራው” ሲባል ሰውን ለማቃለል ሳይሆን <<ሌላ ብዙ ስራ ያለውና ይህንን ሁኔታ ለማጤን በቂ ጊዜም ሆነ የአዕምሮ ዝግጅት የሌለው ማንኛውም ሰው” ለማለት ነው።

ይህ ነገር እጅግ አሳሳቢ መሆኑ የሚታወቀው ክርስቲያን ለጸሎት ተንበርክኮ ወይም መንፈሳዊ ጉባዔ ውስጥ ተቀምጦ ጉግልን ሲጎረጎር ሲታይ ነው። በዚህ ጉዳይ ማንም ላይ ሳይፈረድ ሁሉም ሰው ራሱን በማየት የሚጎዳውን ከሚጠቅመው ቢለይ መልካም ነው። የእግዚአብሔር ቃልም “ንቁ” ይለናል። ያኛውን ትውልድ ተቆጣጥሮና ሱሰኛ አድርጎ እየገዛ ካለ ማንኛውም ነገር ይህ ትውልድ ነጻ መሆን መቻል አለበት።

ኤፌ. 5፥15-16 “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ”።

ቀን ሁሉ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ስለሆነ በራሱ ክፉም ሆነ መልካም የሚባል ቀን የለም። ክፉም ሆነ መልካም የሚሆነው ላዩ ላይ ከተጫነበት ነገር የተነሳ ነው። “እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ” የሚለው እና “ዘመኑን ዋጁ” የሚሉት ሀረጎች በተግባር ልንጠቀምባቸው የሚገቡ ናቸው። የቀኑን ክፋት በማየት ቀኑን መርገም ምንም አይጠቅምም፤ በቀኑ ውስጥ በትክክልና በጥንቃቄ መኖር ግን ዋጋ አለው። ዘመኑን መቀየር አንችልም፤ ዘመኑን መዋጀት ግን በእጃችን ተሰጥቶናል። “መዋጀት” ማለት የሚከፈለውን ዋጋ ከፍሎ ቀኑን ከክፋት ማድረጊያነት አላቅቆ የራስ ማድረግ ማለት ነው።

ያኛው ትውልድ ዘመኑ የሰለጠነበት ሲሆን ይኼኛው ግን ዘመኑን የዋጀ ነው። ዘመኑ ከሰለጠነበት ትውልድ ራስን በመጠበቅ ለዚያኛው ትውልድ መትረፍ ከዚህኛው ትውልድ ይጠበቃል። የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን ያኛውም ትውልድ ቢሆን የዚህኛውን ትውልድ መገለጥ ይጠባበቃል። ምክንያቱም “በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸውና” (መዝ. 4፥6)። በጎውን እየፈለጉ፣ ለእግዚአብሔር ልጆች ያለውን ነጻነት እየናፈቁ ነገር ግን ከጥፋት ባርነት ነጻ መውጣት ሳይችሉ በጨለማው ጉልበትና ተንኮል ተገዝተው ያሉ ብዙ ናቸውና።

በጣም የሚያሳዝነው አንዳንድ ጊዜ በሚገባ ካለማስተዋል የተነሳ ይኼኛው ትውልድ በዚያኛው ትውልድ መንፈስ ተጽዕኖ ስር ሊያውለው በሚችል እንቅስቃሴ ውስጥ ሲታትር መታየቱ ነው። ይህ መታተር በአብዛኛው የሚታየው አሁንም በሚዲያው በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያው በኩል ነው። በበይነ መረብ መገናኛ ከተለያዩ ምንጮች አዕምሮን እንዲማርኩ ተደርገው ተዘጋጅተው በሚለቀቁ ልዩ ልዩ አይነት የጽሁፍ፣ የድምጽም ሆነ የምስል መልእክቶችን በመከታተል ላይ መጠመድ የዘመኑ ሰው መገለጫ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። እዚህ ላይ ማንኛውንም ሚዲያ አስፈላጊ በሆነው መንገድ ብቻ አስተውሎ ለመጠቀም ከረዳ በሚል ጥቂት ስለአዕምሮ እናንሳ። ዓለም የዚያኛውን ትውልድ እንቅስቃሴ ተቆጣጥራ ያለችው በዋናነት በሚዲያ በኩል ስለሆነ አዕምሮአችንን ከዚያ መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው።

በሰውነታችን ውስጥ አንጎልና አዕምሮ እግዚአብሔር የሰጠን ዋና ነገሮች ሲሆኑ ሁለቱ የተያያዙ ናቸው። አንጎል (Brain) የሚባለው በሰውነታችን ውስጥ በአማካይ ከ 1.3 እስከ 1.4 ኪ.ግ. የሚመዝንና 15 ሴ.ሚ. ያህል ርዝመት ያለው ከአንገታችን በላይ የተቀመጠ የሚታይና የሚዳሰስ ተፈጥሮ ያለው ነገር ሲሆን አዕምሮ (Mind) ግን አሳብ፣ ስሜት፣ ፍላጎት፣ ፈቃድና የመሳሰሉ የማይታዩና የማይጨበጡ ረቂቅ ነገሮች በጋራ የሚገለጡበት ቃል ነው ተብሎ በአዋቂዎች ይብራራል። እነዚህ ሁለቱ የሰውን ሁለንተና የሚያንቀሳቅሱ ወሳኝ ክፍሎች ናቸው። እነዚህን መቆጣጠር ከተቻለ መላ ሰውዮውን መቆጣጠር ተቻለ ማለት ነው። ስለዚህ ዓለምና ሰይጣን አዕምሮን ለመቆጣጠር አጥብቀው በትጋት ይሰራሉ። ሰውን የፈጠረው አምላክ ደግሞ ፍጥረቱን ስለሚያውቅ ነው የሚከተሉትን ቃላት አስቀድሞ በመንገር አሳብን፣ አዕምሮን ወይም ልብን አጥብቆ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ያሳሰበው።

2ኛ ቆሮ. 11፥3 “ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሄዋንን እንዳሳታት አሳባችሁ ተበላሽቶ (… so your minds corrupted…) ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽህና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።”

ፊልጵ. 4፥7 “አዕምሮንም ሁሉ የሚያልፍ (…passeth all understanding…) የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን (… keep your hears and minds…) በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”

ቆላ. 1፥9 “…የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አዕምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ (…filled with the knowledge of His will…) እየለመንን ስለ እናንተ ጸሎትን አልተውንም።”

ምሳሌ 4፥23 “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ (… keep thy heart…)፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና”። እዚህ ላይ “ልብ” የሚለው ቃል አሳብ፣ ፈቃድ፣ ማስተዋል…የሚል ትርጉም ያለው ነው።

ይኼኛው ትውልድ ያኛውን ትውልድ በተቆጣጠረው መንፈስ ተጽዕኖ ስር ላለመውደቅ አሳቡ እንዳይበላሽ መጠንቀቅ፣ ልቡና አዕምሮው በክርስቶስ ኢየሱስ እንዲጠበቅ ራሱን መስጠት፣ መንፈሳዊ አዕምሮ የሞላበት እንዲሆን መትጋትና የሕይወት መውጫ የሆነውን ልቡን አጥብቆ መጠበቅ ይኖርበታል። ዓለምም ይህንን ስለምታውቅ የሰዎችን አዕምሮ ለመቆጣጠር በተለይ በሚዲያ በኩል በልዩ ሁኔታ የምትጠቀም መሆኗን መረዳት ያስፈልጋል።

ከዚያኛው ትውልድ ተጠብቀን ለእርሱው ለመትረፍ እንድንችል ቁርጠኛ ውሳኔ በማድረግ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ያስፈልገናል። “አቤቱ ከዚህች ትውልድ ለዘላለም ታደገን” ተብሎ ከተነገረበት ትውልድ ተጽዕኖ ጌታ ኢየሱስ ይጠብቀን! እኛም እንወቅበት። ዕድል ፋንታችን ከዚያ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን “ይህች ትውልድ እርሱን የምትፈልግ ናት” የሚለው ቃል ተፈጽሞልን ለዚያኛው ትውልድም መዳን እንድንተርፍ ጭምር ነው! ከጥፋት ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነጻነት ለመድረስ ለሚቃትተው ለዚያኛው ትውልድ እንድንደርስለት ጌታ ኢየሱስ ዕድል ሰጥቶናል! ይህን ዕድል እንዳናመክነው ጌታ ኢየሱስ ጸጋውን ያብዛልን! ከትውልዱ ተጠብቀን ለትውልዱ እንትረፍ!

Scroll to Top