ቢሾፕ ጌታሁን ላምቤቦ | የኢ.ሐ.ቤ.ክ ዋና ጸሐፊና የሃዲያ ቅ/ሰበካ ኃላፊ

መግቢያ

እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን ከሰጣቸው ብዙ ስጦታዎች ውስጥ የቤተክርስቲያን አመራርና አስተዳደር (Leadership and Administration) በዋናነት ሊጠቀስ ይችላል። ምክንያቱም ወደፊት የሚያራምዱ መሪዎችና መልካም አስተዳዳሪዎች ባይኖሩ ቤተክርስቲያን ትኖራለች ብሎ ማሰብ የሚከብድ ነውና። ይህም ሲባል አስመሳይና አምባገነን መሪዎችና አስተዳዳሪዎች የሚያደርሱት ጥፋት ቀላል ያለመሆኑ ሳይካድ ማለት ነው። በመሆኑም በዚህ አጭር ጽሑፍ የቤተክርስቲያን አመራርን እና አስተዳደርን በጥቂቱ ለመዳሰስ ተሞክሮአል። አመራር እና አስተዳደርን (Leadership and Administration) የሚያመሳስላቸው ጥቂት ነጥቦች ቢኖሩም የጎሉ ልዩነቶች ስላሉአቸው ለያይቶ ማየቱ ተገቢ ይሆናል።

የቤተክርስቲያን አመራር (Leadership)

የቃሉ ትርጉም እንደሚያስረዳው አመራር ማለት ከፊት ለፊት መሆን፣ መምራት፣ በሁሉ ነገር መቅደም፣ ራዕይ ማሳየት፣ ማስተማር፣ መልካም ምሳሌ መሆን፣ በዚህም ምክንያት ወደ መደመጥና መሰማት ደረጃ ላይ በመድረስ ተቀባይነት እስከ ማግኘት ድረስ የሚያበቁ ተግባራትን የሚያከናውን አካል ነው ማለት ይቻላል። ለዚህ ማስረጃ የሚሆንልን በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ስለመልካም መሪዎች ከተጠቀሱት ክፍሎች ሁሉ በቀጥታ ተጽፎ የምናገኘው በመሳፍንት 5፥2 እና ቁጥር 9 ላይ የሚገኘው ነው። እንዲህ ይላል፦ “በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥ ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥ እግዚአብሔርን አመስግኑ። … ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥ በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፤ እግዚአብሔርን አመስግኑ።” ከዚህ ክፍል በቀጥታ ወይም ቃል በቃል የምንረዳው ነገር መሪዎች በትክክል ከመሩ ሕዝቡ ሙሉ ሕይወቱን ኑሮውን ጭምር ሳይሰስት በፈቃዱ ሊሰጥ እንደሚችል ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስም በገላትያ 4፥14-15 “…በሥጋዬም ፈተና የሆነባችሁን ነገር አልናቃችሁትምና አልተጸየፋችሁትም ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ አዎን እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ። …ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ።” እስኪል ድረስ ተወዳጅነት ያገኘ መሪ ስለነበር ምዕመናኑ እርሱ ከሚጠብቀው በላይ ያደርጉለት፤ እንደ መልአክም ይቀበሉት እንደነበር በራሱ አንደበት መስክሮአል።

በሌላ በኩል ደግሞ ትክክለኛ ስላልሆኑ መሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱት ክፍሎች ውስጥም በጥቂቱ ጠቁሞ ማለፉ አስተዋይ ልቦና ላለው መሪ ለጥንቃቄ ይጠቅማል። ለምሳሌ ያህል፦ አንቀጥቃጭ መሪዎች አሉ። ሕዝ.27፥28 በማስፈራራት የሚመሩ መሪዎች እንዳሉ ያመለክታል። ፈሪሳውያን ዓይነት ዕውር መሪዎችም አሉ። ማቴ. 23፥124 ራዕይ የሌላቸው መሪዎችም እንደሚገኙ ያሳያል። ይሁዳ የሰቃዮች መሪ ነበር (ሐዋ. 1፥16)። ብዙ ሕዝብ የሚያስከትሉ በክፋት የተሞሉ የጥፋት መሪዎችም ይኖራሉ። የሚያስቱ መሪዎችም ተጠቅሰዋል (ኢሳ. 9፥16)። ወደ እውነቱ መምራት ሲገባቸው ከመንገዱ በማስቀረት ወደ ጥፋት የሚወስዱ መሪዎችም እንደሚገኙ በብዙ ቦታዎች ተመላክተዋል።

ርዕሰ ጉዳያችን ወደሆነው ወደ ቤተክርስቲያን መልካም መሪዎች ትኩረት ስናደርግ፦ በማቴዎስ ወንጌል 20፥26 ላይ “በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን” ተብሎ እንደተጻፈው የቤተክርስቲያን መሪዎች የሚጠበቅባቸው የመጀመሪያው ነገር በተግባራቸው ሁሉ ዋናውን መሪ ኢየሱስን ለመምሰልና እርሱን ለማሳየት መጣጣር ነው። በ1ኛ ጴጥሮስ 2፥21 ላይ እንደተጻፈው ፍለጋውን መከተል ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው መሪ ወይም አለቃ መሆኑን ለማሳየት አይደለም። የጌታ የኢየሱስ መምጣት በማቴ 20፥28 ላይ በግልጽ ተቀምጧል፦ “እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” የቤተክርስቲያን መሪዎች ዋና ሥራ በዕብራውያን 13፥16 ላይ “…ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ” እንደሚለው ቃል ቤተክርስቲያንን ነፍሳቸውን እስከ መስጠት ድረስ ማገልገል እንጂ በቤተክርስቲያን መገልገል አይደለም። ቢሆን ቢሆን እንኳን ማገልገሉ ቀድሞ መገልገሉ ቢከተል ይሻላል ተብሎ ሊታሰብ ይችላል።

በነገራችን ላይ፦ መሪ ጉልበት አለው፣ ማለት ጡንቻ ሳይሆን የስበት ኃይል አለው- በመልካም ብቻ ሳይሆን በክፉም! በያዕቆብ መልእክት 3፥4 ላይ “እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ።” በማለት የመሪን ወሳኝነት ይናገራል። ወደ ሚፈለገው ሥፍራ ለማድረስ መምራት የግድ ነው ማለት ነው።

በመሪነት ዙሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተደነቁት መሪዎች ውስጥ ሙሴን፣ ኢዮሳፍጥን እና ነህምያን በምሳሌነት መርጦ መጥቀስ ይቻላል።

እስራኤልን ከግብጽ ወደ ከነዓን እንዲያወጣ በእግዚአብሔር የተመረጠው ሙሴ ሕዝቡን በመራበት ዘመን ሁሉ ሳያመነታና አስገራሚ የእምነት ቃላትን በማውጣት እስራኤልን እያደፋፈረ በከፍተኛ ወኔ ሲመራ ታይቶአል። እንዲህ እያለ፦ “ሙሴም ለሕዝቡ፦ አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ አላቸው” ዘጸ. 14፥13-14

ኢዮሳፍጥም የሚደንቅ የእምነት ሰውና በሕዝቡም ዘንድ ተቀባይነት የነበረው መሪ ነበር። በ2ኛ ዜና 20፥20 ላይ፦ “ማልደውም ተነሡ፥ ወደ ቴቁሔም ምድረ በዳ ወጡ፤ ሲወጡም ኢዮሣፍጥ ቆመና፦ ይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፥ ስሙኝ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፥ ትጸኑማላችሁ፤ በነቢያቱም እመኑ፥ ነገሩም ይሰላላችኋል።” በማለት ኢዮሳፍጥ በመሪነቱ ሕዝቡ በአምላካቸው  በእግዚአብሔር እንዲታመኑ፤ በእምነታቸው እንዲጸኑ፤ የነቢያቱን የትንቢት ቃል እንዲያምኑ በማነሳሳት አስገራሚ ድል እንዲቀዳጁ አድርጎአቸዋል።

ነህምያም ባለ ራዕይ፣ ጠንቃቃ፣ ውሳኔ ሰጭ፣ ከአድልዎ የጸዳና ጠንካራ የአስተዳደር ሰው ነበር። ይህንንም ለመንገዱ ደብዳቤ በማጻፍ፣ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ሦስት ቀናት ያህል ተቀምጦ በማሰብ፣ ቆራጥና ብርቱ ውሳኔ በመስጠት፣ ማንንም ሳይፈራ አደብ በማስያዝ፣ የሥራ ክፍፍልም በማድረግ የተዋጣለት መሪና ጠንቃቃ አስተዳዳሪ መሆኑን መጽሐፈ ነህምያ አሳይቶናል።

በተቃራኒ ጎኑ ደግሞ አሮናዊ አመራርና ሳኦላዊ አስተዳደርም አለ፤ እነዚህ ሁለቱ ልቅና መረን፣ ራዕይ አልባ አመራር የነበራቸው ሲሆኑ ሁለቱም በሕዝብ የተመሩ፣ ማለትም ሕዝቡን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ መምራት ያቃታቸው መሪዎች እንደነበሩ እናያለን- ቀጥሎ እንደሚነበበው!

ዘጸአት 32፥4 ላይ፦ “ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም፦ እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አላቸው።” ይላል መሪ የተባለው አሮን።

እንዲሁም በ1ኛ ሳሙኤል 15፥20-21 ላይ፦ “ሳኦልም ሳሙኤልን፦ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቻለሁ፥ እግዚአብሔርም በላከኝ መንገድ ሄጃለሁ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጥቻለሁ፥ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ። ሕዝቡ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በጌልገላ ይሠዉ ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን በጎችንና በሬዎችን ከምርኮው ወሰዱ አለው።” በማለት ሳኦልም መምራቱን ዘንግቶ በህዝቡ በመመራት እርምን መርጦ ውድቀቱን አፋጠነ።

እንግዲህ በመልካምነት የሚጠቀሱ እንደ ሙሴ፣ ኢዮሳፍጥ እና ነህምያ ዓይነቶችን፤ በመጥፎ አመራራቸው ደግሞ ስማቸው የሚነሳ እንደ አሮን እና ሳኦል ዓይነት የሆኑ መሪዎችንና አስተዳዳሪዎችን በምሳሌነት አይተናል። ታዲያ እነዚህን መሪዎች አይቶ ማለፍ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ወስዶ በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሪዎችንና በመልካምነት የሚታወቁ አስተዳዳሪዎችን ፈለግ መከተሉ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።

ከላይ በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ቤተክርስቲያን አመራር ላይ ብቻ ካተኮረች፣ አብዛኛውን ጊዜ በማስተማር፣ በማሰልጠን፣ በመምከር፣ በመጸለይ፣ በአጠቃላይ ከፊት ሆኖ በማሳየት ላይ ታዘወትራለች። እንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ አመራር ለጤነኛ ተከታዮች ጥቅሙ እጅግ ብዙ ነው። ነገር ግን እርማትና ክትትል፣ እንዲሁም ቁጥጥርና ግሳጼ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በግልባጩ ማለትም በሌላ ገጽታው የቤተክርስቲያንን አስተዳደር ማጠናከር የግድ ይሆናል።

የቤተክርስቲያን አስተዳደር (Administration)

የቤተክርስቲያን አስተዳደር ከቤተክርስቲያን አመራር በተለየ መልኩ መጎብኘትን፣ መከታተልን፣ መቆጣጠርን፣ ማረምን፣ ማስጠንቀቅን፣ መገሰጽን፣ አልፎም ተገቢ ሆኖ ሲገኝ ማውገዝንም ሆነ ማሰናበትን የሚያካትት ነው። በአጠቃላይ የቤተክርስቲያን አስተዳደር ወደ ኋላ ተመልሶ መመልከትን እና አይቶም ማድነቅን፣ ማበረታታትን፣ በተገኘው ውጤት ምክንያት ማመስገንንም ሆነ ማበረታቻ መስጠትን ሊያካትት ይችላል። አልፎም አስተዳደር የቤተክርስቲያን መተዳደሪያ ደንብን ተከትሎ በኃላፊነት ደረጃ ወይም በሹመት ማሳደግን ጭምር የሚመለከት ሥራ የሚያከናወንበት እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ ክፍል ነው።

በቤተክርስቲያን አስተዳደር ትኩረት ከሚሰጣቸው ሥራዎች ውስጥ የሚከተሉት በዋናነት ሊካተቱ ይችላሉ።

ጉብኝት

ሐዋርያው ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ 15፥36 ላይ፦ “ከጥቂት ቀንም በኋላ ጳውሎስ በርናባስን፦ ተመልሰን የጌታን ቃል በተናገርንበት በየከተማው ሁሉ ወንድሞችን እንጐብኛቸው፥ እንዴት እንዳሉም እንወቅ አለው።” ይላል። በዚህ ጉብኝት ጉዞ ወቅት ከሚያዩትና ከሚሰሙት የተነሳ ብዙ ነገር ሊያስተካክሉ እንደሚችሉ ማንም ሰው መገንዘብ ይችላል። አንድ ወቅት ለጉብኝት በሄድኩበት ቅርንጫፍ አጥቢያ ቤቱን ከሞላው ሕዝብ መባ የሚሰበስበው አንድ ሰው ብቻ ነበርና ቢያንስ አራት መባ ሰብሳቢዎች እንዲሆኑ ያደረኩት ትዝ ይለኛል።

ክትትል

ሐዋርያው ጳውሎስ በወንጌል ልጁ የሆነውን ጢሞቴዎስን በ1ኛ ጢሞ. 6፥11 ላይ፦ “አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል።” ብሎት ነበር። ከቆይታ በኋላ በ2ኛው መልእክቱ ምዕራፍ 3፥10 ላይ፦ “አንተ ግን ትምህርቴንና አካሄዴን አሳቤንም እምነቴንም ትዕግሥቴንም ፍቅሬንም መጽናቴንም ስደቴንም መከራዬንም ተከተልህ፤” በማለት መከተሉን በመከታተል አረጋግጦ “ተከተልህ” ብሎ ሲያደንቀው እናያለን።

ቁጥጥር

ማቴዎስ ወንጌል 25፥14-30 የተጻፈው ቃል እንደሚያስረዳን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ባስተማረን ምሳሌያዊ ትምህርቱ፦ “ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። … ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው።” ያለውን ክፍል እናገኛለን። ይህም ለሚመለከተው ክፍል ሥራ ከሰጡ በኋላ የቁጥጥር ሥርዓትን በመዘርጋት መቆጣጠር የግድ ማስፈለጉን ያሳየናል። በዚሁ ክፍል በተካሄደው የቁጥጥር ወይም የፍተሻ ሥራ ሁለቱ ታማኞች መክሊታቸውን አትርፈው ሊሸለሙ በቅተዋል፤ “ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።” ያ ያልታመነውና መክሊቱን ቀብሮ የተገኘውም ባሪያ በፍተሻው ተደርሶበታል። “ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን?… የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ይላል።

ችግርን መፍታት

በቀደመችው ቤተክርስቲያን የገጠመውን ውዝግብ ለመፍታት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ፈጣን እርምጃ በመውሰድ በወቅቱ የተከሰተውን ችግር ፈትተው ሰላም እንዲሰፍን ማድረጋቸውን በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ምዕራፍ 6፥1-5 የተጻፈው ቃል ይነግረናል። “በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፥ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና።አሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው፦ የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን። ይህም ቃል ሕዝብን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤”

ለዶክትሪን ጥብቅና መቆም

ሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ላይ አንዳንዶች ከይሁዳ ወርደው ልዩ ትምህርትን በማስተማር ማህበረ ምዕመናንን በማወካቸው ብዙ ጥልና ክርክር ሲሆን ሐዋርያትና ሽማግሌዎች በኢየሩሳሌም አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ፦ “ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ፤ ጤና ይስጣችሁ።” በማለት ፈጣን አስተዳደራዊ ውሳኔ አስተላልፈዋል። በጻፉትም ደብዳቤ ከአህዛብ ወገን ያመኑ ክርስቲያኖች እንደ ሙሴ ስርዓት መገረዝ ሳያስፈልጋቸው በሐዋርያት ትምህርት ከጸኑ ይበቃል በማለት እንዲረጋጉ አድርጎአቸዋል። እንዲሁም በገላትያ 1፥6-8፦ “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።” በማለት አንድ ጊዜ ፍጹም ሆኖ ለተሰጠው የወንጌል ሃይማኖት እንዲጋደሉ በማያወላዳ ሁኔታ አስጠንቅቀዋል። [ማር. 16፥8፤ ይሁዳ ቁ.3]

ነገሮችን በአዕምሮ/በልብ ስፋት ማየት

አስተዳደር የልብ ስፋት ይፈልጋል። በሐዋ.17፥11 ላይ የተጠቀሱት የቤርያ ሰዎች የልብ ስፋት ነበራቸው። “እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና፦ ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ።” ይላል። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 10 ላይ እግዚአብሔር ቆርኔሌዎስንና ቤተሰቡን ወዳጆቹንም በመላእክት እገዛና በራዕይ መገለጥ በጴጥሮስ አገልግሎት ካዳናቸው በኋላ፦ “ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ …።” ባሉት ጊዜ “ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱ ወረደላቸው።” ብሎ በትህትና ሲያስረዳቸው “ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና፦ እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ።” እንዲሉ አሰኝቶ መዳን ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን ለምድር ሕዝብ ሁሉ እንደሆነ መንፈስ ቅዱስ ወርዶ እንደመሰከረ ባስረገጠላቸው ጊዜ አእምሮአቸው ሰፍቶ ስለነርሱ /ስለ አሕዛብ/ መዳን እግዚአብሔርን ሊያከብሩ ችለዋል [ሐዋ.11፥3፤18]። ጌታ ኢየሱስ የአዕምሮ ወይም የልብ ስፋት እንዲሰጠን መጸለይም ያስፈልጋል።

መንፈሳዊ እገዛ

ወንጌላዊው ፊልጶስ በሰማርያ ወንጌልን ሰብኮ ብዙዎችን አሳምኖ በማጥመቅ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቢያስፋፋም አንድ የጎደለ ጸጋ ነበርና፦ ያንን ጸጋ እንዲቀበሉ የጸሎት እገዛ ያስፈልጋቸው ነበር። “በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው። እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤” (ሐዋ. 8፥14-15) በማለት እጅ ጭኖ በመጸለይ መንፈሳዊ እገዛ እንዳደረጉላቸው ቃሉ ይገልጣል። በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በእነርሱ አገልግሎት ስር የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች የሚጎድላቸውን ጸጋ በማየት የሚደገፉበትን ወይም የሚረዱበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚጠበቅባቸው ይህ እውነተኛ ታሪክ አቅጣጫ ይሰጣል።

ርኩሰትን ማውገዝ

የቆሮንቶስን ቤተክርስቲያን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ሰዎች በጣም ደፋር ሆኖ የአባቱን ሚስት እስከ ማግባት ከደረሰው ሰው ሁሉም ምዕመናን እንዲለዩ በማድረግ ቤተክርስቲያን ቅድስናዋን ጠብቃ እንድትኖር አድርገዋል። ክፉ የሠራውም እንዲወገዝ እንዲወገድም በማድረግ በድፍረት ፈርደዋል። “በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና። … ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ።” (1ኛ ቆሮ.5፥1-2)

መለያየትን መኮነን

1ኛ ቆሮንቶስ 1፥10-16 ሁላቸውም አንድ ንግግር እንዲናገሩ እንዲሁም በአንድ ሃሳብ እንዲስማሙ እንጂ በአንዳቸውም ልብ ውስጥ መለያየት አንዳይፈጠር አጥብቀው በማስተማር ሁሉም ወደ ሞተላቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመለከቱ አድርጎአቸዋል። መከፋፈልን ለመፍጠር የሚሞክሩትን ደግሞ በይሁዳ ቁ. 19 ላይ እንደተጻፈው፦ “እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው።” ብለው በድፍረት ኮንነዋል። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሳዔ ምክንያት በወንጌል ምስክርነት ወደ ቤተክርስቲያን የመጡት ነፍሳት ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚደርሱት በመልካም አመራርና አስተዳደር ጭምር ነው። ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መልካም መሪዎች በነበሩባቸው ዘመናት ሁሉ እስራኤል እግዚአብሔርን ያመልክ እንደነበር፤ መሪዎች በጠፉበት ዘመን ደግሞ ጣኦትን ይከተል እንደነበር በግልጥ ተጽፎአልና። በመሳፍንት መጽሐፍ 2፥10-11፦ “ትውልድ ሁሉ ደግሞ ወደ አባቶቻቸው ተከማቹ፤ ከእነዚያም በኋላ እግዚአብሔርን ለእስራኤልም ያደረገውን ሥራ ያላወቀ ሌላ ትውልድ ተነሣ። የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነ ነገር አደረጉ፥ በኣሊምንም አመለኩ።” ይላል። እንዲሁም በ1ኛ ዜና. 15፥3 “እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር።” ብሎ በእነዚያ መሪዎች በጠፉባቸው ዘመናት እስራኤል እርስ በርስ ይዋጋ እንደነበር ይገልጻል።

እንግዲህ፦ በቤተክርስቲያን ውስጥ በመሪነትና በአስተዳዳሪነት ኃላፊነት የተቀመጥን ሰዎች፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ለተከታዩ ለጢሞቴዎስ በ1ኛ ጢሞ. 4፥15 ላይ “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፥ ይህንም አዘውትር። ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።” እንዳለው እኛም ድነን፣ ሌሎችም እንዲድኑ በማድረጋችን እጥፍ ክብር የሚገባቸው “በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች” ተብለን ለመጠራት መትጋት፣ መጣር፣ መጣጣርም ይኖርብናል። 

አምላካችን እግዚአብሔር ሁላችንንም ይርዳን፣ ይደግፈን፣ ይምራንም!

Scroll to Top