ወንድም ዳኘው ሙሉነህ | ከአ.አ ሲና አጥቢያ

ከእውነት ምስክር መጽሔት የተወሰደ

(5ኛ ዓመት ቁጥር 1-ነሐሴ 2016 ዓ.ም)

“ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።” ኤፌ 4፥12-13 ጊዜ በተለወጠና በጨመረ ቁጥር ብዙ በዙሪያችን ያሉ ክስተቶች እየተለወጡ ይሄዳሉ። ገበሬው መሬቱን አርሶ የሚዘራው ዘር ጊዜውን ጠብቆ ይበቅላል፣ ጊዜውን ጠብቆ ያድጋል፤ ጊዜውን ጠብቆ ያብባል፣ ጊዜውን ጠብቆ ያፈራል። እነዚህ ሁሉ ሂደቶች በአንድ ጀንበር የሚከናወኑ ሳይሆኑ ጊዜ የሚፈልጉ ናቸው። በማርቆስ ምእራፍ 4፥26-28 ላይ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎአል፤ “በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደዚህ ናት ሌሊትና ቀን ይተኛልም ይነሣልም፥ እርሱም እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል። ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች።”

እግዚአብሔር የፈጠራቸው በዙሪያችን የምናስተውላቸው ነገሮች ሁሉ በጊዜ ሂደት እንዲለወጡ ሆነው ተፈጥረዋል። ህፃናት እድሜአቸው ሲጨምር አካላዊና አእምሮአዊ እድገታቸው እየጨመረ ይሄዳል። ተማሪዎች አመታት ሲጨምሩ የክፍል ደረጃቸውና እውቀታቸው እየጨመረ ይሄዳል። የሰው ልጆች ስልጣኔና ቴክኖሎጂ ዘመን በጨመረ ቁጥር እየረቀቀና እየተሻሻለ ይሄዳል…። ይህ እንግዲህ ጤናማ የሆነውን የእድገት ሂደት ስናይ ነው።

ወደ እውነተኛ ክርስቲያን መንፈሳዊ ህይወት ስንመጣ፣ ጤናማ የሆነ መንፈሳዊ ህይወት በሂደት ወደ ሙላት እንደሚያድግ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ዘመናት ሲለወጡ እግዚአብሔር ከእያንዳንዱ ክርስቲያን የህይወት ለውጥንና ፍሬን ይጠብቃል። ለማደግና ለመለወጥ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ ካሟላ በኋላ ጊዜ ሰጥቶ መልካም ፍሬ ይጠብቃል። ይህ ሳይሆን ሲቀር እግዚአብሔር ማዘን ብቻ ሳይሆን ብዙ በተደረገለት ሰው ወይም ህዝብ ላይ ፍርድ ጭምር እንደሚያመጣ በኢሳይያስ ምእራፍ 5፥1-6 ላይ በቅኔ መልክ የተነገረው ቃል ያረጋግጣል።

ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 12፥48 ላይ “ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል” ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር ከህዝቡ የጠበቀውን ፍሬ ባለማግኘቱ ማዘኑንና በነብዩ በኢሳይያስ በኩል በኢየሩሳሌም ይኖሩ በነበሩ በይሁዳ ሰዎች ላይ የፍርድ ቃል መናገሩን በዚህ በኢሳይያስ ምዕ 5 ላይ እናነባለን። ይህም በታሪክነት ብቻ አንብበን የምናልፈው ጉዳይ ሳይሆን ዛሬም እያንዳንዳችንን የሚመለከተንና ሊገስጸን የተጻፈ ቃል ነው።

በመጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 32 ላይ የምናነበው አንድ ታሪክ አለ። ኢዮብ ያ ሁሉ መከራ በደረሰበት ጊዜ ሊያጽናኑት ከተለያዩ አገሮች የመጡ “የኢዮብ ወዳጆች” የተባሉ 3 ሽማግሌዎች ነበሩ። እነርሱም ቴማናዊው ኤልፋዝ፣ ሹሐዊው በልዳዶስ እና ነዕማታዊው ሶፋር ነበሩ። ሶስቱም ሰዎች የእድሜ ባለጸጎች ነበሩ። ኢዮብን እናጽናናለን ብለው መጥተው የባሰ በቁስሉ ላይ ጥዝጣዜ ጨመሩበት። ከዚህም የተነሳ “ኤሊሁ” የተባለ ከእነርሱ በእድሜ ያነሰ ጎልማሳ (ወጣት) እነዚያ ሰዎች የእድሜአቸውን ያህል ብስለትና ጥበብ የሌላቸው እንደሆኑ ነገራቸው። ኤሊሁ እንዲህ አለ፤ “እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፤ ስለዚህም ሰጋሁ፤ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ። እንደዚህም አልሁ፦ ዓመታት በተናገሩ ነበር፥ የዓመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር። ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል። በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፥ ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም።” (ኢዮብ 32፥1-9)

ኤሊሁ እነዚያ 3 ሰዎች ሽማግሌዎች ስለነበሩ ከእነርሱ ኢዮብን የሚያጽናና ቃል ጠብቆባቸው ነበር። “በእድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም” ማለቱ በእድሜ ማርጀት በራሱ ሰውን ጠቢብና አስተዋይ ሊያደርገው እንደማይችል ያስገነዝባል። ይህ ሰው (ኤሊሁ) እንደተናገረው ሰውን አስተዋይና ጠቢብ የሚያደርገው በእድሜ መግፋቱ ብቻ ሳይሆን የእግዘአብሔር መንፈስ በዚያ ሰው ላይ መኖሩና መስራቱ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ በበኩሉ በጻፋቸው መልእክቶቹ የክርስቲያኖችን በመንፈሳዊ ህይወት አለመብሰል እየጠቀሰ ሲወቅሳቸው እናነባለን። በዕብራውያን ምዕራፍ 5፥12-14 ላይ “ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና…” በማለት ጊዜ አስተምሮንና አሳድጎን እንጂ በከንቱ ማለፍ እንደሌለበት አሳስቦአል። “ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ” የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያን የኖርንበት ቆይታ በጨመረ ቁጥር እኛ ከነበርንበት በጥቂቱም ቢሆን ፈቀቅ ማለት እንደሚጠበቅብን ይጠቁማል። እንግዲህ በዙሪያችን የምናያቸውና የምናስተውላቸው ህያዋን ፍጡራን ሁሉ ሲያድጉ ዝም ብለው በባዶ ነገር አያድጉም። ህያዋን ፍጡራን ሁሉ ለማደግ ምግብ፣ ውሃ፣ ኦክሲጂን፣ ጥበቃና እንክብካቤ ይፈልጋሉ። እግዚአብሔር ሕያዋንን ሁሉ ሲፈጥር እነርሱ ከመፈጠራቸው በፊት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሁሉ አዘጋጅቶ ነው የፈጠራቸው። ክርስቲያንም በመንፈሳዊ ህይወቱ ለማደግ ምግብ ይፈልጋል፣ ውሃም ይፈልጋል፣ ጥበቃና እንክብካቤም ይፈልጋል።

1.ዘመን ሲጨምር የቃል ሙላታችን ይጨምር!

“እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።” 1ጴጥ 2፥1-3

ቃሉን እለት እለት መናፈቅ፣ መስማት፣ ማንበብ፣ መተግበር ያሳድገናል። ለውጪው ሰውነታችን (ለሥጋችን) ከምንመገበው ምግብ ጥቂቱ ብቻ ነው ተፈጭቶና ልሞ ወደ ደማችን ውስጥ የሚገባው። የተቀረው አብዛኛው የሚወገድ ነው። ለዚህ ነው አሁንም አሁንም መብላትና መጠጣት ያስፈለገን። የእግዚአብሔርንም ቃል ስንሰማና ስናነብ ከሰማነውና ካነበብነው ትንሹ ብቻ ነው ውስጣችን የሚቀረው። ደጋግመን ካነበብነውና ከሰማነው ነው በውስጣችን እየጨመረ የሚሄደው። “የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ” ወደሚለው ህይወት በአንድ ጀንበር ልንደርስ አንችልም።

ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ሲመክረው በ1ኛ ጢሞ. 4፥15 ላይ “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፥ ይህንም አዘውትር…” ብሎታል። ምንድን ነው ማዘውተር ያለበት ብለን ከጠየቅን በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 13 ላይ “እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ” ብሎ የመከረውን ምክር እናነባለን። ከመምከርና ከማስተማር በፊት ለራስ ማንበብና መሞላት መቅደም አለበት።

እንግዲህ የቃሉን ወተት መመገብ ሲባል መስማት ብቻ ወይም ማንበብ ብቻ አያሳድገንም። የሰማነውንና ያነበብነውን ቃል አክብረን ከተገበርነው ነው የምናድገው። እግዚአብሔር ለኢያሱ ትልቅ ሃላፊነት ሲሰጠው እጅግ እንዲበረታ ነገረው፤ ሃላፊነቱ ቀላል አልነበረምና (ኢያሱ 1፥6-8)። የኢያሱ ስኬት ምስጢር ሕጉን (ቃሉን) በመጠበቅ ውስጥ የተቋጠረ እንደሆነ እግዚአብሔር ነገረው።

ንጉሱ ዳዊትም በ1ኛው መዝሙር ላይ በክፉዎች ምክር ያልሄደ፣ በዋዘኞች ወንበር ያልተቀመጠ፣…በእግዚአብሔር ሕግ ደስ የሚለውና ሕጉን በቀንና በሌሊት የሚያስብ (የሚያደርግ) በወንዝ ዳር እንደተተከለ ዛፍ እየለመለመና ፍሬአማ እየሆነ እንደሚሄድ በዝማሬ ተቀኝቶአል። ይኸው ንጉሡ ዳዊት በመዝሙር 119፥98-100 ላይ “ለዘላለም ለእኔ ነውና ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ። ምስክርህ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ። ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ…” በማለት የእግዚአብሔር ቃል ከአስተማሪዎቹና ከሽማግሌዎች ይልቅ ጠቢብና አስተዋይ አድርጎ እንደቀረጸው መስክሮአል። ለእኛም በዘመናችን ከቃሉ የሆነ ማስተዋል ይሁንልን፤ ዘመናት በጨመሩ ቁጥር ተንኮል የሌለበትን የቃሉን ምግብ እየተመገብን ለማደግ እንጣር። 

2.ዘመን ሲጨምር የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይጨምር!

የእግዚአብሔር መንፈስ አንድ ሰው በተፈጥሮ ችሎታው መሥራት የማይችላቸውን መሥራት እንዲችል ኃይል ይሰጠዋል፤ በተፈጥሮ ጭንቅላቱ መረዳት የማይችላቸውን የተሰወሩ ነገሮች ይገልጣል፣ ከእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ሁሉና ፈቃዱን ማወቅ እንዲችል አስተዋይ ያደርገዋል። ቀደም ሲል ከኢዮብ መጽሐፍ የተጠቀሰው “ኤሊሁ” የተባለ ሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል” በማለት ማስተዋል እድሜ በመጨመር ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር መንፈስ የሚገኝ እንደሆነ ተናግሮአል።

ሙሴ ለ40 ቀንና ሌሊት በፆምና ፀሎት በእግዚአብሔር ፊት በቆየበት ወቅት እግዚአብሔር የሚነግረውን ሁሉ ዘርዝሮ የሚመዘግብበት ማስታወሻ አጀንዳ ወይም ድምፁን የሚቀርጽበት መሳሪያ ይዞ አልሄደም፤ እግዚአብሔር የሚያሳየውን ዲዛይንና ምስል የሚቀርጽበት የቪዲዮ መቅረጫ መሳሪያም አልነበረውም። ይሁን እንጂ እጅግ ብዙ ልኬትና ዝርዝር ያላቸው 5 መጻሕፍት በጭንቅላቱ ታትመውለት ወደ መኖሪያው ተመልሶ አንድ ሳያስቀር በመጽሐፍ ጽፎአቸዋል። የመገናኛውን ድንኳን አሠራርና ሥርዓት ብቻ እንኳን ብንመለከት ብዙ ዝርዝርና ጂኦሜትሪያዊ ልኬት ጭምር ያለው ነው። በዕብራውያን ምእራፍ 8 ላይ “∙∙∙ በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና” ተብሎ እንደተጻፈ ሙሴ እነዚያን መጻሕፍት ሁሉ ዘርዝሮ የጻፈው ፈርኦን ቤት በተማረው የተፈጥሮ እውቀቱ ተጠቅሞ ሳይሆን በተራራው ላይ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ አሠራር እጅግ አስደናቂ ነው።

በአዲስ ኪዳን ዘመንም እነ ሐዋርያው ጴጥሮስ መጻሕፍትን ያልተማሩ ሰዎች ሆነው ሳለ ካልተማሯቸው መጻሕፍት ታላላቅ ምስጢራትን እየጠቀሱ እግዚአብሔር በሰጣቸው መገለጥ ወንጌልን ሰብከዋል፣ ቅዱሳንን መክረዋል፣ አጽናንተዋል። መንፈስ ቅዱስ በወረደበት በበአለ ሃምሳ ቀን በብዙ ሕዝብ ፊት ቆሞ፣ በሆነው ነገር ግራ ተጋብተው ለነበሩት ሕዝብ “በነቢዩ በኢዩኤል የተነገረው ትንቢት ተፈፀመ” አላቸው። ከበአለ ሃምሳ በፊት ግን ሐዋርያው ጴጥሮስ የኢዩኤል ትንቢት ስለ መቼ እንደተነገረ ብቻ ሳይሆን መጽሐፉን ራሱን ከነአካቴው የማያውቀው እንደነበረ የአይሁድ ጸሐፍት መስክረዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ እስከ 3ኛ ሰማይ በእግዚአብሔር ራዕይ ተነጥቆ በመሄድ ብዙ ጥልቅ የሆኑ ምስጢራት ተገልጠውለት ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የምትመራባቸውን እጹብ ድንቅ የሆኑ መርሆዎች እግዚአብሔር በሰጠው መገለጥ ጽፎልናል። ብዙ ሰዎች አዲስ ኪዳን በአብዛኛው የጳውሎስን አመለካከት የያዘ የፍልስፍና መጽሐፍ ይመስላቸዋል፤ ይህ ግን የተሳሳተ አመለካከት ነው። ይኸው ጳውሎስ 1ኛ ቆሮ. ምዕራፍ 2 ላይ እንዲህ በማለት ጽፎአል፤ “መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም” በማለት መንፈስ ቅዱስ ምስጢራትን እንደሚገልጥ አረጋግጦአል። ስለዚህ በጳውሎስ የተሰበከው ወንጌል የራሱ ፍልስፍና ወይም ከገማልያል የተማረው የኦሪት ትምህርት ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ ከሰማይ የገለጠለት እንደሆነ ቅዱሳን እንድናስተውል መክሮአል። እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ የክርስቲያኖችን የልብ ዓይኖች በማብራት ምንና ምን ነገሮችን እንድናውቅ እንደሚያደርገን በኤፌሶን ምዕራፍ 1፥17-19 ላይ እናነባለን። ዘመኑ ይለወጥ፥ ይጨምር። በዚያው ልክ ደግሞ በእኛ እግዚአብሔር የሚያሳድረው መንፈስ ከቁርጭምጭሚት ወደ ጉልበት፥ ከጉልበትም ወደ ወገብ፥ ከወገብም ወደ ሚዋኝበትና መሻገር ወደማይቻልበት ደረጃ እንዲያድግልን ብርቱ ናፍቆትና ልመና ሊኖረን ይገባል።

3.ዘመን ሲጨምር ጸጋችን ይደግ!

የሰውን ተፈጥሮአዊ ሰውነት እንኳን ስናይ ስናሠራውና ሳናሠራው እኩል አይዳብርም፣ አይቀለጥፍም። ወታደሮች ጡንቻቸውንና አእምሮአቸውን ለማዳበርና ለማነቃቃት በከባባድ ስልጠና ውስጥ ማለፍ ግድ ይላቸዋል። አትሌቶች እልህ አስጨራሽ ስልጠና (ልምምድ) ሳያደርጉ በዘፈቀደ በሩጫ ሜዳ ላይ ቢሰለፉ ተወዳድረው ማሸነፍ የማይታሰብ ነው። የሰው ጡንቻ ካላሠሩት የሚሟሽሽ፣ ካሠሩት ደግሞ የሚፈረጥም ነው። የሰው አእምሮም እንደዚሁ ሲያሠሩት የሚሠራ፣ ካስተኙትም የሚተኛ ነው።

እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በሰው ላይ የሚያስቀምጠው ጸጋም ከዚህ ከተፈጥሮአዊ ሂደት ጋር የሚመሳሰልበት ነገር አለው። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ 11፥14-15 ላይ “ተፈጥሮ እንኳን አያስተምራችሁምን?” በማለት ከተፈጥሮ የምንማራቸው ቁም ነገሮች እንዳሉ ጽፎአል። በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25፥14-27 የተጻፈው የጌታ ኢየሱስ ምሳሌአዊ ትምህርት እግዚአብሔር በላያችን የሚያስቀምጠው ጸጋ ካሠራነው የሚያድግ፣ ቀብረን ካስቀመጥነው ደግሞ የማይጨምርና በኋላ ላይ የሚወሰድ መሆኑን ያስተምረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን የመከረው ምክር ይህንን እውነት ያረጋግጣል። “በትንቢት ከሽማግሌዎች እጅ መጫን ጋር የተሰጠህን፥ በአንተ ያለውን የጸጋ ስጦታ ቸል አትበል።” (1ኛ ጢሞ 4፥14። 2ኛ ጢሞ. 1፥6)

ሐዋርያው ጳውሎስ ጸጋን በእሳት መመሰሉ የሚገርም ነው፤ እሳት ካዳፈኑት ባይጠፋም አቅም የሌለው ሆኖ በአንድ በተወሰነ ስፍራ ተወስኖ የሚቀመጥ፣ ካቀጣጠሉት ደግሞ ታላላቅ ጫካዎችን እስኪያወድም ድረስ ኃይለኛ የሰደድ እሳት የሚሆን እንደሆነ እናስተውላለን። የዓለም ገንዘብ እንኳን ሲሰሩበት ነው እየበዛ የሚሄደው፤ ከዓለም ሀብት ይልቅ ልናሠራውና ልናሳድገው፣ እግዚአብሔር ለሰጠበት ዓላማ ልናውለው የሚገባው ግን እግዚአብሔር በቸርነቱ የሰጠን የጸጋ ስጦታ ነው። ጊዜ በጨመረ ቁጥር የተሰጠንን ጸጋ ለይተን አውቀን እንድናሰራውና ጸጋችን እየጨመረ እንዲሄድ ጌታ ኢየሱስ ይርዳን።

4.ዘመን ሲጨምር የጸሎት ጉልበታችን ይጨምር!

ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በቀደሙት አመታት ብዙ ጸሎት ቤቶች አልነበሯትም። ነፍሳት ግን ከየአቅጣጫው ይጎርፍላት ነበር። እነዚህ ነፍሳት በየዛፉ ሥር፣ በደሳሳ ጎጆዎችም እየተሰበሰቡ ጌታ ኢየሱስን በታላቅ ፍቅርና መሰጠት ሲያመልኩ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል እየወረደ በመካከላቸው ልዩ ልዩ ተአምራት እያደረገ ህዝቡን ያጸና ነበር፣ የሚድኑትም እለት እለት በእነርሱ ላይ ይጨምሩ ነበር።

ባሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ባርኳት ብዙ ጸሎት ቤቶች ተሠርተዋል፣ በርካታ አገልጋዮችም አሏት። ስለዚህ በረከት ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ይክበር። የተገነቡት ጸሎት ቤቶች ግን ገና እንደሚገባው በአዳዲስ ነፍሳት አልተሞሉም። የጸሎት ጉልበት ያስፈልገናል!

ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ላይ ታሪካቸው የተፃፈው ሁለት የእድሜ ባለጸጎች ያስገርሙኛል። ሽማግሌው ስምዖን “ጻድቅና ትጉህ” እንደነበረ ተጽፎለታል። ይህ ትጉህ ሰው በጌታ የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር። እንደ ኦሪት ሕግ ሥርዓት ሊፈጽሙ ዮሴፍና ማርያም ህፃኑን ኢየሱስን ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ በሄዱ ጊዜ፣ ያ በጌታ የተቀባውን የምታይበት ቀን ዛሬ ነው ተብሎ በእግዚአብሔር ተነግሮት ወደ ቤተ መቅደስ ወጣ። ህፃኑንም (ጌታ ኢየሱስን) አቅፎ “ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤..” አለ። ይህ ሰው ጻድቅና ትጉህ (በጸሎት የተጋ) ነበር፣ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበር። ካህንም ምንም እንደነበረ አልተጻፈም። ሆኖም ለብዙ የሃይማኖት መምህራን የተሰወረ የመሲሁ መምጣት የተገለጠለት ሰው ነበር። ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ጌታ ኢየሱስን “የጸራቢው የዮሴፍ ልጅ” ብለው ሲረዱት ስምኦን “በሰዎች ሁሉ ፊት የተዘጋጀውን የእግዚአብሔር ማዳን አየሁ” አለ።

ሐና የተባለችም ነቢይት እድሜዋ ከ90 አመት ያለፋት ሆና ጌታ ኢየሱስን ወደ መቅደስ ባስገቡት ጊዜ ቀርባ አመሰገነች። የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ኢየሱስ ትናገር ነበር። እነዚህ ሁለት በእድሜ የገፉ ሰዎች የነበራቸው የጋራ የሆነ ቁም ነገር ትጋታቸው ነው። ለሌሎች የተሰወረ ይህን የመሰለ ታላቅ ምስጢር ለእነርሱ የተገለጠው እግዚእሔር ስለሚያዳላ አይደለም። እነዚህ ጻድቃን ሰዎች አጥብቀው ስለፈለጉትና ስለተከተሉት ነው። የጸሎት ህይወታችን ባለበት እየተንፏቀቀ ዘመናት ይፈራረቁብን ወይስ እንደ ስምኦንና ሐና ትጋታችን ከአመት አመት እየጨመረ ይሂድ?

5. ዘመን ሲጨምር የወንጌል ጉልበታችን ይጨምር

“ነገር ግን ተናገር፣ ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ህዝብ አሉኝና” [ሐዋ. 18፥9-10]

የምስክርነት ህይወት ቀደም ሲል በዚህ ጽሁፍ ከተጠቀሱት የቃል ሙላት፣ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ ጸጋን ማነሳሳትና ጸሎት ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ግልጽ ነው። የእግዚአብሔር ቃል በሮሜ ምዕራፍ 10 ላይ “ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፣ በአፉም መስክሮ ይድናል” ይላል። የምስክርነት ህይወት ያለው ሰው ሁለት ሥራ ነው የሚሠራው፤ ሌላውን ሰው ወደ ኢየሱስ አምጥቶ እንዲድን ይረዳል፣ ራሱን ደግሞ ያድናል። በዳንኤል ምዕራፍ 12፥3 ላይ “ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ።” ተብሎ ተጽፎአል።

ወንጌልን የሚናገር ሰው ትልቅ ድፍረት እያገኘ፣ የበለጠ እየበረታ ይሄዳል። በወንጌል ምስክርነት ወቅት የሚነሱትም ጥያቄዎች እለት እለት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ስለሚያደርጉት በዶክትሪን እውቀት የበረታ ይሆናል። እግዚአብሔር በእያንዳንዳችን ያስቀመጠው ቃልና መንፈስ ወደ ሌላ ሰው ሲተላለፍ እየተጨመረ የሚሄድ፣ ውስጣችን አፍነን ከያዝነው ደግሞ በጊዜ ሂደት የሚወሰድብን ነው። በመጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 11፥24 ላይ “ያለውን የሚበትን ሰው አለ፥ ይጨመርለታልም፤ ያለ ቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ፥ ይደኸያልም” ተብሎ ተጽፎአል።

ለማጠቃለል፣ ዘመን ሲለወጥና ሲጨምር የእኛም ህይወት መለወጥና መጨመር እንዲችል ቃሉን እለት እለት ለማንበብ እንወስን፤ መንፈሱን እለት እለት እንጠማ፣ እንፈልግ። መንፈስ ቅዱስን ከሚያሳዝኑ አካሄዶች ራሳችንን እንለይ፤ እግዚአብሔር በላያችን ያስቀመጠውን ጸጋ ለይተን በማወቅ እናሠራው፣ እናነሳሳው። እንደ ስምዖንና ሐና በጸሎት የተጋን ሰዎች እንሁን፤ ወደ እግዚአብሔር ፊት መቅረብ ያለበት ብዙ ጥያቄ (ልመና) አለንና። እግዚአብሔር በውስጣችን ያስቀመጠውን የወንጌል ዘር አውጥተን እንዝራው፤ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ ይሆንልናል። ክብር ለጌታ ኢየሱስ ይሁን።

Scroll to Top