ቢሾፕ አዲሱ በሪሶ | የምዕራብ አርሲ ቅ/ሰበካ ኃላፊ

የእውነት ምስክር (3ኛ ዓመት ቁጥር 2-ህዳር 2015 ዓ.ም)

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዳዊት ሲናገር “ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ።” ሐዋ. 13፥36 ይላል። ይህ ክፍል እግዚአብሔር አንድን ሰው ለአገልግሎት ሲጠራ አገልግሎቱን የሚፈጽምበት ጊዜ (ዘመን) እና በዚያ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ መፈጸም ያለበትን አገልግሎት (ተልዕኮ) እንደሚሰጠው ያመለክታል። ይህም እውነታ አንድ ሰው ያንን የተሰጠውን ተልዕኮ መፈጸም ብቻ ሳይሆን በተሰጠው ጊዜ የመፈጸም መለኮታዊ ግዴታ አለበት።

በአንድ አካል ላይ ያሉት ብልቶች ሁሉ ሥራቸው አካሉን ማገልገል ቢሆንም እያንዳንዱ ብልት መፈጸም የሚችለው ግን የተሰጠውን ብቻ ነው። እንዲሁም በእግዚአብሔር ለአገልግሎት የተጠራ አገልጋይ ማንም ሊወጣለት (ሊያከናውንለት) የማይችለው፤ በስኬት ሲፈጽመው የሚሸለምበትና ካላሳካ ደግሞ የሚጠየቅበት መለኮታዊ አደራ ከእግዚአብሔር እጅ ተቀብሎአል ማለት ነው (ቆላ.4፥17)።

ዮሐ. 17፥4 ኢየሱስ እንደ አገልጋይ በምድር ሆኖ ስለ ቤተክርስቲያን በጸለየው የምልጃ ጸሎት እንዲህ አለ፦ “እኔ ላደርግ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ አሁንም አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ።” ይላል። ከዚህ ክፍል የምንረዳው በእግዚአብሔር ዘንድ ተዘጋጅቶ የሚጠብቀን ክብር አለ። ለዚያ ክብር ለመብቃት ደግሞ መስፈርቱ በምድር እርሱን ማክበር ነው። እርሱን የምናከብረው ደግሞ በተሰጠን የአገልግሎት ዘመን ውስጥ ልናደርገው (ልንፈጽመው) የሰጠንን ሥራ በመፈጸም ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ የወንጌል አገልጋይ በእግዚአብሔር ተጠርቻለሁ ማለት ብቻ ሳይሆን ያ የጠራው አምላክ ምን እንዲያርግ እንዳዘዘው ለይቶ ማወቅና በጊዜውም ለመጨረስ መትጋት ይጠበቅበታል። አለበለዚያ ተልዕኮው ሳይፈጸም የተሰጠው ጊዜ ያልቅበትና ከተጠያቂነት የማያመልጥ ይሆናል።

በዚህ ላይ ልብ ልንለውና በሚገባ መረዳት ያለብን ቁልፍ ጉዳይ የእግዚአብሔር ሥራ (አገልግሎት) ዘመን ተሸጋሪና ትውልድ ከትወልድ እየተቀባበለ የሚያስቀጥለው ቢሆንም በየዘመናቱ በእግዚአብሔር ተጠርተው ለተነሱትና ለሚነሱትም የተከፋፈለ መሆኑ መታወቅ አለበት። ልክ እንደ ነህምያ “አንተ ከዚህ እስከዚህ አድስ፤ ከአንተ በኋላ የሚነሳ (የሚረከብ) ከዚህ ይጀምርና እስከዚህ ድረስ ያስቀጥል!” ተብሎ ለእያንዳንዳችን ተከፋፍሎ የተሰጠ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ በእግዚአብሔር ተጠርቶ የተላከ አገልጋይ ውድድሩ ከሌላ አገልጋይ ጋር አይደለም፤ ከተቀበለው አደራ ወይንም ተልዕኮውን ከመፈጸም ጋር ነው። መጠየቅ ያለብን “እነ እከሌ የት ደረሱ?” ሳይሆን “እንድፈጽመው ከጌታ የተቀበልኩትን አደራ የት አድርሼዋለሁ? ሳልፈጽመው እንዳላልፍ ወይም የአገልግሎት ጊዜዬ እንዳያልቅብኝ ምን ማድረግ አለብኝ?” የሚል ነው።

መዝ.102፥23-24 “የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ።በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ።” ብሎ መዝሙረኛው የጸለየው ይህንኑ ለእኔ የተመደበውን የአገልግሎት ድርሻዬን ሳልጨርስ ለማለት እንደሆነ እንረዳለን። በተለይ ቤተክርስቲያን እያደገች ስትሄድ የሚታዩ ነገሮች የማይታዩትን ለመሸፈን  መዘርጋታቸው አይቀርም። ዋናውን ነገር ዞር አድርገው ድጋፍ ሰጪዎቹ ዋና ለመሆን መጋፋታቸው የማይቀር ነው። እግዚአብሔር ስለ ቃል ኪዳኑ የሚያመጣቸው ቁሳዊ በረከቶችም ቁመታቸው በጣም ረዝሞ ዋናውን መንፈሳዊና ዘላለማዊ በረከቶችን እንዳይጋርዱ እየተጠነቀቁ በመጠንና በምሳሌነት መኖር ከበረከቶች ሁሉ የሚበልጥ በረከት ነው።

2ኛ ቆሮ.4፥17-18 “የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፣ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን፣ ዘላለምን ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘላለም ነው።” ይላል። የማይታየው የሚታየውን አስገኝቷል፣ እያስገኘም ነው፣ ያስገኛልም። የሚታየው ግን የማይታየውን ማስገኘት አይችልም። በሌላ አገላለጽ የሚታየው የማይታየውን ያስከትላል፤ የሚታየው ግን የማይታየውን ማስከተል አይችልም። በአኗኗራችንም ሆነ በአገልግሎታችን ዋና ነገር ዋና ሆኖ እየመራ ሩጫችንን መፈጸም አለብን።

ሐዋ.6፥1-7 እንደምናነበው ሐዋርያትንም ለትንሽ ጊዜ ሳይረብሻቸው አልቀረም። “አሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው፣ የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገልግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ወንድሞች ሆይ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥብብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፤ በዚህ ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን።” እንደ ሐዋርያት የተላከበትንና እንዲፈጽመው የተሰጠውን ለይቶ የሚያውቅና በዚያ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመፈጸም የሚተጋ አገልጋይ እግዚአብሔር የረዳው አስተዋይና ልባም ባሪያ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ ከማንም በላይ ማለት በሚቻለው ደረጃ ብዙ መስዋዕትነትን የከፈለ፣ የሰበከ፣ ያስተማረ፣ የመራና የብዙዎችን ጥያቄ የመለሰ ሰው ቢሆንም እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ በደማስቆ መንገድ ላይ በብርሃን ተገልጦ ኢየሱስ የሰጠውን (የተቀበለውን) አደራ ከምንም ጋር ከክብር፣ ከሥልጣን፣ ከጥቅም ወዘተ ጋር ሳያወዳድር ሩጫውን እንደጨረሰ እንመለከታለን።

አይደለም ያልተፈቀደው የተፈቀደው እንኳን አይሰለጥንብኝም እስከ ማለት ድረስ ምንም ነገር አሳቡንና ጊዜውን እንዲሻሙበትና ከእግዚአብሔር በተቀበለው ተልዕኮው ላይ የጥያቄ ምልክት እንዲፈጥሩበት ፈጽሞ አልፈቀደም (1ኛ ቆሮ.6፥12፣ 1ኛ ቆሮ. 12፥23)። በ1ኛ ቆሮ. 9፥26-27 “ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፤ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ።” ይላል። ሐዋርያው በዚህ ክፍል እየነገረን ያለው ሌሎችን አድነን እኛ አገልጋዮች እንዳንጣል (እንዳንጠፋ) በጥንቃቄ ለመዳናችን ቅድሚያ ሰጥተን እንድናገለግል ወይም እንድንኖር ሲሆን በአገልግሎታችንም የሚቀድመውን አስቀድመን የተሰጠንና እግዚአብሔር በዘመናችን እንድንፈጽመው በሰጠን ላይ ትኩረት ሰጥተን ለመፈጸም እንድንተጋ ነው።

ሰይጣን የአገልጋይ ሕይወትና አገልግሎት እንዳይሳካ የሚጠቀምባቸው ማጭበርበሪያዎች የተከለከሉ ነገሮችን ብቻ አይደለም፤ እንድናደርግና እንዲኖሩን የተፈቀዱ ነገሮችን ቅደም ተከተል በማዘባረቅ ነው። እግዚአብሔር አስቀድሙ ያለንን ስናስቀድም ሌሎች ነገሮች ይከተሉታል፤ የሚከተለውን ስናስቀድም ግን የሚቀድመው እንዲቀድም የተሰጠ ስለ ሆነ ተከታይ መሆን ፈጽሞ አይችልምና የተላክንበትን ዓላማ ማሳካት አይታሰብም።

እግዚአብሔር አገልጋይን የፈለገበት፣ የጠራበትና የሚጠራበትም ዋና ዓላማ ከላይ እንዳነበብነው ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል ነው። እነዚህ በየትኛውም የሥራ ዓይነትና ብዛት ሊገፉ ወይም ሊሸፈኑ ፈጽመው ልንፈቅድ ወይም ምክንያት ልንሰጥ አንችልም። ሉቃስ 1፥1-4 “ከመጀመሪያ በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን” እንደሚል በዓይን ያዩትና ያስተላለፉልን ሐዋርያት የቃሉ አገልጋዮች ነው የሆኑት። እንግዲህ የቃሉ አገልጋዮች ከሆኑ በቃሉ ውስጥ መኖር መቆፈር (የማጥናት) በቃሉ ዕውቀትና እምነት ማደግ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው ማለት ነው።

አንድ ወቅት ቢሾፕ ደጉ የተናገሩትን (የጻፉትን) እዚህ ላይ ለመጥቀስ እንሞክር። “ከእግዚአብሔር ትምህርት ቤት ምረቃ የለም”። እንግዲህ የእግዚአብሔር ትምህርት ቤት ተማሪ ወይም የእግዚአብሔር ቃል ተማሪ የአንድ ወቅት ተማሪ ሊሆን አይችልም። ይልቁን ተማሪነቱን እየጨመረ መቀጠል ይጠበቅበታል።

ቤተ ክርስቲያን እያደገች ስትሄድ ብዙ የሚታዩና የማይታዩ በረከቶች እንደሚመጡላት የታመነ ነገር ነው። ንብረት ማስተዳደር፣ የግንባታ ሥራዎችን ማከናወን፣ ችግሮችን መፍታት፣ ማደራጀት ወዘተ ሁሉ ጊዜን የሚጠይቁ ብቻ ሳይሆን ጨርሶ መጠቀም የሚፈልጉ ከመሆናቸውም አልፎ ዋናውን ተልዕኮ ማለት ቃሉን ማገልገልና ለጸሎት መትጋትን እስከ መጋፋትና መሸፈንም ድረስ ጫና ይፈጥራሉ። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማገልገል የተጠራ አገልጋይ ሁሉ ግን በሕይወቱና በአገልግሎቱ ዋናን ነገር ዋና አድርጎ ለመቀጠልና ለማስቀጠል በጽናት መትጋት፣ መጨከንም ይጠበቅበታል።

ዕብ. 10፥24 “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ” እንደሚል እንድንነቃቃ ማለት እንድናስተውል፣ ምናልባትም ከተወሰድንበት እንድንመለስ፣ ከመዘናጋትም ነቅተን በዋና ነገር ላይ እንድናተኩር ማለት እንደሆነ እንረዳለን። ይህችም ጽሑፍ እርስ በርሳችን የመተያየት አካል ሆና እንድትቆጠር እግዚአብሔርንም አንባቢውንም እንለምናለን።

በዚሁ ምእራፍ ቁጥር 25 “በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” ይላል። “በእንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው” በቆይታ ዋናውን ነገር ቦታ የሚያስለቅቅ ልማድ እንደሚፈጠር ተፈጥሮም እንደ ታየ እየጠቀሰ ያስጠነቅቃል። “ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ” በማለት ደግሞ በዚህ በመጨረሻው ሰዓት አገልግሎታችንን ለመፈጸም በእንዴት ዓይነት ትጋትና ቅንዓት የፍጻሜውን ዙር መሮጥ እንዳለብን ይመክረናል።

ለምሳሌ አንድ ገበሬ በእርሻው ላይ ሲሠራ ምናልባት ጠዋት ላይ ያንንም ሌላውንም መነካካት ይችል ይሆናል። በአሥራ አንደኛው ሰዓት ግን ማሳደር የሌለበትን ለይቶ በትኩረት ይፈጽማል። እኛም የአሥራ አንደኛው ሠዓት የመከሩ ሠራተኞች እንደ መሆናችን መጠን የሚቀድመውን አስቀድመን (መቅደም ባለበት ነገር ላይ) ጊዜያችንና ጉልበታችን ጸጋችንንም ማፍሰስ ከተጠያቂነት ያድናል ብቻ ሳይሆን አክሊል ያሸልማል።

አስቴ.8፥8-17 የተጻፈውን የእግዚአብሔር ቃል ስንመለከት “…ደብዳቤውንም በንጉሱ ፈረስ ቤት በተወለዱት፣ ለንጉሱም አገልግሎት በተለዩ በፈጣን ፈረሶች በተቀመጡ መልዕክተኞች እጅ ሰደደው።” (ቁጥር 10) ይላል። በቁጥር 14 ላይ ደግሞ “ለንጉሱ አገልግሎት በተለዩ ፈጣን ፈረሶች የተቀመጡት መልዕክተኞች በንጉሱ ትዕዛዝ ተርበትብተውና ቸኩለው ወጡ፤አዋጁም በሱሳ ግንብ ተነገረ።” ይላል። እንደዚህ መርበትበትና መቸኮል ለምን አስፈለገ? ከተባለ መልዕክቱ ጊዜ የተወሰነለት ከዚያ ጊዜ ቀድሞ ካልደረሰ የማያድን ስለሆነ ነው። እስኪ አስቡት? እነዚያ መልዕክተኞች በየመንገዱ ቆመው ስለሚበላና ስለሚጠጣ፣ በመንገድም ስለ ገጠማቸው ነገሮች ማውራት፤ ወይም እርስ በርሳቸው መከራከር፣ መበላለጥ ቢጀምሩና ደብዳቤው ለአንድ ቀን ብቻ ቢዘገይ የደብዳቤው መጻፍ ምንምትርጉምአይኖረውም ነበር። ምክንያቱም የተላከው የማዳን መልዕክት በጊዜ የተገደበ (ቀን የተቀጠረለት) ነበረና።

“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ ያመነ የተጠመቀም ይድናል።” ተብሎ በእኛ እጅ የተላከው መልዕክትስ በጊዜ የተገደበ አይደለምን? ዛሬ ቀን ቤተ ክርስቲያን ብትነጠቅ ነገ በኢየሱስ ስም ለኃጢአት ሥርየት ተጠምቆ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ መዳን እንደማይኖር እርግጥ ነው። ቤተክርስቲያንስ በእኛ ዕድሜ ባትነጠቅ አገልግሎታችንን ለመፈጸም የተሰጠን የአገልግሎት ዕድሜአችንስ ውስን አይደለምን? ምናልባት ልንፈጽመው የተሰጠንን ሳንፈጽም ሊያልቅብን እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ነው። ከላይ ለተጠየቁት ጥያቄዎች መልሳችን “አዎን” ከሆነ እንግዲያውስ የተጠራንለትን ዓላማ በመለየት ዋናውን ነገር ዋና አድርገንና ትኩረታችንን የሚሻሙትን የግራ ቀኝ ድምጾች “ወግዱ” ብለን ልባችንን በመንገዳችን ላይ በማድረግና በመጠበቅ የቀረንን የአገልግሎት ዘመን አገልግሎታችንን ለመፈጸም በትጋትና በጽናት በመጨከን ለድል አክሊል እንሩጥ።

ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን!

Scroll to Top